1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሩሲያ የአሮጌዉ ፕሬዝዳት አዲስ ፕሬዝዳትነትና ተቃዉሞዉ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 29 2004

ሚኻኤል ጎርቫቾቭ የለኮሱት የሩሲያ ሁለተኛ አብዮት ለፕሬዝዳትነት ያበቃቸዉ ቦሪስ የልትሲን አምነዉ ክሬምሊንን ሲያወርሷቸዉ ጎሮቫቾቭ ብቃታቸዉን ጠርጥረዉ ነበር።ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ሲያወድሷቸዉ፣ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉ ኮሊን ፓዌል ጠልተዉቸዉ ነበር።

https://p.dw.com/p/14rO7
Russian Prime Minister Vladimir Putin speaks at a congress of the United Russia party in St. Petersburg, Russia, Saturday, Nov. 21, 2009. United Russia is a power base for Putin, who has not ruled out a return to the presidency in 2012. (AP Photo/Dmitry Lovetsky)
ፑቲንምስል AP



07 05 12
 
                      
«የሩሲያ ፌደሬሽን ፕሬዝዳትን ሙሉ ሐላፊነት ገቢር ለማድረግ ቃል እገባለሁ።የሕዝቡን የዜጎችን መብትና ነፃነት ለማክበርና ለማስከበር፥ የሩሲያ ፌደሬሽንን ለማስጠበቅና ለመደገፍ፥ የሐገሪቱን ልዓላዊነት፥ ነፃነት፥ ደሕንነትና አንድነትን ለማስከበርና ዜጎችን በቅንነት ለማገልገል (ቃል እገባለሁ።)ቭላድሚር ቭላድሚሮቪች ፑቲን፥።በዉርስም፥ በምርጫም ብለዉ ከስምንት ዓመት በላይ የኖሩበትን የፕሬዝዳትነት ሥልጣን እንደገና ያዙ።ዛሬ።ተወገዙም።የአሮጌዉ ፕሬዝዳት-አዲስ ፕሬዝዳትነት መነሻ፥ ፖለቲካዊ ስብናቸዉ ማጣቀሻ፣ የሩሲያ እዉነታ መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።ሚኻኤል ጎርቫቾቭ የለኮሱት የሩሲያ ሁለተኛ አብዮት ለፕሬዝዳትነት ያበቃቸዉ ቦሪስ የልትሲን አምነዉ ክሬምሊንን ሲያወርሷቸዉ ጎሮቫቾቭ አብዮቱን ግብ የማድረስ ብቃታቸዉን ጠርጥረዉ አጠያይቀዉ ነበር።ፕሬዝዳንት ጆርጅ  ቡሽ ሲያደንቁ፥ ሲያወድሷቸዉ፣ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉ ኮሊን ፓዌል ጠልተዉ አናንቀዋቸዉ ነበር።ሩሲያን ከጥፋት፣ሁለተኛ አብዮቷን ከዉድቀት በማዳናቸዉ የመደነቃቸዉን ያክል በአምባገነንነት ይወገዛሉ።ቭላድሚር ፑቲን የተቃርኖ ዉሁድ።

የዛሬዉ የሩሲያ የመካከለኛ መደብ ሕብረተሰብ የደረጀዉ በሳቸዉ ዘመነ-ሥልጣን መሆኑ አላነጋገረም።ያ ሕብረተሰብ ግን ዋነኛ ተቃዋሚያቸዉ ነዉ።እሱ አንዱ ነዉ።
             
«ባለፈዉ መጋቢት አራት ማታ ፑቲን አደባባይ ወጥተዉ ባደረጉት ንግግር (በምርጫ) ማሸነፋቸዉ ማሸነፋቸዉን አስታዉቀዋል።ያዉቃሉ? ነገሩ እንዲሕ ነዉ።አዎ! እሳቸዉ በየትኛዉም መንገድ ለማግኘት የተፋለሙለትን ቁጥር ጦርነት በርግጥ አሸንፈዋል።እና እሳቸዉ የቁጥር ፕሬዝዳንት ናቸዉ።የሕዝቡ ፕሬዝዳት ግን አይደሉም።»

ማክሲም ቪቶርጋን።የፊልም ተዋኝ ነዉ።

አዲሱ «መንግሥት ምናልባት ሐገሪቱ ሥለምትለማበትና ሕዝቡ ሥለሚበለፅግበት መርሕ (ከተቃዋሚዎች ጋር) ገንቢ ዉይይት ያደርግ ይሆናል» አለ ሚኻኤል ሹኮቭ።የሰላሳ አራት አመት ወጣት ነዉ።ገለልተኛ ነኝ ይላል።

 ሹኮቭ ያኔም-ዛሬም እንደ ወጣት ሩሲያዊ ለራሱ ጥሩ-ትምሕርት፥ ሥራ ለማግኘት ከመጣር፥ ለሐገር፣ ለወገኑ እድገት ደሕንነት ከመመኘት ባለፍ ሥለ ፖለቲካዉ ጡቃንጡቅ ብዙም አያዉቅም። የሱና የብጤዎቹ ኑሮ ከያኔ ዛሬ ብዙ እንደሚሻል ግን ጠንቅቆ ያዉቀዋል።ያኔ የሃያ-አንድ አመት ተማሪ ነበር።1999 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የወላጆቹ ገቢ ከዕለት ወደ ዕለት እያሽቆለቆለ፥ ድሕነት እያፈጠጠ መምጣቱን፣ የኑሮ ዉድነቱን፣ ከማላሰል ባለፍ ሰበብ ምክንያቱን ለማስተንተን እዉቀቱም ብስለቱ ፍላጎቱም አልነበረዉም።

ቼችንያ የዘመተዉ ጦር ድል እያደረገ መሆኑን  አለማወቅ ግን አችልም ነበር።ትንሽ ትንሽ የሚያዉቀዉ የኮፒዉተር መርሐ-ግብር ከጥቂት ቀናት በሕዋላ በሚለወጠዉ አዲስ ዘመን ምክንያት ይሳከራል የሚለዉን አስተያየትም አለመስማት አይችልም ነበር።የሞስኮ ቴሌቪዥን ልዩ ቃለ-መጠየቁን ያሰራጨዉ የዚያ ወጣት ዓዕምሮ ብዙ በሚያቀዉ ችግር፣ ብዙ በሰማዉ የቼችንያ ድል፥ ብዙ በማያዉቀዉ የኮፒዉተር መሳከር መሐል በተቃረጠበት ሰሞን ነበር።

ታሕሳስ-አጋማሽ 1999  «ፕሬዝዳንቱ እርስዎን እንደተተኪያቸዉ ነዉ የሚያዎት።» ጠየቀች ጋዜጠኛዋ አዲሱን ጠቅላይ ሚንስትር፥-«ፕሬዝዳንቱ እንደዚያ ካሉ፣ ባሉት አለመስመስማማት ከንቀት ይቆጠራል» መለሱ።ከፕሬዝዳንት ቦሪስ የልሲን ምናልባት ከጥቂት ታማኞቻቸዉ በስተቀር፣ እኛ በሞስኮ ፖለቲካ ብዙም የማይታወቁት መጣጣ፣ መላጣ፣ አይነ-ቅብዝብዝ ሰዉዬ የተመሰቃቀለችዉን ሐገር በቅጡ ይመራሉ፥ የነሹኮቭን ኑሮ ከቁልቁሊት ሩጫ ይገታሉ ብሎ የገመተ፥ ተስፋ ያደረገ መኖሩ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።

ሰዉዬዉ ግን በሳምንቱ ያረጁ የፋጁትን፥ በጤና እጦት፥ በመጠጥ ብዛት የተዳከሙትን ፕሬዝዳት ቦሪስ የልትሲንን ተክተዉ ተጠባባቂ ፕሬዝዳት ሆኑ።ታሕሳስ ሰላሳ-አንድ 1999።ቭላድሚር ፑቲን።ለሩሲያ የዘመን መለወጫ ስጦታ ብጤ ነበር።

ኦሌግ ኖይማይቫኪን የሃያ-ስድስት አመት ወጣት እና የኮሚዉተር ባለሙያ ነዉ።«ከዚሕ ሥርዓት ምጣኔ ሐብታዊም ሆነ ማሕበራዊ ዕድገት ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም» አለ በቀደም።ፑቲን የሚመሩት መንግሥት ለወደፊቱ በጎ-መጥፎ መስራት አለመስራቱ በርግጥ ሲሆን የሚታይ ነዉ።

ኖይማይቫኪን የአስራ-ሰወስት አመት ልጅ በነበረበት ዘመን የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን የተረከቡት ፑቲን ግን ያኔ ብዙዎች የገመቱትን ኋላ በግምት አስቀርተዉታል።ፑቲን መጀመሪያ እንደ ጠቅላይ ሚንስትር ኋላ እንደ ፕሬዝዳት ወደ ቼቺንያ ያዘመቱት የሩሲያ ጦር በዚያች ትንሽ ግዛት ጉስቁል ሕዝብ ላይ ያደረሰዉ ግፍ በደል በርግጥ መንግሥታቸዉን በሰብአዊ መብት ረጋጭነት፥ ጦራቸዉን በገዳይነት ማስወቀስ-ማስተቸቱ አልቀርም።ከሶቬት ሕብረት መፈረካከስ በሕዋላ ለሩሲያ ፌደረሽን መበታተን ትልቅ ስጋት የነበረዉን ጦርነት በድል አድራጊነት ማጠናቀቃቸዉ ግን በርግጥ አላከራከረም።

ፑቲን የፕሬዝዳትነት ሥልጣኑን ሲረከቡ በቆዳ ሥፋት ከዓለም ተወዳዳሪ የማይገኝላት፥ በተፈጥሮ ሐብት የተንበሸበሸችዉ፥ በጦር ሐይል ቴክኖሎጂ፥ በጠፈር ሳይንስ የረቀቀች-የመጠቀችዉ ሩሲያ  ከልዕለ-ሐይልነት ወደ ምዱባን መኖሪያነት፥ ከጠንካራ የሕግ ሥርዓት ተገዢነት ወደ ማጅራት መቺ፥ አጭበርባሪ ማፍያዎች መፍለቂያነት፥ ከእዉቀት ሐብት መፍለቂያነት ወደ ተበዳሪ-ለማኝነት የዘቀጠች ሐገር ነበረች።

የቀድሞዉ እዉቅ የስላላ ባለሙያ ሁለተኛ የፕሬዝዳትነት ዘመነ-ሥልጣናቸዉን በሁለት ሺሕ ስድስት ሲያጋምሱ ግን የዚያች ሐገር አጠቃላይ የሐገር ዉስጥ ገቢ በሰባ ሁለት ከመቶ ተንቻሮ ነበር።በየቆመበት የዛገ-የወላለቀዉ፥ ዘመናይ የጦር መሳሪያና መርከብ ታድሶ፥ ወይም ባዳዲስ ተተክቶ የቆመዉ የጦር እንዱስትሪ አንሰራርቶ ፥ደሞዝና ቀለብ አጥቶ የተጎሳቆለዉ ወታደር የታላቅ ሐገር ወታደርነት ክብር ማዕረግ አግኝቶ የትልቂቱን ሐገር ትልቅነት አስከባሪነቱን አረጋግጦ ነበር።

በ1999  ከሩሲያ ሕዝብ ከሰላሳ-ከመቶ የሚበልጠዉ ከድሕነት ጠገግ በታች ይኖር ነበር።በሁለት ሺሕ ስምንት የደኸዉ ሩሲያ ቁጥር ወደ አስራ-አራት ከመቶ አሽቆልቁሎ ነበር።ወደ ተመፅዋችነት ዘቅጣ የነበረችዉ ሩሲያ ከዓለም ሰባተኛ ባለ ኢኮኖሚ ሐገር ሆናለች።

የሩሲያዊዉ ሠራተኛ አማካይ የወር ደሞዝ ከሰማንያ ዶላር ወደ ስድስት መቶ አርባ ዶላር ተንቻሯል። በዚሕም ሰበብ ሰዉዬዉን ዛሬም «የትልቁ አባት ሐገር» አዳኝ፥ የታላቁ ሕዝብ ታላቅ መሪ እያሉ የሚያንቆለጳጵሷቸዉ ሚሊዮኖች አሉ።ባለፈዉ መጋቢት በተደረገዉ ምርጫ የማሸነፋቸዉ ዜና ሲሰማ ሞስኮን የቀድሞ ቀይ አደባባይ ያጥለቀለቀዉ ደጋፊያቸዉ ቁጥርም ቀላል አይደለም።
                 

ፑቲን፥ ለፈጠሯት ለዲሲቱ ሩሲያ ግን ብዙዎች እንደሚሉት መርሕ-አስተሳሰባቸዉ አሁን በርግጥ አርጅተዉበታል።በፕሬዝዳትነትም በጠቅላይ ሚንስትርነትም ብለዉ ሩሲያን ላለፉት አስራ-ሁለት ዓመታት የመሩት ፑቲን ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ላይ በመቆየታቸዉ፥ መሠልቸታቸዉ አልበቃ ብሎ የመጋቢቱን ምርጫ አጭበርብረዋል መባሉ ነዉ እስከ ዛሬ ያልበረደዉ የተቃዋሚዎቻቸዉ ቁጣ ሰበብ።


«ምርጫ ነበር? ንገሩኝ፥ ይሕ ምርጫ ነበር?ያንን ያዞ እንባ ያነቡትን ሰዉዬ የኛ ፕሬዝዳንት ማለት እንችላለን።ዛሬ እንድንሰለፍ የተሰጠን ፍቃድ ሲያበቃ ሌላ የሆነ ቦታ መሔድ አለብን።ለመበተን መጣደፍ የለብንም።ነገሩ ቀላል ነዉ።አድም እነሱ እንደገና ስድስት አመት ይገዙናል አለበለዚያ እኛ እነሱን (እናስወግዳለን)።እታገላለሁ።እናንተም።»

የግራ ፖለቲካ የሚያቀነቅነዉ ንቅናቄ መሪ ሰርጌይ ኡዳልሶቭ።ፑቲን ማሸነፋቸዉን ከተቃወሙት የሞስኮ ሠልፈኞች አንዱ ነበሩ።ፑቲን ዛሬ ቃለ-መሐላ ሲፈፅሙም ተቃዋሚዎቻቸዉ በአደባባይ ሠልፍ እንዳወገዟቸዉ ነዉ።

የፑቲን መርሕ ከሐገር ዉስጥ ደጋፊ-ተቃዋቂዎቹን እንዳራራቀ ሁሉ የዉጪ መርሐቸዉም የድጋፍ-ተቃዉሞ ስብጥር ነዉ።ተቃሮኖ።ሰኔ ሁለት ሺሕ ላይ ከያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ሲገናኙ ቡሽ «የልባቸዉን ስሜት» ካይናቸዉ ዉስጥ አነበብኩ በማለት አወድሰዉ-አድንቀዋቸዉ ነበር።

ፑቲንን ከቡሽ እኩል ያዩት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ኮሊን ፓወል ግን የአለቃቸዉን እምነት አልተጋሩም ነበር።እንዲያዉም እኔ «ከፑቲን አይን ያነበብኩት-ኬጂቢን ነዉ» አሉ። እሳቸዉም ጡረተኛ ጄኔራል እንጂ ዲፕሎማት አልነበሩም።ያም ሆኖ ፑቲን የአፍቃኒስታኑን ጦርነት ሲደግፉ፥«በአለም አቀፍ ፀረ-ሽብር» ዘመቻ ሲሳተፉ ለምዕራባዉያኑ ጥሩ ወዳጅ፥ ደሕና መሪ  ነበሩ። የኢራቅ ወረራን ሲተቹ፥ የአሜሪካን የፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬል መርሐ-ግብር ሲያወግዙ፥ በተለይ አሁን የሶሪያን መንግሥት መቀጣቱን ሲቃወሙ መጥፎ ፖለቲከኛ እና መሪ ናቸዉ።

ዛሬ ቃላ መሐላ ከመፈፀማቸዉ በፊት በሰጡት መግለጫ ሐገራቸዉንና ከምዕራባዉያን በጣሙን ከዩናትድ ስቴትስ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል «አስፈላጊዉን ርቀት እጓዛለሁ» ብለዋል።ፑቲን ከዉድቀት ያዳኑት የሩሲያ ሁለተኛ አብዮት የሚደገፍ፥ የሚወደድበት ከምጣኔ ሐብቱ እድገት፥ ከወታደራዊ አቅሙ ብርታት እኩል የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ማጎንቆሉ ነዉ።ጀርመናዊዉ የሩሲያ ጉዳይ አዋቂ የንስ ሲገርት የሩሲያ የዲሞክራሲዉ ሥርዓት ጅምር መጠንከሩን ይጠራጠራሉ።
             
«የዲሞክራሲያዊ አስተዳድርን በተመለከተ እኔ በጥቅስ ምልክት ዉስጥ ነዉ የማስቀምጠዉ።ምክንያቱም እኔ እንደሚመስለኝ ዲሞክራሲን የሚመሰክሩ ሁኔታዎች አይታዩም።ሩሲያ ዛሬ የአምባገነን ሐገር ናት።ዲሞክራሲያዊት ናት ማለት አይቻልም።»

ፕሬዝዳት ፑቲን በተሻሻለዉ ሕግ-መንግሥት መሠረት ዛሬ «ሉዓላዊነቷን እና አድነቷን ሊያስከብሩ ቃል የገቡላትን ትልቅ ሐገር እስከ ሁለት ሺሕ አስራ-ስምንት ይመራሉ።ከዚያ በሕዋላ በሚደረገዉ ምርጫ እወዳደራለሁ ቢሉም ላንድ ዙር ሕጉም ይፈቅድላቸዋል፥ ሥልጣኑም በጃቸዉ ነዉ።ለዛሬዉ ይብቃን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

1089471 Russia, Astrakhan. 04/10/2012 From left in the center: blogger Aleksey Navalny and former candidate for mayor of Astrakhan Oleg Shein take part in an unauthorized rally against mayoral election fraud in Astrakhan. Alexey Kudenko/RIA Novosti
ተቃዉሞ ሰልፍምስል picture-alliance/dpa
1089423 Russia, Astrakhan. 04/10/2012 Oleg Shein, former candidate for mayor of Astrakhan, takes part in an unauthorized rally against mayoral election fraud in Astrakhan. Alexey Kudenko/RIA Novosti
ተቃዉሞምስል picture-alliance/dpa
Activists gather, holding banners and placards, in a show of support for Russia's Prime Minister Vladimir Putin in central Moscow February 4, 2012. Tens of thousands of Russians defied bitter cold in Moscow on Saturday to demand fair elections in a march against Putin's 12-year rule, and thousands of others staged a rally supporting the prime minister. The banner (C) reads "Who, if not Putin?" REUTERS/Sergei Karpukhin (RUSSIA - Tags: CIVIL UNREST POLITICS ELECTIONS)
ደጋፊያቸዉምስል REUTERS

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ