1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሣምንታዊ የስፖርት ጥንቅር

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 2006

አርሰናል በማንቸስተር ሲቲ 6 ለ3 ተረቶ ግስጋሴው ጋብ ሲል፤ ሊቨርፑል ቶትንሐም ሆትስፐርን 5 ለ ባዶ በማንኮታኮት አርሰናልን ተናንቆታል። አርሰናል በሻምፒዮንስ ሊጉ ኃያሉ ባየር ሙንሽን ይጠብቀዋል። ሌሎች ዘገባዎችንም አሰናድተናል።

https://p.dw.com/p/1Aahc
ምስል Reuters

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 35 ነጥብ ይዞ በቀዳሚነት የሚገኘው አርሰናል ከትናት በስትያ በማንቸስተር ሲቲ አይቀጡ ቅጣት ከተቀበለ በኋላ ብቸኛ ግስጋሴው ጋብ ብሏል። ሊቨርፑል በግብ አዳኙ ሉዊስ ሱዋሬዝ ፊታውራሪነት ቶትንሐም ሆትስፐርን 5 ለባዶ ረምርሞ ከአርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ተሳክቶለታል። አሁን በሊቨርፑል እና በአርሰናል መካከል የነጥብ ልዩነቱ ሁለት ብቻ ሆኗል።

ለሊቨርፑል ትናንት በ17ኛው ደቂቃ የመጀመሪያዋን ለእራሱ ደግሞ 16ኛውን ግብ ከመረብ ያሳረፈው ሉዊስ ሱዋሬዝ ነበር። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ መጠናቀቁን የሚገልፀው የዳኛው ፊሽካ ሲነፋ ሊቨርፑል በጆርዳን ሔንደርሰን አማካኝነት ባስቆጠረው ግብ 2 ለባዶ እየመራ ነበር። ከእረፍት መልስ በ63ኛው ደቂቃ ላይ የሱዋሬዝን ጎድን በጫማው የረገጠው ፓውሊንሆ ከሜዳ መሰናበቱ ቶትንሐም ለማንሰራራት የነበረውን ተስፋ አጨለልሞበታል። አፍታም ሳይቆይ ሱዋሬዝ ለፍላንጋና ያመቻቻት ኳስ ከመረብ ታርፍና ሊቨርፑል 3 ለባዶ መምራቱን ይቀጥላል። በዕለቱ ኮከብ የነበረው ይኸው ሱዋሬዝ አራተኛዋን ግብ በማስቆጠር አምስተኛዋን ራሂም ስቴርሊንግ እንዲያሳርግባት አመቻችቶለታል። በትናንቱ ጨዋታ ሽቴቨን ጄራርድ ባለመሰለፉ ሉዊስ ሱዋሬዝ የቡድኑ አንበል ነበር፤ እናም ምሽቱ ለሱዋሬዝም ለሊቨርፑልም ስኬታማ ነበር።

ማንቸስተር ዩናይትድ
ማንቸስተር ዩናይትድምስል Reuters

ማንቸስተር ዩናይትድ በበኩሉ ትናንት አስቶን ቪላን ገጥሞ 3 ለባዶ ቢያሸንፍም በደረጃ ሠንጠረዡ ዝቅ ብሎ መቃተቱ አልቀረለትም። ማን ዩናይትድ የደረጃ ሠንጠረዡን ከሚመራው አርሰናል በ10 ነጥቦች ዝቅ ብሎ 25 ነጥብ በመያዝ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ትናንት በተደረገ ሌላ ጨዋታ ኖርዊች ሲቲ እና ስዋንሲ ሲቲ አንድ እኩል አቻ ወጥተዋል። ከትናንት በስተያ አርሰናል በማንቸስተር ሲቲ 6 ለ 3 በመሸነፉ የተነሳ ባለበት ሲረጋ፤ ማንቸስተር ሲቲ ከተቀናቃኙ አርሰናል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ አድርጎታል። ቸልሲ ክሪስታል ፓላስን 2 ለ አንድ በማሸነፍ እንደ ሊቨርፑል በ33 ነጥብ ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኤቨርተን ፉልሐምን 4 ለ 1፣ ካርዲፍ ሲቲ ዌስት ብሮሚች አልቢዮን 1 ለባዶ አሸንፈዋል። ኒውካስል ከ ሳውዝ ሐምፕተን አንድ እኩል፤ ዌስት ሐም ዩናይትድ እና ሰንደርላንድ ያለምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል። 9 ነጥብ ብቻ ያለው ሰንደርላንድ በደረጃ ሠንጠረዡ ጠርዝ ላይ ይገኛል።

ትናንት ከመረብ ያስቆጠራቸውን ሁለት ግቦች ጨምሮ የሊቨርፑሉ ሉዊስ ሱዋሬዝ 17 ግቦችን በማስቆጠር አሁንም ኮከብ የግብ አዳኝነቱን አስመስክሯል። የማንቸስተር ሲቲው ሰርጂዮ አጉዌሮ በ13 ግቦች እየተከተለው ይገኛል። ሌላኛው የሊቨርፑል ኮከብ ዳንኤል ስቱሪጅ 8 ግቦችን ይዞ ይከተላል።

ኮከብ ግብ አግቢዎችን ካነሳን አይቀር የጀርመኑን ቡድንደስ ሊጋ የቦሩሲያ ዶርትሙንዱ ሮበርት ሌቫንዶቭስኪ በ11 ግቦች እየመራ ይገኛል። የባየር ሙንሽኑ ማሪዮ ማንቹኪ እና የሔርታ ቤርሊኑ አድሪያን ራሞስ እያንዳንዳቸው 10 ግቦችን በማስቆጠር ይከተሉታል።

የደረጃ ሰንጠረዡን ባየር ሙንሽን በ44 ነጥቦች በመምራት ላይ ይገኛል። ባየር ሌቨርኩሰን በ37 ነጥቦች ይከተላል። ቦሩሲያ ዶርትሙንድ 32 ነጥቦችን ይዞ በግብ ክፍያ ልዩነት ሆኖም በነጥብ እኩል የሆነውን ሞንሽን ግላድባህን ከስሩ አድርጎ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል። በቡንደስ ሊጋው ያለፉትን አስር ጨዋታዎች ማሸነፍ የተሳነው አይንትራኽት ፍራንክፉርት ኃያሉ ባየር ሌቨርኩሰንን 1 ለባዶ ጉድ አድርጎታል። ብቸኛዋን ግብ ማርኮ ሩስ በ61ኛው ደቂቃ ላይ በባየር ሌቨርኩሰን መረብ ላይ አሳርፏል። ትናንት ሻልካ በኒኮላስ ሆፍለር እና ጄፈርሰን ፋርፋን ግቦች ፍራይቡርግን 2 ለ ባዶ ረቷል።

ቡንደስ ሊጋውን በበላይነት የሚመሩትን ቡድኖች ጨምሮ የጀርመን ቡድኖች በሻንፒዮንስ ሊጉ ከእነማን ጋር እንደሚገጥሙ ዛሬ ይፋ ሆኗል። ያለፈውን የአውሮጳ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ለመጨበጥ የቻለው የጀርመኑ ባየር ሙንሽን የእንግሊዙን ፕሬሚየር ሊግ ከሚመራው አርሰናል ጋር እንደሚገጥም ታውቋል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን እና የባየር ሙንሽን ተሰላፊው ፊሊፕ ላም ቡድኑ ከአርሰናል ጋር መገናኘቱን አስመልክቶ የተሰማውን ሲገልፅ እንዲህ ነበር ያለው።

ፊሊፕ ላም
ፊሊፕ ላምምስል Getty Images

«ከእዚህ ቀደም በምድባችን ማንቸስተር ሲቲ ከተደለደለ በኋላ አሁን ያለምንም ጥርጥርየሚጠብቀን ከባድ ፈተና ነው። በእርግጥ ከቀድሞ ወዳጆች ማለትም ከጀርመን ብሔራዊ ቡድን አባላት ጓደኞቻችን ጋር መገናኘቱ ደስ ይላል። ያ ምንጊዜም አስደሳች ነው። ከእዚያ ባሻገር ግን ከባድ ግጥሚያ ነው የሚጠብቀን። እርግጥ ነው፤ ባለፈው ዓመት ከአርሰናል ጋር ተጋጥመን ስለቡድኑ በደንብ አውቀናል። ያም ሆኖ በእዚህ የውድድር ዘመን አርሰናሎች ጠንካራ ሆነው በመውጣት የበለጠ መሻሻል አሳይተዋል። ያንን የፕሪሚየር ሊጉ ያሳይል። እና ቀላል ስራ አይደለም።»

በእዚህ የባየርን ሙንሽን እና አርሰናል ግጥሚያ የአርሰናሎቹ ጀርመናውያኑ ሜሱት ኦዚል፣ ሉቃስ ፖዶልስኪ እና ፔር ሜርቴሳከር የሚፋለሙት የሀገራቸው ልጆች ያሉበትን ሙንሽንን ድል ለማድረግ ነው። ጨዋታው በጀርመን ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም የሚጠበቅ ነው። ሌላኛው የጀርመን ቡድን ሻልካ ከስፔኑ ኃያል ሪኢል ማድሪድ ጋር ነው የሚገጥመው። ከማድሪድ ጋር እንደሚገናኙ ዛሬ ይፋ ሲሆን፤ የሻልካው አሰልጣኝ የንስ ኬለር እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።

«ተጋጣሚዎቹ በአጠቃላይ አደገኞች ናቸው። ግን ከተጋጣሚዎቹ ሁሉ ድንቅ ተጋጣሚ፣ ኃያል ቡድን እና በዓለማችን ከፍተኛ ስኬት ካስመዘገቡ ቡድኖች መካከል ዋነኛው ከሆነው ሪያል ጋር መገናኘት ለእኛ እጅግ ደስ የሚል ነው። እናም ከእዚህ ቡድን ጋር መጋጠም ለደጋፊዎቻችንም ቢሆን በጣም አስደሳች ነው።»

ክርስቲያኖ ሮናልዶ
ክርስቲያኖ ሮናልዶምስል Denis Doyle/Getty Images

በሻምፒዮንስ ሊጉ ድልድል የአራት ጊዜ የአውሮጳ ባለድሉ የስፔኑ ባርሴሎና ከእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ ጋር እንደሚገጥምም ታውቋል። የእንግሊዙ ማንቸስተር ዩናይትድ ከግሪኩ ባለድል ኦሎምፒያኮስ፣ የሰባት ጊዜ የጣሊያን አሸናፊው አስ ሚላን ከአትሌቲኮ ማድሪድ፤ የጀርመኑ ባየር ሌቨርኩሰን ከፈረንሳዩ ፓሪስ ሴይንት ጀርሜይን፣ ቸልሲ ከቱርኩ ጋላታሳራይ ጋር ይገጥማሉ። ድልድሉ ስዊዘርላንድ ኒዮን ውስጥ ነው ዛሬ ይፋ የሆነው። ጨዋታዎቹ በአጠቃላይ ከሁለት ወራት ገደማ በኋላ ነው የሚጀምሩት።

አሁን የስፔን ላሊጋ እና የጣሊያን ሴሪ ኣ የእግር ኳስ ውጤቶችን አጠር አድርገን ለመዳሰስ እንሞክራለን። በስፔን ላሊጋ ትናንት አትሌቲኮ ማድሪድ ቫሌንሺያን 3 ለባዶ አሸንፏል። ሪኢል ሶሲዳድ ሪያል ቤቲስን 5 ለ1 ረቷል። ሴቪላ ከአትሌቲክ ክለብ አንድ እኩል እንዲሁም አልሜሪያ ከኤስፓኞላ ባዶ ለባዶ አቻ ወጥተዋል።

የደረጃ ሠንጠረዡን ባርሴሎና በ43 ነጥብ ይመራል። አትሌቲኮ ማድሪድ በግብ ክፍያ ልዩነት ብቻ ይከተላል። ሪያል ማድሪድ በ38 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ እና የአትሌቲኮ ማድሪዱ ዲዬጎ ኮስታ እያንዳንዳቸው 17 ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ለመጨረስ እየተፎካከሩ ነው። የሪያል ሶሴዳዱ ግሪስማን በ10 ግቦች ይከተላቸዋል።

ጁቬንቱስ ቱሪን ካሊጋሪ
ጁቬንቱስ ቱሪን ካሊጋሪምስል picture-alliance/dpa

በጣሊያን ሴሪ ኣ ናፖሊ ኢንተር ሚላንን በአስደናቂ ሁናቴ 4 ለ2 በመምራቱ ከ13 ዓመታት በኋላ ዋንጫ ለመብላት ተስፋው እየለመለመ ነው። ትናንት ጁቬንቱስ ሳሱሎን 4 ለባዶ ሸኝቷል። ፊዮሬንቲና ቦሎኛን 3 ለባዶ አሸንፏል። ሆኖም በደረጃ ሠንጠረዡ 30 ነጥብ ይዞ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ናፖሊ በ35 ነጥብ ሶስተኛ፣ ሮማ ሁለት ነጥብ ከፍ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ይዟል። ጁቬንቱስ 43 ነጥቦችን ሰብስቦ በቀዳሚነት በመገስገስ ላይ ይገኛል። ሴሪ ኣውን በ13 ከመረብ ያረፉ ግቦች የሚመራው የፊዮረንቲናው ጁሴፔ ሮሲ ነው። የጁቬንቱሱ ካርሎስ ታቬዝ በ10 ግቦች ይከተላል።

ትናት ምሽት የጀርመን ስፖርት ሽልማት ስነስርዓት ሲካሄድ ከቡድኖች ዘንድሮ እስካሁን ድረስ ሽንፈት ያልገጠመው ባየር ሙንሽን ተሸላሚ ሆኖዋል። በአትሌቲክሱ ዘርፍ ደግሞ ክሪስቲና ኦበርግፎየል እና ሮበርት ሐርቲንግ ለመሸለም በቅተዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ