1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከ 7 ሚሊዮን በላይ የመናዉያን ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል።

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 16 2009

ካለፉት ሁለት አመታት ወዲህ በጦርነት የምትታመሰዉ  ደቡብ አረባዊቷ ሀገር የመን በጦርነት ሳቢያ ከሚደርሰዉ እልቂት ባሻገር  ረሀብና የኮሌራ በሽታም  የከፋ ሰብዓዊ ቀዉስ እያስከተለ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታዉ ምክር ቤት አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/2ibd1
Jemen Cholera
ምስል Reuters/A.Zeyad

Man-Made Catastrophe Escalating in Yemen - MP3-Stereo

 

 የየመን ሰብአዊ ቀዉስ በሀገሪቱ በሚካሄደዉ ጦርነት ሳቢያ የተከሰተ« ሰዉ ሰራሽ»  ችግር በመሆኑ  ግጭቱን ለማስቆም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ግፊት እንድያደርግ  ድርጅቱ አሳስቧል።

የድርጅቱ የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ስቴፈን  ብሪያን  የየመንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ሰሞኑን በዩኤስ አሜሪካ ኒዮርክ  ለምክር ቤቱ  እንዳስታወቁት፤  በሀገሪቱ  ወደ 7 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለከፋ  ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል። 
ከረሀብ አደጋዉ በተጨማሪም  በኮሌራ በሽታ የሚሰቃዩ የመናዉያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቶ አሳሳቢ ደረጃ ለይ መድረሱን  ድርጅቱ አመልክቷል።በየመን  16 ሚሊዮን ሰወች የዉሃ አቅርቦት የማያገኙ ሲሆን 17 ሚሊዮን ሰወች ደግሞ የሚቀጥለዉን  ምግባቸዉን መቼና እንዴት እንደሚያገኙ እርግጠኞች አይደሉም  ተብሏል። ጭካኔ የተሞላበት ግጭትና የፍትህ መጓደልም ለየመናዉያኑ ተጨማሪ የዕለት ተዕለት ፈተናወች ናቸዉ ሲሉ ስቴፋን ብርያን ያብራራሉ።
«ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የመናዉያን ተደራራቢ ስቃይ ተደቅኖባቸዋል።እነርሱም የረሀብ አደጋ ስጋት ፣በአለም በስፋቱ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የኮሌራ ወረርሽኝ፣በየቀኑ የሚያጋጥም የነጻነት እጦትና ጭካኔ የተሞላበት ግጭት እንዲሁም ኢፍትሃዊነት ናቸዉ።»
እንደ ሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪዉ ገለፃ ባለፉት ሁለት አመታት  ችግሩን ለመፍታት በድርጅቱ በኩል  የተደረጉ አንዳንድ  ጥረቶች ቢኖሩም በሳዉዲ ጥምር ጦር በሚደገፈዉ በሀገሪቱ መንግስትና  በኢራን በሚደገፉት የሁቲ ዓማፅያን መካከል በሚካሄደዉ ጦርነት  ሳቢያ   በሀገሪቱ የሚታየዉ  ችግር እየጨመረ መጥቷል። በጎርጎሮሳዊዉ  2017 በአንድ ወር ብቻ በሀገሪቱ የተፈጸመዉ  የአየር ጥቃት በ2016 አመቱን ሙሉ ከተካሄደዉ 3 እጥፍ የሚልቅ ሆኖ ተገኝቷል። በያዝነዉ ወር መጀመሪያ ብቻ በጥቃቱ 6 ህፃናትን ጨምሮ 12 ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል።በጦር መሳሪያ በተደረጉ ግጭቶችም በ2017 በአንድ ወር ብቻ የተካሄደዉ ከ2016 ጋር ሲነጻጸር 50 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ግጭቱ እየተባባሰ መምጣቱን ማሳያ ነዉ ተብሏል።ስቴፋን በጉዳዩ ላይ ለዉጥ አለመታየቱ አሳዛኝ ነዉ ይላሉ።
«ባለፉት ሁለት አመታት በየመን በሚታየዉ የከፋ ሰብዓዊ ጉዳት በጥልቅ አዝኛለሁ።እኔና የእኔ ቡድን አባላት ከፍተኛ ጥረት ብናደርግም በዚህ ሊወገድና ሊሻሻል በሚችል አሳዛኝ ሰዉ ሰራሽ ቀዉስ ላይ የረባ ዉጤትን የሚያሳይ ዘገባ ማቅረብ አልቻልንም።ያ ሀገሪቱን እያወደመ ነዉ።» 
እንደ አለም አቀፉ የጤና ድርጅት ከጦርነቱና ከረሀቡ በተጨማሪ ጊዜ በማይሰጥ የኮሌራ ወረርሽኝ   በአማካኝ 5000 የመናዉያን በተለይም ነብሰጡር ሴቶችና የሚያጠቡ እናቶች በየ ቀኑ ይያዛሉ።ያም ሆኖ ግን 55 በመቶ የሚሆኑት የየመን የህክምና መስጫ ተቋማት በጦርነቱ ከጥቅም ዉጭ በመሆናቸዉ ተገቢ ህክምና መስጠት አስቸጋሪ ሆኗል።በቀሪወቹ  የጤና ማዕከላት የሚሰሩ ወደ 1 ነጥብ 2የሚጠጉ  የጤና ባለሙያወች፣ መምህራንና ሌሎች የመንግስት ሰራተኞች ካለፈዉ ታህሳስ ጀምሮ ወርሃዊ ክፍያቸዉ በመቋረጡ ስራቸዉን በተገቢዉ ሂኔታ ማከናወን እንዳልቻሉ ድርጅቱ ገልጿል።ያም ሆኖ ግን እስካሁን ችግሩን የሚያቃልል  እርዳታ አልተገኘም ተብሏል።
በየመን እየተባባሰ የመጣዉን  ሰብዓዊ ቀዉስ መከላከል ብሎም ማስወገድ የሚቻል ሰዉ ሰራሽ ችግር ቢሆንም   ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  በቂ ምላሽ ባለመስጠቱ  አሁንም ድረስ በሚሊዮን  የሚቆጠሩ የመናዉያን  ያለመፍትሄ የሰቆቃ ህይወት እንዲገፉ መደረጉ አሳዛኝና አሳፋሪ ነዉ ሲሉም ስቴፋን  ይተቻሉ። 
«ለሁላችሁም፤  በተለይም ለፀጥታዉ ምክር ቤት በቀጥታ የምገልፀዉ ሁኔታዉ ምን ያህል ሊያሳፍረን እንደሚገባ ነዉ።በተፋላሚወቹ መካከል ያለዉን ጦርነቱን በማስቆም የእያንዳንዱ የመናዊ ፍላጎትና ህጋዊ ተስፋወች እንዲሟሉለት ማድረግ ይገባ ነበር።ያ ባለመሆኑ  ድክመታችንን  መቀበል አለብን። »
የየመን ቀዉስ የፓሊሲወች ስልቶችና ድርጊቶች ቀጥተኛ ዉጤት ነዉ የሚሉት አስተባባሪዉ ላለፉት  ሁለት አመታት የዘለቀዉን ግጭት  የሚያስቆም ፓለቲካዊ መፍትሄ እንዲመጣ  ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊት  ማድረግ አለበት ሲሉ  አስምረዉበታል።
በተባበሩት መንግስታት የየመን አደራዳሪ እስማኤል ኡልድ ሸክሀሚድ ደግሞ   ከረሀቡ ፣ከበሽታዉና ከጦርነቱ ሌላ  ሀገሪቱ አራተኛ ፈተና ይገጥማታል ባይ ናቸዉ።አልቃይዳንና አረቢያን ፔኑሱላ የመሳሰሉ  አሸባሪ ድርጅቶች  መፈንጫ የመሆን።
ከሁለት አመታት በላይ የዘለቀዉ የየመን የርስበርስ ጦርነት  በርካታ ሰብዓዊ ቀዉሶችን ከማስከተሉ  በላይ እስካሁን ከ12 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት ዳርጓል።

Jemen Milizen entfernen Landminen platziert von Houthi-Rebellen
ምስል picture-alliance/dpa/STR

ፀሐይ ጫኔ

ነጋሽ መሀመድ