1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳን ከኤርትራ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ዘጋች

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 28 2010

ሱዳን በምስራቃዊው የሀገሪቱ ክፍል ከኤርትራ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ዘጋች፡፡ የድንበር መዝጋቱ እርምጃ የተሰማው ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ከኤርትራ ጋር በምትዋሰነው የከሰላ ግዛት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገጉ ከሳምንት በኋላ ነው፡፡ 

https://p.dw.com/p/2qRXy
Sudan Darfur Konflikt Soldaten
ምስል Getty Images/AFP/A. Shazly

የሱዳን መንግስታዊ የዜና አገልግሎት ሱና “የከሰላ አገር ገዢ አዳም ገማአ አዳም ወደ ኤርትራ የሚያሻግሩ ሁሉም ድንበሮች ከታህሳስ 27 ምሽት ጀምሮ እንዲዘጉ ድንጋጌ አስተላልፈዋል” ሲል ዘግቧል፡፡ ዘገባው ድንበሩ የተዘጋበትን ምክንያት አልጠቀሰም፡፡ በኤርትራ ያለውን ጨቋኝ መንግስት በመሸሽ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን በህገወጥ መንገድ በከሰላ በኩል አድርገው ወደ ሱዳን እንደሚገቡ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ አስታውሷል፡፡

ዜና ወኪሉ ያነጋገራቸው አንድ የከሰላ ነዋሪ ባለፉት ሁለት ቀናት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሱዳን ወታደሮች፣ በርካታ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እና ታንኮች ከተማይቱን በማቋረጥ ወደ ኤርትራ ድንበር ሲያቀኑ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሶስት የከሰላ ነዋሪዎች ለሮይተርስ እንደተናገሩት የሱዳን ወታደሮች በድንበር አቅራቢያ ሰፍረዋል፡፡ 

በከሰላ ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው ቅዳሜ ታህሳስ 21 ቀን 2010 ዓ.ም ተደንግጓል፡፡ በሱዳኑ ፕሬዝዳንት  ኦማር ሀሰን አልበሽር አማካኝነት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰሜን ኮርዶፋንም ይጨምራል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሱዳን መንግስት በጥቅምት ወር በዳርፉር እና ብሉ ናይል ግዛቶች አቅራቢያ የጀመረው የትጥቅ ማስፈታት ዘመቻ አካል እንደሆነ መገለጹ ይታወሳል፡፡ በሱዳን ከሁለቱ ግዛቶች ሌላ በሰባት ግዛቶች የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሁንም እንደጸና ነው፡፡ ከእነዚህ ግዛቶች ውስጥ አምስቱ በዳርፉር ክልል የሚገኙ ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ በደቡብ ኮርዶፋን እና ብሉ ናይል ስር ያሉ ናቸው፡፡         

ተስፋለም ወልደየስ

እሸቴ በቀለ