1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሪያድ፤ ሳልህ በባህረ ሰላጤዉ አገሮች የቀረበዉን ዉል ፈረሙ

ረቡዕ፣ ኅዳር 13 2004

የየመን ፕሬዝደንት አሊ አብዱላ ሳልህ ስልጣን ለመልቀቅ የሚያስችላቸዉን ዉል ፈረሙ። ከተቃዋሚዎች ጋ ለመተባበርና የቀረበላቸዉን ዉል በሚመለከት ለመተባበርም መዘጋጀታቸዉን ሳልህ መናገራቸዉን ተዘግቧል።

https://p.dw.com/p/Ry7y
አሊ አብዱላ ሳልህምስል picture alliance/dpa

ዛሬ ስዑዲ አረቢያ መዲና የተፈረመዉ ዉል የሳልህን የ33ዓመታት የስልጣን ዘመን ከፍፃሜ የሚያደርስ እንደሆነም ተገልጿል። ሰንዓ ላይ ለጋዜጠኞች ጉዳዩን ይፋ ያደረጉት የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ የየመን ልዑክ ጃማል ቢን ኦማር ተቃዋሚዎችና ገዢ ፓርቲዎች እቅዱ በሚከናወንበት ሁኔታ ላይ ከስምምነት ደርሰዋል። በሪያድ ይፈፀማል ተብሎ የሚጠበቀዉ የፕሬዝደንት ሳልህ ፊርማም ካለፈዉ ዓመት ጥር ወር አንስቶ በህዝባዊ ዓመፅ ለምትናወጠዉ የመን መረጋጋትን እንደሚያመጣም አመልክተዋል፤

«የስልጣን ሽግግሩ የሚደረግበት ደረጃና ዝርዝሩ የረዘመ ሲሆን፤ ብሄራዊ የአንድነት መንግስት ከመመስረት አንስቶ፤ አመፅን በማስቆም የሚያረጋጋ፤ እንዲሁም በጦር ኃይሉ ዉስጥ ያለዉን ክፍፍል አጥፍቶ የሚሊሽያዉን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር ወታደራዊ ኮሚሽን ማቋቋምን ያካትታል። በተጨማሪም በዚሁ አዉድ ይቺ አገር የገጠማትን ፈተና በመነጋገርና ለየመኖች ቀጣዩን መስመር የሚያመላክት ብሄራዊ ዉይይት መድረክ ማቋቋምም ይኖራል።»

ዘገባዎች እንደሚሉት ፕሬዝደንት ሳልህ ስልጣናቸዉን ለምክትላቸዉ ለመስጠት ሳይዘጋጁ አልቀሩም። እንዲያም ሆኖ ዉሉ የሳልህን ያለመከሰስ መብት ያስከብራል በሚል በሺዎች የሚቆጠሩ የመናዉያን ለተቃዉሞ አደባባይ ወጥተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሠ