1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መጋቢት 7 2001

የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋና የቀደምቱ ዲቪዚዮኖች የእግር ኳስ ውድድር፣ አትሌቲክስ፣ ቴኒስና የቢስክሌት እሽቅድድም።

https://p.dw.com/p/HDOt
ሄርታ-በርሊን ከሰንበቱ ድል በኋላ
ሄርታ-በርሊን ከሰንበቱ ድል በኋላምስል picture-alliance/ dpa

እግር ኳስ

የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር እየገፋ መጥቶ ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ላይ ወደ ሩብ ፍጻሜው ተሸጋግሯል። ወደተከታዩ ዙር ያለፉት ስምንት ክለቦች ማን ከማን እንደሚገናኝ ዕጣ የሚወጣው በፊታችን ቅዳሜ ነው። ከሣምንቱ ውጤቶች በኋላ በሶሥት ክለቦች ተሳታፊነት በውድድሩ በመቀጠል እንዳለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም የሊጋ ጥንካሬ በማሣየት ላይ ያለችው እንግሊዝ ናት። በወቅቱ የፕሬሚር ሊጉን አመራር ይዞ የሚገኘው ማንቼስተር ዩናይትድ በመጀመሪያው ጨዋታ ከኢንተር ሚላን ባዶ ለባዶ ከተለያየ በኋላ የመልስ ግጥሚያውን 2-0 በማሽነፍ የኢጣሊያውን ሻምፒዮን በለየለት ሁኔታ አሰናብቷል።

ይሄው ያለፈው ረቡዕ ግጥሚያ ማንቼስተር ዩናይትድ በአውሮፓ ክለቦች ውድድር ለ 21ኛ ጊዜ ሳይሽነፍ በመቀጠል አዲስ ክብረ-ወሰን ያስመዘገበበትም ነበር። ጁቬንቱስ ቱሪን በአውሮፓው ሻምፒዮና በልዕልና ዘመኑ ከ 1970 እስከ 1972 ዓ.ም. ድረስ በሃያ ግጥሚያዎች ሳይሽነፍ ሁለተኛነቱን እንደያዘ ነው። ማንቼስተር ለመጨረሻ ጊዜ በኤ.ሢ.ሚላን ተረትቶ ከሻምፒዮና ሊጋው ግማሽ ፍጻሜ ውድድር የወጣው ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በአውሮፓ ጠንካራው መሆኑን የተቀሩት ተሳታፊ ክለቦችም አስመስክረዋል። ቼልሢይ ጁቬንቱስን፤ ሊቨርፑልም የስፓኙን ሻምፒዮን ሬያል ማድሪድን ከውድድሩ ሲያስወጡ በተለይ ሊቨርፑል ሬያልን በአጠቃላይ ውጤት 5-0 መሸኘቱ በዕውነትም የልዕልና ምልክት ነው።
አርሰናልም እንዲሁ በመጀመሪያው ግጥሚያ በሮማ 1-0 ከተሸነፈ በኋላ በፍጹም ቅጣት ምት 7-6 በሆነ ውጤት በለየለት የመልስ ግጥሚያ ወደተከታዩ ዙር አልፏል። ሁለቱ የስፓኝ ክለቦች ባርሤሎናና ቪላርሬያልም ወደ ሩብ ፍጻሜው ዙር መሻገሩ ሲቀናቸው ሶሥተኛው የስፓኝ ክለብ አትሌቲኮ ማድሪድ ግን በፖርቱጋሉ ሻምፒዮን በፖርቶ ከወዲሁ መሰናበቱ ግድ ነው የሆነበት። በተቀረ የጀርመኑ ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺን ስፖርቲንግ ሊዝበንን በታላቅ ልዕልና ከውድድሩ አስወጥቷል። ባየርን ለሩብ ፍጻሜው ያለፈው ስፖርቲንግን በመጀመሪያ 5-0 ከዚያም በመልሱ ግጥሚያ 7-1 በሆነ ውጤት እንዳልነበር አድርጎ በመሸኘት ነው። እርግጥ የጀርመኑ ሻምፒዮን የአስካሁን ግጥሚያዎቹን በቀላሉ ቢወጣም ተከታዩ ዙር ግን ቀላል የሚሆንለት አይመስልም። ቢሆንም አሠልጣኙ ዩርገን ክሊንስማን ለመደናገጥ ምክንያት የለም ባይ ነው።

“እርግጥ ዕጣው ግሩምና ማራኪ ተጋጣሚ እንደሚያመጣልን ተሥፋ እናደርጋለን። ቡድናችን እስካሁን በሁለም የሻምፒዮና ሊጋ ጨዋታዎች ያለውን ጥንካሬ በሚገባ ነው ያሣየው። ከመጨረሻዎቹ ስምንት ቡድኖች አንዱ ለመሆን በቅተናል። ስለዚህም አውሮፓ ውስጥ ማንንም፤ በእግግጥ ማንንም የምንፈራበት ምክንያት አይኖርም። የተቀሩት ቡድኖች በሙሉ ጠንካራ መሆናቸው ግን የማያጠያይቅ ነገር ነው”

ወደ ሰንበቱ የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር እንሻገርና ባርሤሎና በትናንት ግጥሚያው አልሜይራን 2-0 በመርታት አመራሩን መልሶ ወደ ስድሥት ነጥቦች ለማስፋት በቅቷል። ተከታዩ ሬያል ማድሪድ አንድ ቀን ቀደም ሲል አትሌቲኮ ቢልባዎን 5-2 በማሸነፍ የባርሣን አመራር ለጊዜውም ቢሆን በሶሥት ነጥብ ገድቦት ነበር። ቫሌንሢያ ከሁዌልቫ 1-1 ሲለያይ ሶሥተኛው ሤቪያም ከማላጋ ጋር 2-2 በሆነ ውጤት በመወሰኑ ሬያል ላይ ለመድረስ የሚያደርገው ጥረት አልተዋጣለትም። በሻምፒዮናው ሊጋ የቀናው ቪላርሬያል ደግሞ በአትሌቲኮ ማድሪድ 3-2 ተሸንፎ ወደ አምሥተኛው ቦታ አቆልቁሏል። የስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ውድድር ሊጠናቀቅ 11 ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ዘንድሮ ሻምፒዮናው በባርሣና በሬያል መካከል የሚለይለት እየመሰለ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን ካለፈው ረቡዕ የሻምፒዮና ሊጋ ሽንፈቱ በማገገም ፊዮሬንቲናን 2-0 ሲረታ የሰባት ነጥብ ልዩነት አመራሩን ሳያስነካ ቀጥሏል። ጁቬንቱስ ቦሎኛን ከኋላ ተነስቶ 4-1 በማሸነፍ በሁለተኝነቱ ሲቆናጠጥ ሢየናን 5-1 የሸኘው ኤ.ሢ.ሚላን ደግሞ ሶሥተኛ ነው። ለኤሢ.ሚላን ከአምሥት ሁለቱን ጎሎች ላስቆጠርው የብሄራዊው ቡድን አጥቂ ፊሊፖ ኢንዛጊ የትናንት የመጨረሻ ግቡ በእስካሁን ጨዋታው 300ኛዋ ነበረች። ይሄው አሃዝ አደገኛ ጎል አግቢ መሆኑን የሚመሰክር ነው። በጠቅላላው ኢንተር በሻምፒዮንነት አቅጣጫ ሲገሰግስ 12 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ለሚገኘው ለኤ.ሢ.ሚላን ግን ዘንድሮ የዋንጫ ባለቤት የመሆን ዕድሉ ያለቀለት ነው የሚመስለው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሰንበቱ ከሶሥቱ ቀደምት ክለቦች ሁለቱ የተፈታተሹበት ነበር። ሊቨርፑል ባለፈው ቅዳሜ በኦልድ-ትሬፈርድ ስታዲዮም በተካሄደው ግጥሚያ 4-1 አሸንፏል። ለ 11 ግጥሚያዎች ሳይሽነፍ የቆየው ማንቼስተር ዩናይትድ ለዚያውም በገዛ ሜዳው በዚህ መጠን ይሸነፋል ብሎ ያሰበ ብዙ አልነበረም። ማኒዩ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ባስቆጠራት የፍጹም ቅጣት ምት ግብ ቢመራም የሊቨርፑልን ድንቅ ቡድን ጨርሶ አላስበረገገም። ፌርናንዶ ቶሬስ በመጀመሪያ ውጤቱን ሲያስተካክል ስቲቭን ዤራርድ፣ ፋቢዮ አውሬሊዮና አንድሬያ ዶሤና ደግሞ የተቀሩትን የድል ጎሎች ለማስቆጠር በቅተዋል።
የሊቨርፑል ድል ለሻምፒዮናው የሚደረገው ፉክክር አዲስ ነፍስ እንዲዘራ ነው ያደረገው። ሌላው ቀደምት ቡድን ቼልሢይም ትናንት ማንቼስተር-ሢቲይን 1-0 በመርታት አለሁ ማለቱን እንደቀጠለ ነው። ማንቼስተር ዩናይትድ ቢሸነፍም በአራት ነጥቦች ብልጫ ሊጋውን እየመራ ሲሆን ቼልሢይና ሊቨርፑል አራት ነጥቦች ወረድ ብለው ሁለተኛና ሶሥተኛ ናቸው። ሶሥቱም የሻምፒዮንነት ዕድላቸውን እንደጠበቁ ይቀጥላሉ። አርሰናልና ኤስተን-ቪላ በ 52 ነጥብ አራተኛና አምሥተኛ ሲሆኑ ኤቨርተን ስድሥተኛ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ሄርታ-በርሊን ሌቨርኩዝንን 1-0 በማሽነፍ በአራት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ቀጥሎበታል። በዚህም ሰንበት የበርሊን የድል ዋስትና ባለፉት ስድሥት ግጥሚያዎች በጠቅላላው ስምንት ጎሎችን ያስቆጠረው የኡክራኒያው ተወላጅ አንድሬ ቮሮኒን ነበር። የበርሊን ደጋፊዎች ፈንጠዝያ ከሣምንት ሣምንት እየጨመረ ቢሄድም አሠልጣኙ ሉሢየን ፋቭር ድሉ ጥቂትም ቢሆን የዕድል እንደነበር አላጣውም።

“እጅግ በጣም በጣም ተደስተናል። ግልጽ ነው፤ ከሌቭርኩዝን ጋር 1-0 መውጣት። በሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት ሻል ያልን ነበር። እና ይበልጥ ወደፊት እየተጫወትን እንዳለ ከዕድል ጋር ጎል ለማስቆጠር ችለናል።, ግን አንድሬ ጎሏን ምናልባት ቀድሞ ማስገባት ነበረበት”


ያም ሆነ ይህ ባየርን ሙንሺን ቦሁምን በቀላሉ 3-0 በመርታት ሁለተኛ ሲሆን ቮልፍስቡርግም ሻልከን 4-3 በማሽነፍ ሶሥተኝነቱን ይዟል። ሃምቡርግም ትናንት ኮትቡስን 2-0 በመሸኘት አራተኛ ሲሆን ሶሥቱም ቡድኖች እኩል 45 ነጥብ ነው ያለቸው። ሆፈንሃይም በ 43 ነጥቦች አምሥተኛ ነው። የቡንደስሊጋው ውድድር ሊጠናቀቅ ገና አሥር ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ በመሠረቱ በስድሥት ነጥቦች ብቻ የሚለያዩት አምሥቱም ክለቦች ሻምፒዮን የመሆን ዕድል አላቸው።

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት ደቡብ ኮሪያ-ሶውል ላይ በተካሄደ ዓለምአቀፍ የማራቶን ውድድር በወንዶች ኬንያዊው ሞሰስ አሩሣይ በ 2 ሰዓት ከ 7 ደቂቃ ከ 54 ሤኮንድ አሸናፊ ሆኗል። ኢትዮጵያዊው ደጀኔ ይርዳው ሁለተኛ ሲወጣ ሩጫውን ሶሥተኛና አራተኛ በመሆን የፈጸሙትም የኬንያ አትሌቶች ናቸው። ኮሪያዊው ጂ-ያንግ-ጁን ደግሞ ሩጫውን በአምሥተኝነት ፈጽሟል። በሴቶች ማራቶን ሮቤ ቶላ ስታሸንፍ ኮሪያዊቱ ሊ-ሱንግ-ያንግ ሁለተኛ፤ የሕዝባዊት ቻይና ተወዳዳሪ ዋይ-ያናን ደግሞ ሶሥተኛ ሆናለች።

ባለፈው ቅዳሜ ሃግ ላይ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ሩጫ አዲስ የዓለም ክብረ-ወሰን ለማስመዝገብ አልሞ የነበረው ሃይሌ ገብረ-ሥላሴ በኬንያዊው አትሌት በሣሚይ-ኪሮፕ-ኪትዋራ በመቀደም ያሰበው ሳይሳካለት ቀርቷል። ኪትዋራ ሩጫውን በ 59 ደቂቃ ከ 47 ሤኮንድ ሲፈጽም ሌላው ኬንያዊ ሣሙዔል ዋንጂሩ ከሁለት ዓመታት በፊት በዚያው ስፍራ አስመዝግቦት ከነበረው ፈጣን ጊዜ ላይ ሊደርስ አልቻለም። ቢሆንም አምሥት መቶ ሜትር ያህል ሲቀረው ሃይሌን ጥሎ በመሄድ በአስደናቂ ሁኔታ ነው ያሸነፈው። ሃይሌ ራሱ “ሣሚይ በመጨረሻው መታጠፊያ ላይ አልፎኝ ሲሄድ በማየቴ በጣም ነው የተደነቅኩት፤ ግሩም ሩጫ ነበር” ሲል ነው ኬንያዊው የተሻለው ሯጭ እንደነበር ያረጋገጠው።

ቴኒስ

በካሊፎርኒያ የኢንዲያን-ዌልስ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድር በወንዶች በዓለም የማዕርግ ተዋረድ ላይ አንደኛው የሆነው ራፋኤል ናዳል ጀርመናዊ ተጋጣሚውን ሚሻኤል ቤረርን በሁለት ምድብ ጨዋታ በለየለት ሁኔታ በማሸነፍ ወደ ሶሥተኛው ዙር አልፏል። ሻምፒዮኑ ናቫክ ጆኮቪችም ብርቱ ትግል ቢገጥመውም የአርጄንቲና ተጋጣዊውን ቫሣሎ አርጉዌሎን ለማሸነፍ በቅቷል። ከሌሎቹ ወደ ሶሥተኛው ዙር ከተሻገሩት መካከል አርጄንቲናዊው ዴል ፖርቶ፣ የስፓኙ ዴቪድ ፌሬር፤ እንዲሁም አሜሪካውያኑ ኤንዲይ ሮዲክና ማርዲይ ፊሽ ይገኘታል። በሴቶች ደግሞ ሩሢያውያኑ ዲናራ ሣፊናና ቬራ ዝቮናሬቫ፤ አሜሪካዊቱ ጂል ክሬይባስ፣ የፖላንዷ ኡርሱላ ራድቫንስካና የእሥራኤሏ ሻሃር ወደ ተከታዩ ሶሥተኛ ዙር ተሻግረዋል።

ቢስክሌት

በቢስክሌት እሽቅድድም የስፓኙ ሉዊስ ሣንቼዝ ትናንት በአጠቃላይ ውጤት የፓሪስ-ኒስ አገር አቁዋራጭ ውድድር አሸናፊ ሆኗል። በኢጣሊያ የቲሬኖ-አድሪያቲኮ እሽቅድድም ደግሞ ጀርመናዊው አንድሬያስ ክሎደን አምሥተኛውን ደረጃ በአሸናፊነት ሲወጣ በአጠቃላይ ነጥብም እየመራ ነው።

Mesfin Mekonnen