1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሩስያ አዲስ ፓትርያርክ መምረጥዋ

ረቡዕ፣ ጥር 20 2001

አንድ መቶ ሀምሳ ሚልዮን አባላት የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ትናንት አዲስ ፓትርያርክ ሰየመች።

https://p.dw.com/p/Gi0w
ፓትርያርክ ኪሪል
ፓትርያርክ ኪሪልምስል AP

ሰባት መቶ አስራ አንድ አባላት የሚጠቃለሉበት የቤተ ክርስትያኒቱ ሲኖዶስ በመዲናይቱ ሞስኮ ባካሄደው የድምጽ አሰጣጥ ስነ ስርዓት ላይ የስሞሌንስክና የካሊኒንግራድ አካባቢ መንፈሳዊ መሪ ኪሪልን በከፍተኛ የድምጽ ብልጫ ለሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን መሪነት መርጦዋቸዋል። አርያም ተክሌ ዝርዝር ዘገባ አላት።

የስሞሌንስክና የካሊኒንግራድ አካባቢ መንፈሳዊ መሪ ኪሪል ሲኖዶሱ ባካሄደው የመጀመሪያው ዙር ምርጫው የካሉጋና የቦሮቭስካን መንፈሳዊ መሪ ክሌመንትን አምስት መቶ ስምንት ለአንድ መቶ ስድሳ ዘጠኝ በሆነ የድምጽ ብልጫ በማሸነፍ ባለፈው ወር ህይወታቸው ያለፈችውንና የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያንን ላለፉት አስራ ስምንት ዓመታት የመሩትን ፓትርያርክ አሌክሴይን ተክተዋል። በምርጫው በዕጩነት ይቀርባሉ ተብለው የነበሩት የቤላሩስ አካባቢዎች መሪ ፊላሬት ከምርጫው መራቃቸውን ቀደም ሲል ቃል አቀባያቸው ቪጊላንስኪ አስታውቀዋል።

« ፊላሬት ዕጩነታቸውን ስበዋል። ደጋፊዎቻቸውም ድምጻቸውን ለኪሪል እንዲሰጡ ጠይቀዋል። »

የሰባ ሶስት ዓመቱ ፊላሬት በዚሁ ርምጃቸው የቤተክርስትያኒቱን የአንድነት ምልክት ለማጉላት መፈለጋቸውን አስረድተዋል። በርግጥም፡ ብዙዎች ይህንኑ የፊላሬትን ርምጃ እና ኪሪልም በመጀመሪያው ዙር መመረጣቸውን በቤተ ክርስትያኒቱ ዙርያ እንዲኖር የሚፈለገውን አንድነት እንዳጎላ ድርጊት ተመልክተውታል። ሲኖዶሱ ድምጽ ከመስጠቱ በፊት ባሰሙት ንግግራቸው፡ የቤተክርስትያኒቱ አንድነት ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነበር የጠየቁት።

« የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የምትከተለውን መንገድ ለመወሰን ይኸው አሁን በእግዚአብሄር መሪነት ከተለያዩት ሀገሮችና አካባቢዎች እዚህ መጥተናል። የሩስያ ዳግም ጥምቀት ስለታየባቸው ስላለፉት አስራ ስምንት ዓመታትም አቋም መውሰድ አለብን። የቤተክርስትያናችንን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እንድናሰላስል ተጠርተናል። »

ኪሊል አዲሱ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሆነው ከተመረጡ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክታቸውም ይህንኑ የቤተክርስትያኒቱን የአንድነት ፍላጎት ያጎላውን ጥሪያቸውን በድጋሚ ከማስተጋባታቸው ጎን፡ የቤተክርስትያኒቱ ተከታይ ምዕመናን ፕሮቴስታንቶችና ካቶሊካውያን ወደራሳችው ሀይማኖት ሊስቡዋቸው የሚያደርጉትን ሙከራ እንዲቋቋሙ አሳስበዋል። በዚህም አንዳንዶች አዲሱና ዘመናይ አመለካከት አላቸው የሚባሉት ፓትሪያርክ ኪሪል፡ በሟቹ አሌክሴይ አንጻር፡ ከሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ጋር ያለውን የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ግንኙነትን ያሻሽሉ ይሆናል በሚል አሰምተዋእት የነበረውን ተስፋ አደብዘውታል። ላለፉት አሰርተ ዓመታት የወንጌልን ቃል ያሰሙበት የራሳቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራም የነበራቸው አዲሱ ፓትርያርክ ኪሪል የሩስያ ፖለቲከኞች እንደፈለጉት ሊቆጣጠሩዋቸው የማይችሉ ጠንካራ ግለሰብ መሆናቸውን አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች የኪሪልን ምርጫ አስመልክተው አስታውቀዋል።

የሩስያ ፕሬዚደንት ዲሚትሪ ሜቬዴቭ ከምርጫው በኋላ ለኪሪል ባስተላለፉት የደስታ መልዕክት ላይ፡ ኪሪል በቤተ ክርስትያንና በመንግስት መካከል የሚኖረውን ውይይት የሚያጠናክሩና መንፈሳዊ እሴቶችን የሚያራምዱ መሪ እንደሚሆኑ ተስፋቸዋውን ገልጸዋል።

AA, Tekle Yewhala

Quelle: AFPE,RTR, DW