1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሞስኮ፤ ሜርክልና ፑቲን የአበባ ጉንጉን አኖሩ

እሑድ፣ ግንቦት 2 2007

የኹለተኛዉ የዓለም ጦርነት የተጠናቀቀበትን ጊዜ አስመልክቶ ዛሬ የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልና የሩስያዉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሞስኮ ዉስጥ በሚገኘዉ በጦርነቱ የወደቁና ማንነታቸዉ የማይታወቅ ወታደሮች መካነመቃብር ላይ ኹለት የመታሰብያ የአበባ ጉንጉን አኖሩ።

https://p.dw.com/p/1FNlB
PK Putin und Merkel in Moskau
ምስል Reuters/Host Photo Agency/RIA Novosti

ከዚህ መካነመቃብር ላይ ኹለት የመታሰብያ የአበባ ጉንጉን ከማኖር ሥነ-ስርዓት በኋላ ኹለቱ መሪዎች ለምሳ ተገኛኝተዉ የሚያከናዉኑዋቸዉ ሥራዎች እንደነበሩ ነዉ የተገለፀዉ። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ወደ ሩስያ የተጓዙት ቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ናትሲ ጀርመንን ድል ያደረገችበት 70ኛ ዓመት በማስታወስ ቅዳሜ ሞስኮ ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ ሰልፍ የታየበት ዝግጅት ከተካሄደ በኋላ መሆኑ ነዉ። ሩስያ በዩክሬይኑ ቀዉስ ያላትን አቋም ተከትሎ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ጨምሮ በርካታ የምዕራብ ሃገራት መንግሥታት የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ያበቃበትን ዕለት በማስመልከት ትናንት ሞስኮ ላይ በተካሄደዉ ዝግጅት ላይ ሳይገኙ መቅረታቸዉ ይታወቃል። ፕሬዚዳንት ፑቲን በበኩላቸዉ ምዕራባዉያኑ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ያለመገኘታቸዉ ቁብ እንዳልሰጣቸዉ ነዉ ያመላከቱት። እንድያም ሆኖ ትናንት ሞስኮ ላይ በተካሄደዉ ከፍተኛ ዝግጅት የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ኪ ሙን፤ የቻይና መንግሥት እና የፓርቲ መሪ ሺ ጂንፒንግ እንዲሁም የኩባዉ ፕሬዚዳንት ራዉል ካስትሮ ተገኝተዉ ነበር።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ