1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ርዋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ጀርመን

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 11 2007

በቡሩንዲ እና በርዋንዳ ፕሬዚደንቶች የሥልጣን ጊዚያቸውን ለማራዘም ጥረት ጀምረዋል። ይህንኑ ጥረት፣ የዶይቸ ቬለ ካትሪን ማታይ እንደዘገበችው፣ ጀርመን በተለያየ መልኩ ነው የምተመለከተው። ይህም አደገኛ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ተቺዎች አስጠንቅቀዋል።

https://p.dw.com/p/1G0u8
Bujumbura Burundi Protest Gewalt
ምስል Reuters/J. P. Harerimana

[No title]

የቡሩንዲ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን ለመወዳደር መወሰናቸውን ይፋ ካደረጉ ካለፉት በርካታ ወራት ወዲህ በሀገሪቱ ተቃውሞ እና የኃይሉ ተግባር ቀጥሏል። ከ15 ዓመት በፊት የቡሩንዲ የርስበርስ ጦርነት ማብቃቱን ባረጋገጠው እና በአሩሻ፣ ታንዛኒያ በተፈረመው ውል እና ከ10 ዓመት በፊት በፀደቀው የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት፣ ሁለት የአምስት ዓመት የአገልግሎት ዘመኑን የፈፀመ ፕሬዚዳንት ለተጨማሪ ዘመራር ዘመን በሥልጣን ሊቆይ አይችልም። ይሁንና፣ ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ ለመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የተመረጡት በምክር ቤቱ መሆኑን በማመልከት ፣ የፊታችን ሀምሌ 21፣ 2015 ዓም በሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ መወዳደር እንደሚችሉ ነው የሚከራከሩት። የመንግሥቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ርምጃው የመፈንቅለ መንግሥት ያህል እንደሚቆጠር በማመልከት ሕዝቡ የፕሬዚደንቱን ውሳኔ ተቃውሞ እንዲነሳ ቅስቀሳቸውን ቀጥለዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጠቅላላ የቡሩንዲ ጊዚያዊ ሁኔታ በስጋት እየተከታተለው ይገኛል። ተቀናቃኞቹ ወገኖች ለተፈጠረው ውዝግብ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲያፈላልጉለት ጥሪ አስተላልፋለች።

በቡሩንዲ አንፃር፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጎረቤት ርዋንዳ ለተፈጠረው ተመሳሳይ ሁኔታ ያን ያህል ትኩረት አልሰጠም። የርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜም ፣ ምንም እንኳን ሕገ መንግሥቱ ባይፈቅድላቸውም፣ ሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው እአአ በ2017 ዓም ሲያበቃ ለሶስተኛ ጊዜ ለመወዳደር ሀሳብ እንዳላቸው ነው የተሰማው። ፕሬዚደንቱ ስለዚሁ ጉዳይ በይፋ ባይናገሩም፣ ገዢው ዓብዮታዊ ግንባር ፓርቲያቸው፣ «RPF» የካጋሜን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም አዳዲስ ሥልቶችን ተግባራዊ ለማድረግ መንገዱን በማመቻቸት ላይ ይገኛል። ፓርቲው ይህንኑ ጥረቱን ለማሳካት በዚህ ሳምንት ሕገ መንግሥቱን ለማስቀየር ለምክር ቤት ያቀረቡትን ረቂቅ ሕግ እንደራሴዎቹ በሰፊ የድምፅ ብልጫ አፅድቀውታል። በፀደቀው ሕግ መሠረት፣ የርዋንዳ ሕዝብ በፕሬዝደንቱ ሥልጣን ዘመን ላይ ያረፈው ገደብ ይነሳ አይነሳ በሚለው ጥያቄ ላይ ሬፈረንደም ያካሂዳል። ዕለቱ ገና ያልተወሰነው የሬፈረንደሙ ውጤት አዎንታዊ ምላሽ ካገኘ ካጋሜ እድሜ ልክ ይገዛሉ።

Präsident von Ruanda Paul Kagame
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

የያኔው ዓማፂ ቡድን ዓብዮታዊ ግንባር ፓርቲያቸው እአአ 1994 ዓም 800,000 የቱትሲ ጎሳ እና ለዘብተኛ የሁቱ ጎሣ አባላት የተገደሉበትን የጎሣ ጭፍጨፋ ካበቃ ወዲህ ፕሬዚደንት ካጋሜ ርዋንዳን በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ በመግዛት ላይ ይገኛሉ።

በርዋንዳ በሰፈነው መረጋጋ ፣ በሀገሪቱ በተመዘገበው የኤኮኖሚ እድገት እና ባነቃቃችው ማህበራዊ ተሀድሶ የተነሳ ራሷን በአፍሪቃ እንደ አርአያ የምትታይ ሀገር አድርጋ ነው የምትመለከተው፣ የጀርመን መንግሥትም ይህንኑ አስተያየት ይጋራል።

Botschafter in Ruanda Peter Fahrenholtz
አምባሳደር ፋርንሆልትስምስል picture-alliance/dpa/J. Carstensen

የቡሩንዲ እና የርዋንዳ ፕሬዚደንቶች የሀገራቸው ህገ መንግሥት የሥልጣን ዘመን የማራዘም እቅዳቸው እንቅፋት እንደደቀነባቸው ይሰማቸዋል። ይሁንና፣ በቡሩንዲ የሚገኙት የጀርመን አምባሳደር ፔተር ፋርንሆልትስ የቡሩንዲን ፕሬዚደንት ለሶስተኛ ጊዜ የመወዳደርን እቅድ በግልጽ ቢነቅፉም፣ በርዋንዳ ሊካሄድ የታሰበውን ሬፈረንደም በግልጽ ደግፈዋል። ፋርንሆልትስ ለርዋንዳ መንግሥት ቅርበት አለው ለሚባለው «ኒው ታይምስ» ለተባለው የሀገሪቱ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ « በ(ርዋንዳ) የሕገ መንግሥቱን ለውጥ እና ምርጫውን በተመለከተ ግልጽ እና ትክክለኛ ሂደት እንደሚገኝ እርግጠኛ መሆናቸውን ነው» የገለጹት። አስፈላጊውን ውሳኔ የመውሰዱ ኃላፊነት የርዋንዳ ሕዝብ እጅ ላይ መሆኑን ያመለከቱት ጀርመናዊው አምባሳደር ፋርንሆልትስ በዚያው ቃለ ምልልስ ቡሩንዲ ወደፊት ትራመድ ዘንድ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ፒየር ንኩሩንዚዛ የመወዳደር እቅዳቸውን እንዲሰርዙ እስከመምከር ርቀው ሄደዋል። የጀርመን አምባሳደሮች ለወትሮው ቃለ ምልልስ የማይሰጡበት እና ጥንቃቄ የተመላው ዲፕሎማሲያዊ አነጋገር እንደሚመርጡ ሲታሰብ ይህ የአምባሳደር ፋርንሆልስ አስተያየት አስገራሚ ሆኖ እንዳገኙት በቤልጅየም የአንትወርፕ ዩኒቨርሲቲ የልማት ፖለቲካ መምህር ፕሮፌሰር ስቴፍ ፋንደግኒስት ገልጸዋል። ፋንደግኒስት አምባሳደሩ ለዚሁ አነጋገራቸው ማብራሪያ እንዲሰጡ በላኩላቸው በአንድ ግልጽ ደብዳቤ ላይ ቀጣዮቹን ጥያቄዎች በማስፈር መጠየቃቸውን አስታውቀዋል።

« ቃለ ምልልሱ ጥሩ እና መጥፎ መሪዎች እንዳሉ የሚጠቁም ይመስላል። ጥያቄው ግን ምንድን ነው ርዋንዳን ጥሩ፣ ቡሩንዲን መጥፎ ያደረገው የሚለው ነው። ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን እና የሰብዓዊ መብቶችን በማክበሩ ረገድ ርዋንዳ የተሻለ አሰራር እየተከተለች ነው? በሀገሪቱ የተሻለ የፕሬስ ነፃነት፣ ንቁ ሲቭል ማህበረሰብ አለ? የተቃውሞ ፓርቲዎች ተጨማሪ የመናገር ነፃነት አላቸው? አይመስለኝም። »

ፋንደግኒስት የአምባሳደሩ ምላሽ እስካሁን አልደረሳቸውም።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስለ ርዋንዳ ከጥቂት ጊዜ በፊት ባወጣው የመጨረሻው ዘገባ እንዳስታወቀው፣ ርዋንዳ ውስጥ አስተያየት የመግለጽ እና የፕሬስ ነፃነት ግዙፍ ገደብ አርፎባቸዋል። የመንግሥቱ ተቃዋሚዎች ብርቱ ክትትል ይደረግባቸዋል። አምነስቲ በዘገባው ይፈጸማል ያለው ክትትል እንደደረሰበት የርዋንዳ ዜጋ የሆነው ጋዜጠኛው ፍሬድ ሙቩኒዪ አረጋግጦዋል። ጋዜጠኛው ባለፈው ግንቦት ሀገሩን ለቆ ወደ ኔዘርላንድስ መሸሽ መገደዱን ነው በቅሬታ የሚገልጸው።

« አሁን በስደት ላይ እገኛለሁ። ርዋንዳ ውስጥ ጦርነት የለም፣ ውዝግብ የለም። ያም ቢሆን ግን፣ የዜግነት መብት የለኝም። »

እርግጥ ፣ ርዋንዳ ጥሩ የኤኮኖሚ እድገት አሳይታለች፣ ለዚህም ከያቅጣጫው ብዙ አድናቆት አትርፋለች። ይህ የማይካድ ሀቅ መሆኑን ጋዜጠኛው ቢያመለክትም፣ ይህ አዎንታዊ እመርታ ዴሞክራሲያዊ እሴቶች በሀገሪቱ ከሚስፋፉበት ሂደት ጎን ለጎን እንዲከናወን መመኘቱን ከመግለጽ ወደኋላ አላለም።

« ምኞቴ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን እንዳይወዳደሩ ግፊት እንዲያሳርፍባቸው ነው። ምክንያቱም ይህ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አይታ ለማታውቀው ሀገራችን ጥሩ መልዕክት ያስተላልፋል።»

የጀርመን መንግሥት ቡሩንዲን እና ርዋንዳን በአንድ ዓይን የማታይበት ምክንያት ምንድን ነው? የአንድ ሀገር ተጓዳኞች የሆኑ የውጭ አጋሮች የዚያችን ሀገር መሪዎችን ተግባር እንዲነቅፉ በዚችው ሀገር ውስጥ አለመረጋጋት መፈጠር አለበት ወይ? አምባሳደር ፋርንሆልስ በቃለ ምልልሱ የራሳቸውን አስተያየት ነው የሰጡት ወይስ የሀገራቸውን መንግሥት ወክለው? የአምባሳደሩን አስተያየት ጉዳዩ የሚመለከተው በርሊን የሚገኘው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እንዴት እንደተመለከተው መልስ ለማግኘት ዶይቸ ቬለ በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

የአንትወርፕ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ፋንደግኒስት ግን የአምባሳደሩ ዓይነት አስተያየት ለልማት ትብብር ተዓማኒነት አደገኛ መሆኑን ነው ያስጠነቀቁት። ፋንደንግኒስት እንደሚሉት፣ የጀርመናዊው አምባሳደር አነጋገር በየሀገሮቹ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመትከል የሚታገለው ሲቭሉ ሕዝብ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ እምነት እንዳያድርበት ነው የሚያደርገው። ርዋንዳዊው ጋዜጠኛ ፍሬድ ሙቩኒዪም በሀገሩ ሕገ መንግሥቱን ለመቀየር የተያዘው እቅድ የሀገሩን የወደፊት ዕድል ጎጂ መሆኑን አስጠንቅቋል።

ካትሪን ማታይ/አርያም ተክሌ

ልደት አበበ