1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ረሃብን በስኳር ድንች መቋቋም

ረቡዕ፣ ሐምሌ 28 2002

በኬንያ፣ ናኩሩ ከተማ አቅራቢያ እንጆሮ ውስጥ በሚገኘው ኤገርተን ዩኒቨርስቲ ጠቃሚ ንግግር የሚያሰሙና ተማራማሪ፤ ናቸው።

https://p.dw.com/p/Oc66
ምስል Sascha Quaiser

ዋና ዓላማቸው ግብርናንና ጤንነትን በማጣመር፤ በትውልድ አገራቸው በኬንያ ብሎም በአፍሪቃ ረሃብ እንዲወገድ ማብቃት ነው። በምግብ ሥነ ቴክኒክ የተመረቁት ሜሪ አንያንጎ ኦዩንጋ፣ ምርምራቸው በድንች በተለይም በስኳር ድንች ላይ ነው ያተኮረው።

በአገር በቀል ተክሎች ላይ በተለይም በስኳር ድንች ላይ ምርምራቸውን ያጠናቀሩት ኦዩንጋ፣ ሙያቸውን ከወንጌሉ ቃል ጋር አሰባጥረው፤ «እግዚአብሔር ለአፍሪቃውያን ሁሉ የዕለት እንጀራ (ዳቦ) አይሰጥ ይሆናል፤ ነገር ግን፤ በርካሽ ዋጋ የሚገኝ ከዳቦ የላቀና አልሚ የሆነ ምግብ አዘጋጅቶላቸዋል። እርሱም ውስጡ የሚገመጠውን ብርቱካን የሚመስለው ስኳር ድንች ነው» ። የሜሪ አንያንጎ ኦዩንጋ ምርምር ለልዩው ምርጥ ጣፋጭ ድንች መከሠት አስተዋጽዓ ማድረጉ ነው የተገለጠው። ውጤት በማስመዝገባቸውም፤ የአፍሪቃ ሴቶች የግብርና ምርምርና ልማት መርኀ-ግብር እውቅና በመስጠት በቅርቡ የሁለት ዓመት ነጻ የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ዕድል እንዲያገኙ አድርጓል። ኬንያ ውስጥ፣ በግብርናው ዘርፍ ይህን ዕድል ካገኙት 4 ሴቶች መካከል ኦዩንጋ አንደኛዋ ናቸው። እርሳቸውና 3 ባልደረቦቻቸው ባጠቃላይ ኬንያ ውስጥ በግብርና ዘርፍ ከተሠማሩት ተማራማሪዎች መካከል 20 ከመቶውን የሚወክሉ ናቸው። በኬንያ ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ፤ 80 ከመቶውን የግብርና ሙያ የሚያከናውኑ ሴቶች መሆናቸው የታመነ ነው። የሜሪ አንያንጎ ኦዩንጋ የምርምር ውጤት አምና በበአፍሪቃ የምግብ፤ ግብርና አመጋገብና ልማት በተሰኘው መጽሔት ታትሞ የወጣ ሲሆን ፤ እንደምርምሩ ጠቃሚነት ሁሉ፤ የምርምሩን ውጤት በተግባር ማሳየቱም ሆነ ማከናወኑ ደገሞ የበለጠ ፋይዳ አለው ባይ ናቸው። በመሆኑም ኦዩንጎ፤ ኪሱሙ ከተማ አቅራቢያ፤ ሴቶችን በማስተማር ነው አብዛኛውን ጊዜአቸውን የሚያጠፉት። ድንች የሚተክሉ ኬንያውያት ፤ ስለድንች ምግብነት የማያውቁ ሆነው ሳይሆን፤ ከተማራማሪዋ የሚሰጣቸው ጠቃሚ ማብራሪያ፣ በድንቹ ውስጥ ስለሚገኙ ቪታሚኖችና ይህም ለጤንነት የቱን ያህል የሚበጅ መሆኑን ነው። ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ የአፍሪቃ አገሮች ፤ ዕድሜአቸው ከ 5 ዓመት በታች የሆነ 43 ሚሊዮን ህጻናት፤ የቪታሚን «A» እጥረት ያሠጋቸዋል። ተመራማሪዋ ሜሪ አንያንጎ ኦዩንጋ እንደገለጹት፤ 125 ግራም ብቻ ከሚመዝን ስኳር ድንች ለዕለት የሚያስፈልገውን ቪታሚን «A» ማግኘት ይቻላል።

የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት (WHO) እንደሚያስረዳው፤ የቪታሚን «A» ጉድለት፣ በአመዛኙ፤ ልጆች ዐይነ ብርሃናቸውን እንዲያጡ ሊያደርግ የሚችል ከመሆኑም በላይ፤ እንደ ተቅማጥ ፤ ኩፍኝ፤ በመሳሰሉት አደገኛ በሽታዎች እስከሞት ሊያደርስ ይችላል።

ነፍሰ- ጡሮች የቪታሚን «A » ጉድለት ሲያጋጥማቸው በጨለማ ትንሽ ጭላንጭል እንኳ ያለማየት ሳንክ ሊያጋጥማቸው ይችላል። አስከፊም ሲሆን የእናቶችን ህይወት ያሳጥራል። የኬንያ የግብርና ምርምር ተቋም ባልደረባ፤ ኦዩንጋ፤ በምዕራብ ኬንያ፤ ስኳር ድንች፤ በተለይም ለጤንነት የላቀ አስተዋጽዖ ያደርጋል ተብሎ በጥናት የተደረሰበት ልዩ ጣፋጭ ድንች እጅግ እንዲስፋፋ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። ከምርምራቸው ጋር በተያያዘ፤ በአንድ ፕሮጀክት የታቀፉና በመንግሥት የጤና ጥበቃ ማዕከላት ክብካቤ የሚደረግላቸው ነፍሰ-ጡሮች በመላ፤ በሚሰጣቸው ልዩ ካርድ፤ ወደ ማንኛውም የስኳር ድንች ችግኝ አፍዪ አትክልተኛ ጣቢያ በመሄድ 120 ችግኝ በነጻ ይቀበላሉ። ይህ አሠራር፤ በምዕራብ ኬንያ ከተሣካ፤ አፍሪቃ ውስጥ ከሰሃራ በስተደቡብ በሚገኙ አገሮች ሁሉ እንዲሠራበት መደረጉ አይቀርም ነው የሚባለው።

ኦዩንጋ እንዳስረዱት፣ ልዩው ስኳር ድንች እንደ ዳቦም ሆነ ቻፓቲ(የህንዶች ቂጣ)ወዲያው ሲመገቡት በሰውነት ውስጥ ብዙ የኃይል መጠን(ካሎሪ)አይገኝበትም። ስለዚህ ፣ ከመጠን በላይ ክብደት ላለመጨመር ለሚጠነቀቁ ተስማሚ ነው። 100 ግራም የተቀቀለ፤ ውስጡ ብርቱካን የሚመስል ስኳር ድንች፣ 85 ካሎሪ ፤ ነጭ ዳቦ 220፤ ቻፓቲ (ቂጣ )ደግሞ 300 ካሎሪ እንዳለውም ኦዩንጋ አስረድተዋል።

«የአንድ ሰው የምርምር ውጤት፤ በተግባር ተተርጉሞ፤ በተለይ፤ የገጠሩን ድሃ ዜጋ ከጠቀመ፤ የፕሮጀክቱ አራማጅ፤ ህዝብን ከድህነት ዓለም ፣ ወደ ኤኮኖሚ ልማት እንዳሸጋገረ ድልድይ መሆኑ ስለሚሰማው ፤ እጅግ የሚያረካ የሥራ ክንውን ነው» ማለት ይቻላል።

የአፍሪቃ አረንጓዴ አብዮት አጋር ወይም ተጓዳኝ የሆነው ድርጅት

ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር አኪንውሚ አደሲና ፤«ሳይንቲስቶች

የአፍሪቃን የምግብ እጥረት ማስወገድ ወደሚቻልበት ብልሃት እየተጠጉ የመጡ ሲሆን፤ በሳይንሱ ማኅበረሰባችን ውስጥ ያለውን የጾት ልዩነት ችግር ባስቸኳይ ማስወገድ ይገባናል። በግብርና ሳይንስ ብዙዎች ሴቶች ተማራማሪዎች ያስፈልጉናል። ምክንያቱም፤ የአፍሪቃ የግብርና ገጽ ሴቶች ናቸውና!»ብለዋል። ኦዩንጋ ፤አፍሪቃ ውስጥ፤ በከፍተኛ ደረጃ ፣ በግብርና ምርምር ከሚያደርጉት 180 ሴት ሳይንቲስቶች መካከል አንዷ ናቸው።

ባለፈው ሰኔ ወር Action Aid International የተሰኘው ድርጅት ያቀረበው ዘገባ፤ አነስተኛ ይዞታዎች ያሏቸው አርሶ አዳሮች፤-- ብዙኀኑ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል፤--፣በአፍሪቃ ግብርና፣ 90 ከመቶውን የሚያመርቱት ሴቶች ናቸው ፤ ይህም ፤ ከዓለም የምግብ አቅርቦት ግማሽ ገደማ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው ይላል። ያም ሆኖ፤ ሴቶች ሳይንቲስቶች ያን ያህል በግብርና አይመራመሩም፤ ወይም በዚያ መስክ የመሪነቱ ቦታ የላቸውም። በዓለም አቀፍ የግብርና ምርምር ፤ የምክክር ቡድን ፤ የጾታ የመርኀ-ግብር ክፍፍል ዋና ሥራ አስኪያጅና የአፍሪቃ ሴቶች፣ የግብርና ምርምር እንዲሁም የልማት መርኀ-ግብር (AWARD) መሥራች ፤ ቪኪ ዋይልድ፤ አሁን የለውጥ ጊዜ ነው ባይ ናቸው።

እንደ ቪኪ ዋይልድ አገላለጽ፣ «የአፍሪቃን ሴቶች ማስተማር ፤ ብልህነትን የሚያንጸባርቅ እርምጃ መውሰድ ማለት ነው። ለአፍሪቃውያት ሳይንቲስቶች ሁኔታዎችን ማመቻቸት ደግሞ እጅግ የላቀና ዋጋ ያለው እርምጃ ነው።»

የኬንያ የግብርና ምርምር ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ዶ/ር ኤፍሬም ሙኪሲራ እንዳስገነዘቡት፤ «በአፍሪቃ ድኅነትን ማስወገጃው መላ፤ እኽል በማምረትም ሆነ ፣ የሚላስ የሚቀመስ እንዲገኝ በማድረግ ረገድ፤ ጠቃሚ ሚና ያላቸውን ፤ ሴቶችን፤ በየዘርፉ ለሥልጣን ማብቃት ነው»።

ስኳር ድንች፣ ብዙ ውሃ የሚያሻው ተክል አይደለም፤አፍሪቃውያት ሳይንቲስቶች የግብርናውን ምርምር ሲያካሂዱ ለግብርና አመቺና ጠንቅ የሆኑትንም ግምት ውስጥ በማስገባትበጥብቅ ማሰባቸው የማይቀር ነው። የዓለም የአየር ጠባይ መዛባት፤ በተለይ ድርቅ የተጋረጠባት አፍሪቃ ፤ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ የሚጠበቅበት ይሆናል። በዚህ ነጥብ፤ ላይ በቅርቡ፤ የጋና የትምህርትና የተፈጥሮ አካባቢ ሚንስትር ወ/ሮ አይተዪ እንዲህ ብለው ነበር።

«የምዕራብ አፍሪቃ አገሮችን ብንመለከት ከጊኒ ቢሳዎ እስከ ካሜሩን ፤ ሁላችንም ተመሳሳይ የአየር ንብረት ነው ያለን። ዝናም የሚጥልበት የአካባቢ መሥመር፤ ጠባብ ነው። ይህም ፤ ደን እየተመናመነ፤ የሰሃራ ምድረ በዳ ከሰሜን ወደ ደቡብ እየሰፋ በመምጣቱ የተከሠረ ነው። የድርቅ ወራትም እየተራዘሙ ናቸው። የውሃ እጥረት ፤ የኃይል ምንጭ እጥረት አለ። የአየር ንብረት መዛባት፤ ወሰን የማይገታው ችግር አስከትሎብናል።»

በሰሜን ናይጀሪያ፣ የፉላኒ ብሔር ወገን የሆኑት ሙስሊሚቱ ተመራማሪ አይሻቱ በሺር አርዶ፤ በሳይንሳዊ ጥበብ ከብቶች እንዲራቡ የሚያደርጉ ሲሆን፤ ተማራማሪይቱ፤ በተለምዶ የወንዶች ተግባር ብቻ ነው ይባል የነበረውን ሙያ ሠልጥንውበት ፤ ለሌሎች ተማራማሪ ናይጀሪያውያንም ሆኑ ሌሎች አፍሪቃውያን እህቶቻቸው ጥሩ አርአያ መሆናቸውን ማሳየታቸው አልቀረም።

በአፍሪቃ፣ ሁኔታዎች ቀስ በቀስ እየተለወጡ፤ ለሴቶች እኩል የትምህርት በር እንዲከፈት የሚያመቻቹ ሁኔታዎች መከሠታቸውን እየጠቆሙ ነው። ለ 8 ዓመታት ክትትል የተደረገበት ጥናት ከ2 ዓመት በፊት እንደጠቆመው ከሆነ፣ በግብርና ሳይንስ የተቀጠሩ ሴቶች ሙያተኞች ቁጥር 8 ከመቶ አድጓል። የኬንያ የግብርና ምርምር ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ ፤ ዶ/ር ኤፍሬም ሙኪሲራ፤ ሴቶች እህል በማምረት ብቻ ሳይሆን ቤተሰቡ የሚመገበውን በማቅረብ፣ ምንጊዜም ማዕከላዊ ሚና ተጫውተዋል። ስለሆነም ኅብረተሰቡ ምን እንደሚበጀው ጠንቅቀው ያውቃሉና በግብርናው መስክ የሚመራመሩት ሴቶች ቁጥር፣ ሊጨምር ይገባዋል፣ ነው ያሉት።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ