1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ጥር 25 2001

ያለፈው ሣምንት በዓለም ዙሪያ በርከት ያሉ የስፖርት ውድድሮች የተካሄዱበት ነበር።

https://p.dw.com/p/GljO
ቡንደስሊጋ፤ የሆፈንሃይም ጎል አግቢ ዴምባ-ባ
ቡንደስሊጋ፤ የሆፈንሃይም ጎል አግቢ ዴምባ-ባምስል AP

በዚህ በጀርመን በክረምት ዕረፍት ላይ የነበረውና በእግር ኳስ ተመልካቹ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው የቡንደስሊጋ ውድድር ባለፈው ሣምንት አጋማሽ በፌደሬሺኑ ዋንጫ ጥሎ-ማለፍ ግጥሚያዎች አሃዱ ካለ በኋላ ሰንበቱን እንደገና ቀጥሏል። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎናን ከምጥቀቱ የሚያቆም ተፎካካሪ በዚህ ሣምንትም አልተገኘም፤ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደግሞ ሰንበቱ የቼልሢይ አልነበረም።

በዚሁ በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እንጀምርና ማንቼስተር ዩናይትድ በተከታታይ 12ኛ ድሉ የሻምፒዮናው ቁንጮነቱን አጠናክሯል። ዩናይትድ ኤቨርተንን 1-0 ሲያሸንፍ የድል ጎሏን በፍጹም ቅጣት ምት ያስቆጠረው ያለፈው ዓመት የዓለም ድንቅ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠው የፖርቱጋል ኮከብ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነበር። ማንቼስተር ዩናይትድ ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ አንድ ጨዋታ ጎሎት በሁለት ነጥብ ልዩነት ይመራል። ሊቨርፑል ምንም እንኳ የሣምንት ግጥሞያውን በስኬት ቢወጣውም በሁለተኝነት መወሰኑ ግድ ነው የሆነበት።
በሌላ በኩል በዚሁ በሊቨርፑል 2-0 የተረታው ቼልሢይ የዘንድሮ የሻምፒዮንነት ተሥፋው ከንቱ እንዳይሆን በጣሙን ያሰጋዋል። በነገራችን ላይ ለሊቨርፑል ሁለቱን የድል ግቦች ያስቆጠረው የስፓኙ ኮከብ ፌርናንዶ ቶሬስ ነበር። ቼልሢይ ከትናንት ሽንፈቱ በኋላ ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር የአምሥት ነጥቦች ልዩነት ሲኖረው ከአራተኛው ከኤስተን ቪላ ጋር እኩል ነጥብ ይዞ በጎል ብልጫ ብቻ ሶሥተኛ ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን በዚህ ሰንበትም ቀደምቱን ባርሤሎናን ከሬኮርድ ሂደቱ ሊገታው የቻለ አልተገኘም። ባርሣ ሣንታንዴርን ለዚያውም ከኋላ ተነስቶ 2-1 በመርታት በ 12 ነጥቦች ልዩነት ተዝናንቶ መምራቱን ቀጥሏል። ቡድኑን ከእረፍት በኋላ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር እንዳለፈው ሣምንት ሁሉ ለድል ያበቃው የአርጄንቲናው የኳስ ተዋናይ ሊዮኔል ሜሢ ነበር። ያለፈው የውድድር ወቅት ሻምፒዮን ሬያል ማድሪድ ደግሞ ኑማንሢያን 2-0 አሽንፎ በአስተማማኝ ሁለተኛ ቦታው ላይ እንዳለ ቢሆንም የ 12 ነጥብ ልዩነቱን አስወግዶ ባርሤሎና ላይ ሊደርስ መቻሉ ቢቀር በወቅቱ ሊያምኑት የሚያዳግት ነው።
በተረፈ ሬያልን የሚከተሉት ሤቪያ፣ ቪላርሬያልና አትሌቲኮ ማድሪድ ሁሉም በሰንበት ግጥሚያቸው ሲሽነፉ በሶሥተኛው ሤቪያና በሬያል ማድሪድ መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ስድሥት ከፍ ብሏል። በጎል አግቢነት አሁንም 19 በማስቆጠር የባርሤሎናው ሣሙዔል ኤቶ የሚመራ ሲሆን ዴቪድ ቪያ ከቫሌንሢያ በ 17 ጎሎች ሁለተኛ ነው፤ ሊዮኔል ሜሢ ደግሞ ከ 16 ደርሷል።

በኢጣሊያ አንደኛ ዲቪዚዮን-ሤሪያ-አ. በዚህ ሰንበት ከቀደምቱ ሶሥት ክለቦች መካከል ለድል የበቃው ኤ.ሢ.ሚላን ብቻ ነበር። ሚላን ላሢዮን በአስተማማኝ ሁኔታ 3-0 ሲረታ የእንግሊዙ ኮከብ ዴቪድ ቤክሃም አንዴ በማቀበል ሌላ ጊዜም በግሩም ቅጣት ምት አሌሣንድሬ ፓቶና ማሢሞ አምብሮሢኒ ላስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ቀጥተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሶሥተኛዋን ጎል ያስቆጠረው ደግሞ ብራዚላዊው ካካ ነበር። ኤ.ሢ.ሚላን አሁን ሁለተኛ ነው።
በስድሥት ነጥቦች ልዩነት ሊጋውን ሲመራ የሰነበተው ኢንተር ሚላን በአንጻሩ ከቶሪኖ ጋር 1-1 በሆነ ውጤት ሲወሰን ጁቬንቱስ ደግሞ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ በደረሰበት ሽንፈት ወደ ሶሥተኛው ቦታ አቆልቁሏል። በተረፈ ጌኖዋ አራተኛ፤ ኤ.ኤስ.ሮማ ደግሞ አምሥተኛ ነው። በጎል አግቢነት 15 አስቆጥሮ በብቸኘት የሚመራው የቦሎኛው ማርኮ ዲ-ቫዮ ሲሆን ሌሎች አራት ተጫዋቾች በአንዳንድ ጎል ልዩነት በቅርብ ይከተሉታል።

ከክረምት ዕረፍት በኋላ ሁለተኛ ዙር ውድድሩን በከፈተው የጀርመን ቡንደስሊጋ በሣምንቱ አጋማሽ ላይ በፌደሬሺኑ ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ግጥሚያዎች ብርቱ ጥንካሬ ያሳዩት ቀደምት ክለቦች ባየርን ሙንሺንና ብሬመን ጥሩ አጀማመር ለማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ባየርን ሙንሺን በሃምቡርግ 1-0 ሲረታ፤ ብሬመንም በገዛ ሜዳው በቢለፌልድ 2-1 ተሽንፎ ወጥቷል። ብሬመን እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ከእረፍት መልስ የደነዘዘ መስሎ ነው የታየው። አሠልጣኙ ቶማስ ሻፍም ሽንፈቱ ተገቢ እንደነበር አረጋግጧል።
“ዛሬ ብዙ ነገር ማሣየት አልተቻለንም። ቅልጥፍናን፣ የመጀመሪያ ዕርምጃንና የፍጥነት አጨዋወትን በተመለከተ! በመሆኑም ለማሸነፍ አልቻልንም። ቀላል ነገር ነው! ተጋጣሚያችን ያገኘውን ዕድል ሁሉ ተጠቅሞበታል። ለዚህም ነው ያሸነፈው”

ሃምቡርግና በርሊን በግሩም ጨዋታ በሁለተኛና በሶሥተኛ ቦታ ሲቆናጠጡ ሊጋውን በሁለት ነጥቦች ልዩነት መምራት የቀጠለው ከሁለተኛ ዲቪዚዮን የወጣ አስደናቂ ክለብ ሆፈንሃይም ነው። ሆፈንሃይም ምንም እንኳ ሊጋውን በ 18 ጎሎች የሚመራውን የቆሰለበትን አጥቂ ቬዳድ ኢቢዜቪችን መተካት ቢኖርበትም አንዳች ድክመት አልታየበትም። ባየርን ሙንሺን አራተኛ ሲሆን እኩል ለእኩል የተለያዩት ሌቨርኩዝንና ዶርትሙንድ አምሥተኛና ስድስተኛ ናቸው።

በተቀረ በፈረንሣይ ሊጋ ሁለቱ ቀደምት ክለቦች ኦላምፒክ ሊዮንና ቦርዶ በየበኩላቸው ባካሄዷቸው ግጥሚያዎች ግጥሚያዎች በአኩል ለእኩል ውጤት ሲወሰኑ በሰንበቱ የአመራር ለውጥ አልታየም። ተጠቃሚው ኬንን 2-0 በመርታት በሶሥተኝነት ሊቀርባቸው የበቃው ፓሪስ ሣን-ዠርማን ነው። ኦላምፒክ ማርሤይ፣ ሬንስና ቱሉዝ ደግሞ አንዲት ነጥብ ወረድ ብለው ይከተሉታል።

በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ሮተርዳምን 2-0 የረታው ቀደምቱ አልክማር የቅርብ ተፎካካሪውን የአያክስ አምስተርዳምን ሽንፈት በመጠቀም አመራሩን ወደ ዘጠኝ ነጥብ ሲያሰፋ ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን አይንድሆፈንም ዱቲንኸምን 3-0 በመርታት ቢቀር በአምሥተኛ ቦታው ተቆናጧል። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶ ቤንፊካን አስከትሎ በአንዲት ነጥብ ልዩነት መምራት ሲቀጥል ስፖርቲንግ በሶሥተኝነት ይከተላል።
የቀደምቱ የአውሮፓ ሊጋዎች ሁኔታ ከሞላ-ጎደል ይህን የመሰለ ነው፤ በአፍሪቃ የሻምፒዮና ሊጋ የመጀመሪያ ዙር አንደኛ ግጥሚያዎች ከተመዘገቡት ውጤቶች መካከል ደግሞ የሚከተሉት ይገኙበታል። የሤኔጋል ዱዋኔስ ከሢየራሌዎን ፖርትስ-አውቶሪቲ 3-1፤ ያንግ-አፍሪካንስ (ታንዛኒያ) ከኤቶል (ኮሞሮስ) 8-1፤ ካኖ-ፒላርስ (ናይጄሪያ) ከኤሌክት-ስፖርት (ቻድ 2-0፤ አል-ሜራይክ (ሱዳን) ከአትራኮ (ሩዋንዳ) 2-1፤ ፕሪሜሮ-አጎስቶ (አንጎላ) ከሬኔሣንስ (ኮንጎ) 5-2፤ ሤስኮ-ዩናይትድ (ዛምቢያ) ከማታሬ-ዩናይትድ (ኬንያ) 2-0፤ እንዲሁም አል-አህሊ-ትሪፖሊ ከፖሊስ (ኒጀር) 6-0 ተለያይተዋል።

ትናንት ጃፓን ውስጥ ቤፑ-ኦይታ ላይ በተካሄደ የወንዶች ማራቶን ሩጫ የሞሮኮው ተወላጅ አዲል አናኒ በ 2 ሰዓት ከ 10 ደቂቃ ከ 15 ሤኮንድ ጊዜ አሸናፊ ሆኗል። አናኒ ሙሉውን የማራቶን ርቀት ሲያዳርስ የትናንቱ ገና ለሶሥተኛ ጊዜ ሲሆን ሩጫውን ያሽነፈው በ 37ኛው ኪሎሜትር ላይ ተፎካካሪዎቹን አምልጦ በመሮጥ ነው። ሁለተኛና ሶሥተኛ የወጡት ጃፓናውያኑ ሤይጂ ኮባያሺና ኬይታ አኪባ ናቸው። ኒውዮርክ ውስጥ በሣምንቱ መጨረሻ ተካሂዶ በነበረ የሚልሮዝ ጨዋታ የአውስትራሊያው የምርኩዝ ዝላይ የኦሎምፒክ ባለድል ስቲቭ ሁከር 6,1 ሜትር በመዝለል አስደናቂ ውጤት አስመዝግቧል። ሁከር በአዳራሽ ውስጥ ውድድር ከስድሥት ሜትር በላይ ሲዘል አራተኛው አትሌት መሆኑ ነው።
ኬንያዊው-አሜሪካዊ በርናርድ ላጋት ደግሞ የማይል አሸናፊ ሆኗል። በሌላ የስፖርት ዜና ኬንያዊቱ የዓለም አምሥት ሺህ ሜትር የብር ሜዳይ ተሸላሚ ቪቪያን ቼሩዮት በሚቀጥለው ወር የዓለም የአዳራሽ ውስጥ ሻምፒዮና ከመሠረት ደፋር ጋር በሶሥት ሺህ ሜትር ለመወዳደር ማቀዷን ባለፈው ሰንበት አስታውቃለች። መሠረት በዚህ ርቀት ሁለት ዓመት ያለፈውን ክብረ-ወሰን ለመስበር እንደምትጥር ነው የሚጠበቀው። በተረፈ ግላስጎው ላይ በተካሄደ የሃገራት የአዳራሽ ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድር በአጠቃላይ ነጥብ የኮመንዌልስ ምርጥ ሲያሸንፍ፤ ብሪታኒያ ሁለተኛ፤ ጀርመን ሶሥተኛ፤ እንዲሁን ስዊድን አራተኛ ሆነዋል።

ክሮኤሺያ ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው የዓለም የዕጅ ኳስ ሻምፒዮና ትናንት በፈረንሣይ አሸናፊነት ተፈጽሟል። ያለፈው ኦሎምፒክ ሻምፒዮን ፈረንሣይ ለዚህ ክብር የበቃችው ዛግሬብ ላይ በተካሄደው የፍጻሜ ግጥሚያ አስተናጋጇን ክሮኤሺያን ልዕልና በተመላበት ሁኔታ 24-19 በመርታት ነው። የክሮኤሺያ ቡድን ቢቀር ለፍጻሜ በመድረሱ ሊጽናና ይገባዋል። ያለፈው ሻምፒዮና ባለድል ጀርመን በአንጻሩ ባለፈው ሣምንት ቀደም ብላ በሩብ ፍጻሜው ዙር መሰናበቷ የሚታወስ ነው።

ዘገባችንን በቴኒስ ለማጠቃለል ሰሞኑን ሲካሄድ የሰነበተው ታላቁ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድር “አውስትራሊያን-ኦፕን” በቀደምት ከዋክብቶች የፍጻሜ ግጥሚያ በአስደናቂ ሁኔታ ተፈጽሟል። በወንዶች ሮጀር ፌደረርንና ራፋኤል ናዳልን የመሳሰሉት ሃያል ተጫዋቾች ለፍጻሜ ሲቀርቡ ግጥሚያው የለየለት ከአራት ሰዓት በላይ በፈጀ ጊዜ ነው። የስፓኙ ኮከብ ራፋኤል ናዳል በሰከነ ጨዋታው በማሸነፍ በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ ቁንጮ ሆኖ የቆየውን የፌደረርን አልጋ በከንቱ እንዳልወረሰ በሚገባ አሳይቷል። በነገራችን ላይ ናዳል በአውስትራኢያን-ኦፐን ሲያሸንፍ የመጀመሪያው የስፓኝ ተወላጅ መሆኑም ነው።

በሴቶች ደግሞ አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ባሳየችው ጥንካሬ በመቀጠል በአውስትራሊያን-ኦፕን አራተኛ ድሏን ለመቀዳጀት በቅታለች። ዊሊያምስ ሩሢያዊቱን ዲናራ ሣፊናን በፍጹም የበላይነት ስታሸንፍ በቴኒሱ የማዕረግ ተዋረድ ላይ ከስምንት ዓመታት በኋላ እንደገና ወደ መጀመሪያው ቦታ መመለሷ ነው።

MM