1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሩስያ ወታደሮቿን በተጠንቀቅ አቆመች

ቅዳሜ፣ ሰኔ 14 2006

ምንም እንኳን ሩስያ ወታደሮቿን በተጠንቀቅ ብታቆምም፤ የምዕራቡ ሀገራት ማዕቀባቸውን ቢያጠናክሩም፤ የዮክሬይን መንግሥት የአንድ ወገን የተኩስ አቁም ዉሳኔ ቢደርስም፤ የመፍቀሬ ሩሲያ አማፂያን ጦራቸዉን አላስቀመጡም።

https://p.dw.com/p/1CNbj
Ostukraine Krise Separatisten 12.06.2014 in Snischne
ምስል Reuters

የሩስያዉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወታደሮቻቸዉን በመካከለኛዉ ሩስያ ለጦነት በተጠንቀቅ አቆሙ። የሩስያ ወታደራዊ ኃይል ለአንድ ሳምንት በሳይቤሪያ ድንበር አካባቢ ኡራል ዉስጥ የጦር ልምምድ ማድረጉ ተመልክቶአል። ይህ አካባቢ ከዩክሬይን ድንበር አንድ ሽ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ቦታ ነዉ። በጦር ልምምዱ ወደ 65 ሺ ወታደሮች መካፈላቸዉ ተዘግቧል። ይህ የሩስያ ርምጃ በዩክሬን እና በሩስያ መካከል ያለዉን ቅራኔ ይበልጥ እንዳያባብሰዉ አስግቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬይኑ ፕሬዚዳንት ፔትሮ ፖሮሼንኮ፤ የዩክሬን ወታደሮች በምስራቅ ዩክሬን፤ ከመፍቀሬ ሩስያ ተገንጣዮች ጋር የሚያደርጉትን ዉግያ እንዲያቆሙ ትናንት አርብ መወሰናቸዉ ይታወቃል። ከትናንት ምሽት ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ተግባራዊ የሚሆነዉ የአንድ ወገን የተኩስ ማቆም ዉሳኔ፤ 15 ነጥቦችን ያዘለ ሲሆን፤ የአካባቢዊ መንግሥት ሥርዓትን የሚያጠናክርና ፤ ሩስያ ቋንቋ የሚናገሩ የዩክሬይን ዜጎች ጥቅም የሚያስጠብቅ እና ከለላ የሚሰጥ፣ ህገ-መንግስቱን የሚያሰፋ ነጥብ እንደሚካተትበት ኪቭ የሚገኘዉ የፕሬዚዳንቱ ጽ/ቤት አስታዉቋል። የሞስኮ መንግሥት ግን ይህን ሰላም የማምጣት ሂደት በጥርጣሬ ነዉ የተመለከተዉ። በምስራቅ ዩክሬይን የሚንቀሳቀሱት የመፍቀሬ ሩስያ ተገንጣዮችም፤ የዩክሬይን ጦር ከቦታዉ እስካለቀቀ ድረስ መሳርያቸዉን እንደማያስቀምጡ አስታዉቀዋል።

Ukraine Kiew Poroschenko Parlament 19.06.2014
ምስል AFP/Getty Images

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ