1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምክር ቤታዊ ምርጫ በቡሩንዲ

ሰኞ፣ ሰኔ 22 2007

የሰሞኑ ዓመጽ እና ትችት ሳያግደው ዛሬ በቡሩንዲ የፓርላማ እና የማዘጋጃ ቤት ምርጫ ተካሄደ። በምሥራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገር የምርጫ ጣቢያዎች በይፋ በሀገሪቱ የሰዓት አቋጣጠር ከጠዋቱ 12 ዓመት ጀምሮ ክፍት እንደሚሆኑ ቢነገርም በርካታ የመዲና ቡጁምኑቡራ የምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱት ግን ቢያንስ ግማሽ ሰዓት አሳልፈው ነው።

https://p.dw.com/p/1Fpg8
Parlamentswahlen in Burundi
ምስል AFP/Getty Images/L. Nshimiye

[No title]

የቡሩንዲ ፖሊስ እንዳስታወቀው የታጠቁ ቡድናት ሌሊቱን በርካታ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት አድርሰዋል። እነዚህ ታጣቂዎችም በከተማ እና ከከተማ ውጪ በሚገኙ ጣቢያዎች ላይ ተኩስ ከፍተዋል። የእጅ ቦምብም አፈንድተዋል። እንዲያም ሆኖ በምርጫ ቁሳቁስ ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት አልደረሰም ተብሏል። የመዲና ቡጁምቡራ የምርጫ ኮሚቴ ኃላፊ ሲሪያክ ቡሱሚ፤ የምርጫ ጣቢያዎቹ ዘግይተው የተከፈቱት በሌሊቱ ተኩስ ምክንያት ነው ብለዋል። ስለሆነም በበርካታ ምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁሶቹ በሰዓቱ አልደረሱም ነበር። በዛሬው ምርጫ ከ 3,8 ሚሊዮን በላይ የሚሆን ህዝብ መምረጥ እንደሚችል ተገልጿል። ተቃዋሚዎች ለቀናት ምርጫው እንዳይካሄድ ሲያስተባብሩ ቆይተዋል። 70 ሰዎች በተገደሉበት ሁኔታ ተቃዋሚዎች ነፃ እና ገለልተኛ ምርጫ በሀገሪቱ ይካሄዳል ብለው አያምኑም። ተቃዋሚዎች ከአምስት ዓመታት በፊት የተካሄደውንም ምርጫ እንዲሁ ሊያጨናግፉ ሞክረው ነበር። በርግጥ ይህ መፍትሄ ሊሆን ይችላል? ያሁኑ ይለያል ይላሉ በሀገሪቱ ታዋቂው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ፒየር ክሌቨር ምቦኒምባ ፤« የአሁኑ እንደ 2010 ዓም እንደነበረው አይደለም። እኔ ራሴ ተቃዋሚዎቹን ፈርጄያቸው ነበር። ምርጫው ሲጀምር ራሳቸውን አሸሽተው ነበር። ማሸነፍ ይችሉ ነበር። አሁን ግን ያልተስተካከለውን ነገር አስቀድመው ነው የተረዱት። እኛም የሲቪሉ ማህበረሰብ ይህን ነው የተረዳነው።ሰው እያየ እሾህ አይረግጥም።»

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ኃላፊ ባን ጊ ሙን የቡሩንዲ መንግሥት አመፅ በተሞላበት ሁኔታ ምርጫው እንዲካሄድ መፍቀዱን ተችተዋል። ባን ባለፈው ዓርብ ምርጫው እንዲገፋ ሀሳብ አቅርበው ነበር፤ ይሁንና የቡሩንዲ መንግሥት ጥሪያቸውን አልተቀበለውም። የአፍሪቃ ህብረትም ቢሆን የቡሩንዲ ምርጫን አላወደሰም፤ እንደዉም ህብረቱ የዛሬውን የቡሩንዲን ምርጫ እንደማይታዘብ አሳዉቋል። ለዚህም ምክንያቱ ያለው ሁኔታ ነፃ እና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ይካሄዳል ብሎ ለማለት ስለማያስችል ነው ብሏል። ዛሬ ምርጫ ከወጡ መራጮች አንዱ ደግሞ «የምንፈልገውን ሰው ለመምረጥ ሊፈቅድልን ይገባል። አንድ ሰው ወጥቶ ካልመረጠ፤ ድምፁን ለሚፈልገው ሰው መስጠቱን ማወቅ አለባቸው። አሁን እዚህ ምን እንደሚሆን እየጠበቅን ነው። ሁላችንም ምስክር ነን። አሁን ሰላም እንዲሰፍን እየፀለይን ነው።

Parlamentswahlen in Burundi
ምስል AFP/Getty Images/L. Nshimiye

ባለፈው ግንቦት ወር ከመፈንቅለ መንግሥት የተረፉት የቡሩንዲ መሪ ፒየር ንኩሩንዚዛ የምርጫ ውጤቱን አስቀድመው ተንብየዋል። እንደ ፕሬዚዳንቱ ከምክር ቤቱ ምርጫ ፓርቲያቸው በምህፃሩ CNDD-FDD ከ ሁለት ሶስተኛው በላይ የምክር ቤት መቀመጫዎችን እንደሚያገኝ ርግጠኛ ናቸው። ይህ እውን ከሆነ ደግሞ ምክር ቤቱ ማንኛውንም ሕግ የማፅደቅ መብት ይኖረዋል። የፕሬዚዳንቱ ሐምሌ 8 በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሶስተኛ ጊዜ እጩ እሆናለሁ ማለት፤ በሀገሪቱ ከፍተኛ ዓመፅ አስነስቶ ነበር። ተቃዋሚዎች የንኩሩንዚዛ ሀሳብ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ነው ሲል ይተቻሉ። « እኝህ ሰው በስልጣን ላይ ለመቆየት ሕጋዊ አይደሉም ። ይህንን ደሞ የምለው እኔ ብቻ አይደለሁም፤ ኮፊ አናን፣ ሉዊዝ ሚካኤል ወይም የቤልጂየም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርም ቢሆኑ ተናግረዋል። ጊዜያቸው አክትሟል። ሌላ ሰው ሰለባ መሆን የለበትም፤ የቡሩንዲ ህዝብ የሚፈልገው ሰላም ነው።»

ይላሉ ከተቃዋሚዎቹ አንዱ፤ ለጊዜው ምሥራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገር ቡሩንዲ ህዝቧ ከሚመኘው ሰላም ብዙ ርቃ ትገኛለች።

ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ