1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሴራሊዮን የተፈጥሮ መቅሰፍት

ነጋሽ መሐመድ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 9 2009

የሐገሪቱ ጦር፤ የርዳታ ሠራተኞች እና በጎፍቃደኞች ከሰወስት መቶ  በላይ አስከሬን ማግኘታቸዉን አስታዉቀዋል።የሟቾቹ ቁጥር እስካሁን ከሚገመተዉ እንደሚበልጥ ይነገራል።መንግስት የርሠ-ከተማይቱ ሕዝብ እንዲረጋጋ ሲጠይቅ፤ ሐገር ዉስጥና ዉጪ የሚኖሩ የሴራሊዮን ዜጎች ለተጎዱት ሰዎች መርጃ የሚዉል ገንዘብ እያዋጡ፤ ቁሳቁስም እየሰበሰቡ ነዉ

https://p.dw.com/p/2iHS3
Sierra Leone Überschwemmungen
ምስል picture-alliance/Zumapress/Xinhua

ሴራሊዮን የተፈጥሮ መቅሰፍት

የሲየራ ሊዮን  ርዕሠ-ከተማ ፍሪታዉንን መዳረሻ ባጥለቀለቀዉ ጎርፍ እና ርዕደ-ምድር የሞቱ ሰዎችን አስከሬን ለመፈለግ እና የተጎዱትን ለመርዳት የሚደረገዉ ጥረት ቀጥሎ ዉሏል።የሐገሪቱ ጦር፤ የርዳታ ሠራተኞች እና በጎፍቃደኞች ከሰወስት መቶ  በላይ አስከሬን ማግኘታቸዉን አስታዉቀዋል።የሟቾቹ ቁጥር እስካሁን ከሚገመተዉ እንደሚበልጥ ይነገራል።መንግስት የርሠ-ከተማይቱ ሕዝብ እንዲረጋጋ ሲጠይቅ፤ ሐገር ዉስጥና ዉጪ የሚኖሩ የሴራሊዮን ዜጎች ለተጎዱት ሰዎች መርጃ የሚዉል ገንዘብ እያዋጡ፤ ቁሳቁስም እየሰበሰቡ ነዉ።ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶችም መድሐኒትና ምግብ ይልካሉ ተብለዉ እየተጠበቁ ነዉ።

የአልማዝ ሐብቷን ለመቀረማት አንገት የሚቀላ፤ እጅግ-እግር የሚቀነጠስበትን፤ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች የተዋጉበትን ዘግናኝ ጦርነት ከተሰናበች ብዙ አልቆየችም።ምዕራባዉያን የፊልም ኩባንዮች «የደም-አልማዝ» እያሉ ጠቀም ያለ ገቢ የዛቁበት የጦርነት ታሪክ ተተርኮ ሳያበቃ ሌላ መቅሰፍት ተጋረጠባት። ኢቦላ።ከገዳዩ በሽታ ከተገላገለች  ዓመት-ከመንፈቅ አልደፈነችም።ትናት ሌላ አደጋ።ጎርፍ፤ርዕደ ምድር----ሞት፤ ጥፋት እና ስደት። ሲየራ ሊዮን።
                                         
«ሴራሊዮናዉያን ወገኖቼ ሆይ! ይሕ ከፍተኛ አደጋ እንድንተባበር እና እንድንረዳዳ እንደገና እየተፈታተነን ነዉ።»
ፕሬዝደንት አርነስት ባይ ኮሮማ።ጎርፍ፤ የመሬት መንሸራተት እና ርዕደ-ምድር ለምዕራብ አፊሪቃዊቱ ሐገር «አዲስ አይደለም» ይላል ሲየራ ሊዮንናዊዉ የእንግሊዝኛ ክፍል ባልደረባችን አቡበከር ጃሎ፤ «ያሁኑ ግን የከፋ ነዉ።»
                              
«በየዓመቱ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ይዘንባል።የመሬትና የጭቃ መደርመስ ይደርሳልም።ይሕን ያክል አደጋ ሲያድርስ ግን ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ።አደጋዉ የደረሰዉ ብዙ ሕዝብ በሚኖርበት የፍሪታዉን ክፍል አይደለም።ከተማዉ አጠገብ በሚገኝ ክፍታ ሥፍራ ከዕቅድ ዉጪ በተመሠረተ መንደር ላይ ነዉ የደረሰዉ።»
ፍሪታዉን እንደ አብዛኛዉ የአፍሪቃ ከተሞች ተገቢ የዉኃና የቁሻሻ ማፍሰሺያ ቱቦ የላትም።ባንድ በኩል ዉቅያኖስ፤ በሌላ በኩል የኮረብታ ሰንሰለት ያዋስኗታል።የሕዝቧ አሠፋፈርም እንደነገሩ ነዉ።ይሕ ሁሉ፤ ዝናብ በጣለ ቁጥር ነዋሪዎችዋ በሥጋት እንዲዋጡ ያደርጋል።የዘንድሮዉ አደጋ ለመክፋቱ፤ አቡበከር እንደሚለዉ ተጨማሪ ምክንያቶች አሉ።
                    
«ሰዎች ማንንም ሳያስፈቅዱ ባካባቢዉ ይሠፍሩና ድንጋይ ማዉጣት፤ አሳ ማጥመድና መሸጥ ይጀምራሉ።ዛፉንም ይቆርጣሉ።ትላልቅ ድንጋይ እያወጡ የሚፈልጡና የሚሸጡ ኩባንዮችም አሉ።ፍሪታዉን ዉስጥ ብዙ ግንባታ አለ።አብዛኛዉ ድንጋይ የሚወጣዉ ከዚሕ አካባቢ ነዉ።ዛፉ በመቆረጡ እና ድንጋዩ በመዉጣቱ አፈሩን የሚይዘዉ የለም።ዝናብ ሲጥል በቀላሉ ይደረመሳል።»
የሴራሊዮን መንግሥት አደጋዉ መድረሱን ለሕዝብ ያስታወቀዉ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ነዉ።ለጉዳተኞች ድጋፍና ርዳታ እንዲደረገም ጥሪ ያስተላለፈዉም ትናንትናዉኑ ነዉ።ጋዜጠኛዉ በመንግሥት እርምጃ «በጣም ረክቻለሁ» ይላል።
                          
«ከመንግሥት እስካሁን ባየሁት እርምጃ በጣም ተደስቻለሁ።እንዲሕ ዓይነት ነገር ሲደረግ የመጀመሪያዉ ነዉ።አደጋዉን ለዓለም ያሳወቀዉ መንግሥት ራሱ ነዉ።የምክትል ፕሬዝደንቱ ቢሮ በጠራዉ ጋዜጣዊ ጉባኤ ነዉ ለዓለም ያሳወቀዉ።ለወትሮዉ እንዲሕ ዓይነት ነገር ሲያጋጥም ባሥልጣናት ደንታ የላቸዉም።»
በአደጋዉ የተጎዱትን ለመርዳት ዉጪ የሚኖሩ የሴራሊዮን ዜጎች ገንዘብ እያዋጡ፤ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እያሰባሰቡ ነዉ።የሲየራ ሊዮን መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት ዛሬ ጎርፍና ጭቃ የገደላቸዉ ከ350 የሚበልጡ ሰዎች አስከሬን ተገኝቷል።በአደጋዉ የሞተና የተጎዳዉን ሰዉ ትክክለኛ ቁጥር ማወቅ ግን ጋዜጠኛ አቡበከር እንዳለዉ ባጭር ጊዜ ዉስጥ አይቻልም።

Sierra Leone Überschwemmungen Erdrutsch Leichenhalle
ምስል picture-alliance/AP/Society 4 Climate Change Communication
Sierra Leone Überschwemmungen Erdrutsch
ምስል picture alliance/AP Photo/Society 4 Climate Change Communication

ነጋሽ መሀመድ

ሸዋዬ ለገሠ