1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ርዕሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስኩስ ከቫቲካን

እሑድ፣ መጋቢት 22 2005

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስኩስ ከቫቲካን ባስተላለፉት የትንሣዔ በዓል የመጀመሪያ መልዕክታቸው በዓለም ላይ ሠላምን ለማስፈን የበለጠ ጥረት እንዲደረግ አሳሰቡ። በቫቲካኑ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተካሄደው መንፈሣዊ ስነ ስርዓት ላይ 250 ሺህ ግድም ምዕመናን ተገኝተዋል።

https://p.dw.com/p/187VL
ምስል Getty Images

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስኩስ የእሁድ መጋቢት 22 ቀን 2005 ዓም የትንሣዔ በዓለን ምክንያት በማድረግ ባስተላፉት መልዕክት በዓለም ላይ ሰላምን ለማስፈን የበለጠ ጥረት እንዲደረግ አሳሰቡ። የካቶሊኳ ቤተ-ክርስቲያን መንፈሣዊ አባት የዓለም ሰላም በሰው ንግድ፣ በዓመጽ፣ በሱስ ዕጽዋት ንግድ ጦርነትና በተፈጥሮ ሃብት ብዝብዛ መቀጠል የራስ ወዳድነት አደጋ ተደቅኖጸበት እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

Ostermesse Petersplatz Rom Segen Urbi et Orbi
ምስል AFP/Getty Images

በቫቲካኑ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በተካሄደው መንፈሣዊ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት ምዕመናን 250 ሺህ ገደማ ይጠጋሉ። ፍራንሲስኩስ የሶሪያን፣ የማሊንና የኮሪያን ቀውሶች ነጥለው ሲያነሱ የመካከለኛ ምሥራቅና የአፍሪቃ ውዝግቦች እንደሚያበቁ ያላቸውን ተሥፋም አያይዘው ገልጸዋል። ፍራንሲስኩስ በትንሣዔው ዋዜማ ባለፈው ሌሊት በቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል ባስቀደሱበት ወቅት ከሃይማኖታቸው የራቁ ካቶሊካውያን ወደ ዕምነታቸው እንደመለሱም ጠይቀው ነበር።

አያይዘውም በእስራኤልና በፍልስጥኤም መካከል የዘለቀው ግጭት «እጅግ የተራዘመ» መሆኑን ጠቅሰው በኢራቅ «እያንዳንዱ የዓመፃ ድርጊት ያበቃ ይሆናል» ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁንና ርዕሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስኩስ ለተሰበሰበቡት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር «ከምንም በላይ ለውድ ሶሪያ» ማለታቸውም ተደምጧል። ቀጠል አድርገውም «በግጭት ለተዳቀቀው ህዝቧ፣ ርዳታና ሠላም ለሚሻው ህዝቧ፤ የፖለቲካ መፍትሄ እስኪገን ድረስ የስንቱ ደም ይፍሰስ ስንቱስ እንዲያ ይሰቃይ?» ሲሉ አጠይቀዋል።

Ostermesse Petersplatz Rom
ምስል Reuters

ርዕሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስኩስ በንግግራቸው በዓለማችን ውጥንቅጥ ለተከሰተባቸው የአፍሪቃ ሀገራት፤ ማለትም ለማሊ፣ ናይጀሪያ እና የመካከለኛው አፍሪቃ ሪፑብሊክም ትኩረት አድርገዋል። እስያ ውስጥ ደግሞ ጳጳሱ በተለይ ለኮሪያ ሠርጥ ትኩረት ሰጥተዋል።

የ76 ዓመቱ ርዕሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ፍራንሲስኩስ መልዕክታቸውን ያጠቃለሉት በዓለማችን በተስፋፉ ችግሮች ዙሪያ በተለይም እንደ አደንዛዥ ዕፅ፣ ሕገወጥ የሰው ልጆች ዝውውር እና «ፍትህ አልባ በሆነ የተፍጥሮ ሀብት ብዝበዛ» ባላይ አፅንኦት በመስጠት መሆኑም ተዘግቧል።

የትንሣዔው ስነ ስርዓት የተጠናቀቀው የካቶሊኳ ቤተ-ክርስቲያን ርዕስ እንደተለመደው «ኡርቢ-ኤት-ኡርቢ» ለከተሞችና ለዓለም ዙሪያ የተሰኘ የትንሣዔ ቡራኬያቸውን ካስተላለፉ በኋላ ነው። የትንሣዔው በዓል በኢየሩሣሌምና በሌሎች የዓለም አካባቢዎችም ተከብሮ ውሏል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

መስፍን መኮንን