1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሩሲያና «የተባበረች ሩሲያ« የተሰኘው አስተዳዳሪ ፓርቲ፧

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 8 2000
https://p.dw.com/p/E87I
ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲንና የወደፊቱ ተተኪያቸው ሳይሆኑ አይቀሩም የተባሉት፧ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፧
ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲንና የወደፊቱ ተተኪያቸው ሳይሆኑ አይቀሩም የተባሉት፧ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ፧ምስል AP
የካቲት 23 ቀን 2000 ዓ ም፧ አዲስ የፕሬዚዳንት ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ በሥልጣን ላይ የሚቆዩት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን፧ ለምርጫ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው የሚቀርቡት የእርሳቸው ምልምል፧ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ከተመረጡ፧ ፑቲን የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ቦታ ለመያዝ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን በይፋ አስታውቀዋል። «የተባበረችው ሩሲያ« የተሰኘው የፑቲን ፓርቲ፧ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ሜድቬዴቭ፧ የካቲት 23 ቀን ለሚካሄደው ምርጫ እጩ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲቀርቡ የወሰነው፧ ትናንት ነው። የዶቸ ቨለ ባልደረባ እስቴፋን ላክ ባቀረበው ዘገባ ላይ እንዳለው፧ ወደፊት ሩሲያ፧ በሜድቬዴብና ፑቲን ጥምረት የምትተዳደር አገር እንደምትሆን ሳይታለም የተፈታ ነው።......ተክሌ የኋላ.....
«የተባበረች ሩሲያ« የተሰኘው የሩሲያ አስተዳዳሪ ፓርቲ ባካሄደው ጉባዔ፧ የጉባዔው አዳራሽ፧ በአገሪቱ ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ፧ ነጭ፧ ሰማያዊና ቀይ ቀለማት አሸብርቆ ልዑካኑም በበዓላት በሚለበስ ልብስ አሸብርቀው በመገኘታቸው፧ ለዐቢይ ግብዣ የተሰበሰቡ እንጂ የፓርቲ እጩዎችን ለማስተዋወቅ ዝግጅት የተደረገበት መደበኛ ጉባዔ አልመሰለም። የካቲት 23 ቀን 2000 ዓ ም በሚካሄደው ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ የታጩት ድሚትሪ ሜድቬዴቭ፧ በጉባዔተኞቹ፧ ከሞላ ጎደል መቶ በመቶ ነው የድጋፍ ድምጽ ያገኙት።
በዚህ የፓርቲው ስብሰባ፧ ትልቅ ትርጉም የተሰጠው፧ የፕሬዚዳንት ፑቲን አቋም ነው። ፑቲን፧ ወደፊት በጠቅላይ ሚንስትርነት ለማገልገል ፈቃደኛነታቸውን ይግለጡ እንጂ ጉዳዩን ከቅድመ-ግዴታ ጋር ነው አያይዘው ያቀረቡት።
«የሩሲያ ዜጎች፧ በሜድቬዴቭ ላይ እምነታቸውን ጥለው፧ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ከመረጧቸው፧ እኔም፧ የሩሲያ ፌደሬሽን ጠቅላይ ሚንስትር በመሆን፧ የጋራ ተግባራችን እንዲቀጥል ለማድረግ ዝግጁ ሆኜ እቀርባለሁ።«
ፑቲን፧ የሥልጣን ክፍፍልን በተመለከተ፧ አንዳች ለውጥ እንደማይደረግ ነው የገለጡት። ሜድቬዴቭ፧ ስለፑቲን የወደፊት ድርሻ ባለፈው ማክሰኞ ያቀረቡትን ሐሳብ፧ ራሳቸው ፑቲን ምላሽ የሰጡበት ዘግየት ብለው ነው። ስለሩሲያ የአመራር ዘይቤ፧ የፑቲን የወደፊት ድርሻ ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው የአንክሮ ጥያቄ ምላሽ ያገኘው በእንዲህ ሁኔታ ነበር።
«ለፓርቲው ጉባዔ፧ ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ እጩ ፕሬዚዳንት ይሆኑ ዘንድ ሐሳብ አቀርባለሁ። ፍጹም ሐቀኛና ጨዋ ሰው ናቸው። ቀላእ ባልነበሩ፧ በብዙ ወሳኝነት ባላቸው የሥራ ዘርፎች ተሠማርተው አልግለዋል። የዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ተቀዳሚ ዓላማዎች፧ የመንግሥትና የዜጎች ጥቅሞች መሆናቸውን፧ በሙሉ ኀላፊነት እናገራለሁ።«
ፕሬዚዳንት ፑቲን፧ የመንግሥት ታማኝ ለሆኑት ለሜድቬዴቭ ያላቸውን በጎ አመለካከት በእንዲህ መልኩ ነው የገለጡት። ከፑቲን ጋር ረዘም ላለ ጊዜ ማለትም አሥራ ሰባት ዓመት ያህል አብረው የሠሩት ሜድቬዴቭ፧ የስለላው ድርጅት አባል የነበሩ አይደሉም። ሁለቱም፧ በሴንት ፒተርስበርግ ከተማ አስተዳደር ውስጥ አብረው ሠርተዋል። በመጨረሻ፧ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣን፧ በውስጣዊ ጉዳዮች፧ በተለይ በትምህርት፧ በማህበራዊ ኑሮና በግብርና ዘርፍ ኀላፊነት ተቀብለው ሠርተዋል። በምዕራቡ ዓለም የ«ጋዝፕሮም« ተቆጣጣሪ ምክር ቤት ሊቀመንበርነታቸው ነው የሚታወቁት። ሜድቬዴቭ፧ ፑቲን፧ የቀረበላቸውን ሐሳብ ከተቀበሉ በኋላ እፎይታ ተሰምቷቸው ሲናገሩ፧......
«ቭላዲሚር ፑቲን፧ የቀረበላቸውን ሐሳብ በመቀበላቸው በእርግጥ ደስ ብሎኛል። በአንድ ቡድን በመሰለፍ፧ በፓርላማ፧ የብዙኀን እንደራሴዎችን ድጋፍ በማግኘት፧ በአዲሱ መንግሥት፧ ውስብስብ ያሉ ከፍተኛ ኀላፊነትን የሚጠይቁ ተግባሮችን መፈጸምና መፍትኄዎቻቸውንም ማግኘት እንችላለን።«
ዲሚትሪ ሜድቬቭ፧ በመጪው ምርጫ ማሸነፋቸው የማይቀር ነው። በቅርብ የተካሄደ የህዝብ አስተያየት መመዘኛ መጠይቅ እንደሚጠቁመው፧ ብዙኀኑ መራጮች፧ የፑቲንን ሐሳብ የሚደግፉ ናቸው። ፑቲን፧ ለሜድቬዴቭ መመረጥ ሽንጣቸውን ገትረው እንደሚታገሉ የሚያጠራጥር አይሆንም። የራሳቸውም የወደፊት ዕጣ ከዚሁ ጋር የተቆራኘ ነውና! የወደፊቱ የሩሲያ ፖለቲካ፧ የፑቲን መርኅ እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው። ጥያቄው፧ ጭምቱና ለዘብተኛው ሜድቬዴቭ፧ በፕሬዚዳንትነት ተሰሚነታቸው እንዲጎላ ማድረግ የሚችሉ ናቸው ወይ? የሚለው ነው። የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር፧ ፍራንክ ቫልተር እሽታይንማየር፧ በዛሬው ዕለት፧ ሞስኮ ውስጥ፧ ከሜድቬዴቭ ጋር ተገናኝተው የሚነጋገሩ ሲሆን፧ እሽታይንማየር የእኒሁን ሩሲያዊ እጩነት በደስታ ነው የተቀበሉት። ሜድቬዴቭ፧ ለኤኮኖሜ ዘመናዊ አያያዝ፧ የቆሙ ከምዕራቡም ጋር ማለፊያ ግንኙነት የሚሹ መሆናቸው ነው የሚነገርላቸው።