1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሳይንስና ሥነ-ቴክኒክ በ 2010 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት፣

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 14 2003

በዝች ዓለም ውስጥ ከፍተኛው አስተዋይ ፍጡር፤ ሰው መሆኑ ቢታወቅም፤ ስለሚኖርባት ምድርና ስለሌሎች አጎራባች ዓለማት ፤ በአጠቃላይ ስለፍጥረተ ዓለም (ዩኒቨርስ) ያለው ዕውቀት ግን፣ ውሱን ነው።

https://p.dw.com/p/QjNW
ጀኔቭ አጠገብ፤ በትኅተ-ምድር በተገነባው የአውሮፓውያን የኑልክየር ምርምር ጣቢያ፤ምስል AP

ለዚህም ነው፣ የሳይንስ ምርምሩን አጠናክሮ በመቀጠል ላይ የሚገኘው። ፍጥረተ ዓለም ፣ በአንድ ዐቢይ ፍንዳታ(Big Bang)ከ 13,7 ቢልዮን ዓመት ዓመታት በፊት ሲከሠት ፣ የተቃርኖ ቁስ አካል የተፈጠረውም ሆነ በፍጥረተ ዓለም የሚታየው በምድራችን ላይ ያለው ህይወት ጭምር ፣ ያኔ ነው የተገኘው። ጀኔቭ አካባቢ የሚገኘው የአውሮፓውያን የኑክልየር የምርምር ድርጅት ፤ በአህጽሮት CERN) የአቶምን ድብቅ ቅንጣት ማጥመድ መቻሉን አስታውቋል። ፀረ-ቁስ አካል፣ ከሳይንሱ ማኅበረሰብ ውጭ ሰፊ ትኩረት ነው የተሰጠው። ምነው ቢሉ፤ ተዝቆ የማያልቅ ከሞላ ጎደል ዋጋ የማይከፈልበት የኃይል ምንጭ የሚያስገኝ ነውና!የአውሮፓው የኑክልየር ምርምር ድርጅት (CERN) ዋና ሥራ አስኪያጅ Rolf-Dieter Heuer የመጀመሪያው አዳዲስ ግኝቶች እየተከሠቱ ሲሆን፣ የአቶም ቅንጣቶች ጨፍላቂው ግዙፍ መግነጢሳዊ መሣሪያ(Large Hadron Collider)(LHC)ተግባር ፣ እንደታየው እ ጎ አ እስከ 2012 ዓ ም፤ መጨረሻ ይቀጥላል። የ CERN ምክትል ኀላፊ ሰርጂዎ ቤርቶሉቺ፣ LHC በምርምሩ እመርታ እያሳዬ በመሆኑ፣ በሚመጡት ወራት የፍጥረተ ዓለም (ዩኒቨርስ)25 ከመቶ ክፍል፣ የሆነውን ጽልመታዊ ቁስ አካል (Dark Matter)በተጨባጭ ሁኔታ ጠጋ ብሎ ለማየት የሚያስቸግር አይሆንም ። ጽልመታዊ ቁስ አካል፣ የፊዚክስ ሊቃውንትና የፍጥረተ ዓለም ጠበብት እንደሚያስረዱት ፣ ይህ ሥም የተሰጠው ፣ ማንኛውንም ብርሃን በፍጹም የማያንጸባርቅ ሆኖ በመገኘቱና ሊታይ የሚችል ባለመሆኑ ነው። እንደተባለው ጨለማ የዋጠው ቁስ አካል፣ በፍጥረተ ዓለም 25 ከመቶ የሚሆነውን ቦታ የሚሸፍን ነው ይባላል። እናም ይህ አካል፣ የማይታይ የኃይል ምንጭ ከተሰኘው ፍጥረተ ዓለምን 70 ከመቶ ከሚሸፍነው ጋር ምናልባት ግንኙነት ሳይኖረው አይቀርም። ምድር ላይ ሆኖ፣ በፍጥረተ-ዓለም የሚታዩት የኅዋ አካላት፣ ማለትም ፣ ፀሐያዊ ጭፍሮችና ከዋክብት ፣ ይዞታቸው 5 ከመቶ ብቻ ነው። በ CERN የሚካሄደው የፍጥረተ ዓለምን ምሥጢር ለማወቅ ጥረት የሚደረግበትና የሃይድሮጂንን በዐይን ብሌን የማይታዩ ተቃራኒ የአቶም ቅንጣቶች፣ በ LHC የማግኔት ወጥመድ ማግኘት የተቻለበት የቤተ-ሙከራ ውጤት ብሩኅ ተስፋን ማስጨበጡ ነው የተነገረለት። ከሥነ ፈለክ ጠበብት ሌላ፣ እንዲህ ዓይነቱን ምርምር ተራው ሰው እንዴት ይገነዘበዋል? የ CERN ዋና ሥራ አስኪያጅ Rolf-Dieter Heuer---

«እምቅድመ-ዓለም፣ ፍጥረተ ዓለም ፤ እንዴት ሊከሠት እንደቻለ ለመገንዘብ መጣር ማለት፣ የሚታየውን የኅዋ ክፍል ብቻ ሳይሆን፤ በአመዛኙ የማይታየውን ጨለማውን የኅዋ ክፍል፣ እንደሚያጠቃልል ማወቅ ይኖርብናል። ስለሆነም የጥንቱን- የጧቱን የሚታየውን የኅዋ ክፍል ለማወቅ ፣ የምሞክረው፣ በአንዲህ ያለ ሁኔታ ነው። በሌሊት ፣ አንጋጠው ወደ ኅዋ ቢመለከቱ ፣ ከዋክብትን ፀሐያዊ ጭፍሮችን ያያሉ። የማያንፀባርቅ ጨለማ ክፍልም ያያሉ። የማይታየው እጅግ ግዙፉ የፍጥረተ ዓለም ከፊል መሆኑ ነው። ስለሆነም ጥረታችን ፣ የማይታየውን ክፍል ፣ ልክ እንደሚታየው ክፍል ለመገንዘብ ነው።»

የሰው ልጅ ዘር ቀጣይነት እንዲኖረው ከተፈለገ፣ ባለንበት ምድር ባቻ መኖር አስተማማኝ አይደለም ፣ ሌላ ፕላኔት መፈለግ አለበት እያሉ ሲወተውቱ የቆዩት እውቁ እንግሊዛዊ የሥነ-ፈለክ ሊቅ እስቲፈን ሆኪንግ አጭር የጊዜ ታሪክ (A brief History of Time ) ከተሰኘው እ ጎ አ በ 1988 ካሳተሙት ሰፊ ተነባቢነት ካገኘው መጽሐፋቸው ሌላ ፤ እጅግ ትልቁ እቅድ(The Grand Design)በተሰኘው ቀጣይ መጽሐፍ፣ «ፍጥረተ ዓለም እንዲዘረጋ ፣ የእግዚአብሔር ተሳትፎ ተፈላጊ አልነበረም። ፍጥረተ ዓለም የስበት ኃይል ህግ ያስገኘው (የፈጠረው) ነው» ማለታቸው፣ ከሃይማኖት መሪዎች በኩል ውግዘትን ነው ያስከተለባቸው።

የሩቁን፣ በጥልቀት ለመመርመር ብዙ ገንዘብ የሚያባክኑ አገሮች፣ የምርምር ማዕከላት በአናዋ ምድር ለሚከሠቱ የተፈጥሮና ሰው-ሠራሽ ችግሮች መላ ለመሻት እስከምን ድረሰ ዝግጁ ናቸው?የምድር ነውጥ አምና በጥር ወር፣ ሄይቲን ምን እናዳደረሰባት አይዘነጋም። እሳተ ገሞራ፣ በአይስላንድ፣ ቺሌ፣ ኮሎምቢያ፤ ኤኴዶርና ኢንዶኔሺያ ህዝብ እጅግ አስጨንቆ ነበር። አስቀድሞ የሚያስጠነቅቅ መሣሪያ መትከል ቢቻልም፤ በባህር ወለል፣ በሚያጋጥም ነውጥ ሳቢያ ከሚከሠት የባህር አደገኛማዕበል (ሱናሚ) አደጋ ፈጽሞ ማምለጥ የተቻለ አይመስልም። የምድር ነውጥ፤ እጅግ ኃይለኛ የሚሰኘው ባይሆንም ፣ ከሰሞኑ ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ሆሣዕና አካባቢ፤ የተከሠተው ጥንቃቄን የግድ እንደሚል እሙን ነው። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ ምድርፊዚክስ፤ የኅዋs ምርምርና የኅዋ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኀላፊ ዶ/ር አታላይ አየለ፤ ነውጡ በስምጡ ሸለቆ አካባቢ የተከሠተ መሆኑን ከመግለጻቸውም፣ አካባቢው ለዚህ ዓይነቱ አደጋ የተጋለጠ በመሆኑ ፤ ነውጡ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው ማለታቸው ተጠቅሷል።

(ድምፅ)

2010 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት በተ መ ድ፣ የብዝኀ-ህይወት መታሰቢያ ዘመን እንደመባሉ መጠን፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎች፣ ስለምድራችን ሁለንተናዊ የአየር የውሃና የአፈር ብክለት በሰፊው ከመነገሩ በስተቀር፣ ለመፍትኄው፣ መንግሥታት፣ የሚገባቸውን ያህል ጥረት አላደረጉም። ያም ሆኖ፣ አንዳንድ የምርመራ ውጤቶች፣ ብሩኅ ተስፋ አላሳደሩም አይባልም።

በአፍሪቃ፣ 300 ሚልዮን ያህል ህዝብ፣ ንፁህ የሚጠጣ ውሃ አይገኝም። በመላው ዓለም ቁጥሩ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ነው። ታዲያ የቡብ አፍሪቃው እስቴለንቦሽ ዩኒቨርስቲ፣ ዋጋው ርካሽ የሆነ ለአንድ ብርጭቆ ሻይ የሚውል ንዑስ የሻይ ከረጢት በሚያክል በፕላስቲክ መሰል ንዑስ ከረጢት የሚታሸግ የላመ ጥቁር ድንጋይ የሚመስል ማዕድናዊ የውሃ ማጣሪያ ቅመም በማዘጋጀት ለገጠር ኑዋሪዎች ሁሉ የሚጠቅም የውሃ ማጣሪያ አቅርቧል ።

በሌላ በኩል በተፈጥሮ ሳይንስ በመመካት ፣ ውሃን «ከጉም እንደ ወተት ማለብ» የተሰኘው ፈሊጥ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ዐቢይ ትርጉም እየተሰጠውና ግንዛቤም እየተገኘበት መጥቷል። እ ጎ አ ከ 2988 ዓ ም ወዲህ፣ በዚህ ርእስ ዙሪያ የሚመክር ፤ ዓለም አቀፍ ጉባዔ በ የ 3 ዓመት አንድ ጊዜ የሚመክር ሲሆን፤ ከቫንኩቨር፣ ሴንት ጆንስ፤ ኬፕታውንና ላ ሳሬና ወዲህ፣ ባለፈው ሐምሌ፤ 18-23 , 2002 ሙዑንስተር በተባለችው የጅርመen የዩኒቨርስቲ ከተማ ተካሂዷል። ከጉምና ጤዛ ውሃ እንዴት በተሻለ ዘዴ ሊጠራቀንም እንደሚችል፤ 140 ዓለም አቀፍ ጠበብት ነበሩ፤ ለ 6 ቀናት የመከሩት ። ውሃን፤ ከጉም የማጠራቀሙ ሃሳብ፣ በተለይ ምድረ-በዳ ያላቸውን አገሮች ነው ይበልጥ ያጓጓው። ከማይጨበጠውደመና ፣ ሆኖም፤ አልፎ-አልፎ ዝቅ በማለት የብስንና ባህርን ከሚሸፍን ንፁህ የሚጠጣ ውሃ፣ ችግርን ለማስወገድ አንዱ ብልሃት፣ ጨው የበዛበትን የውቅያኖስ ውሃ እያጣሩ ማቅረብ ሲሆን፤ በዚህ ረገድ ብሪታንያ የመሪነቱን ሥፍራ መያዝ የሚያስችል እርምጃ በመውሰድ ላይ ናት። በዚህ ረገድ የምትጠቀምበት ሥነ-ቴክኒክም፤ ለአውሮፓም ሆነ ለሌሎች አርአያነት ይኖረዋል እየተባለ ነው። እ ጎ አ በ 2021 የለንደን ህዝብ ቁጥር 700,000 ጭማሪ እንደሚያሳይ የተነበየው «ዘመናዊ ውሃ(Modern Water)የተሰኘው ኩባንሪያ በዖማን ያካሄደው የ 6 ወራት ሙከራ አጥጋቢ ውጤት ማስመዝገቡን በመግለጽ በቀላል ወጪ ጨው የበዛበትን የውቅያኖስ ውሃ ማጣራት የሚቻልበት ዘመናዊ ሥነ-ቴክኒክ መኖሩን አሥመስክሯል ነው የተባለው። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ፣ በቀን 68 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ነው ጨው ከበዛበት ውሃ ማጣራት የሚቻለው። እ ጎ አ በ 2016 ወደ 130 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ከፍ ማድረግ እንደሚቻል፤ ዓለም አቀፍ የሚጠጣ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ መጽሔት አሳታሚ ክርስቶፈር ጌሰን ይናገራሉ። የዓለም የዱረ ዐራዊትና እንስሳት ጥበቃ ድርጅት ግን፣ የመጀመሪያው አማራጭ ውሃን ሳያባክኑ በቁጠባ መጠቀም ይገባል ሲል ይመክራል። ጥቅጥቅ ያለ ጉም በሚከሠትባቸው ወቅቶች፤፣ በማጥመጃ የፕላስቲክ መረብ አማካኝነት በቀን 170 ሊትር ያህል ጥራት ያለው ንፁህ የሚጠጣ ውሃ ማጠራቀም እንደሚቻል ኤርንስት ፎርስት የተባሉ የጀርመን የውጃሃ ልማት ድርጅት ባልደረባ አስረድተዋል።

በተለያዩ የሳይንስ ዘርፎች፤ የሚደረገው ምርምር ምንጊዜም እንደቀጠለ ሲሆን፣ ሊያከትም 9 ቀናት በቀሩት 2010 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት ከተፈለሰፉት የሥነ ቴክኒክ ውጤቶች ጥቂቶቹንና ዋና- ዋናዎቹን እንጥቀስ ።

በመጀመሪያ በ 50ኛው የበርሊኑ ዓለም አቀፍ የመገናኛና የመዝናኛ የቤት ዕቃዎች ትርዒት ለአይታ ከቀረቡት ጥቂቶቹን እናስታውሳችሁ።

(ድምፅ)

ሌላው፤ «ጉግል» የሠራው Apple iPhone ለተሰኘው አማራጭ ሆኖ የቀረበው Android Phone የሚሰኘው ነው።

ባለፈው መጋቢት የአሜሪካው የኅዋ ምርምር መ/ቤት የፈለሰፈው ኬፕለር የኅዋ የሩቅ መነጽር፤ ርዝማኔው ከ 3 ጫማ ትንሽ ቢበልጥ ነው፤ ከ 600-3,000 የብርሃን ዓመት ርቀት ያላቸውን ምድር መሰል ፕላኔቶችን በሚገባ የሚያስስ ነው።

የኤሌክትሪክ ዐይን (Electric Eye)

ለዐይነ ሥውራን በከፊል የዐይን ብርሃን የሚሰጥ ነው። በዐይን መነጽር ቅርጽ ተሠርቶ፣ ካሜራ የተገጠመለት ነው። በ«ቲታንዬም» የተሸፈነው ንዑስ ባትሪ መሰሉ መሣሪኢ፣ ከካሜራ የሆነ ምስል ሲቀርብለት በዐይን ብሌን ነጸብራቅ በመፍጠር፤ የማየት ተግባር ያላቸውን ነርቮች ያነቃቃል። በ2010 ጎርጎሮሳዊ ዓመት ከተፈለሰፉት እጅግ ጠቃሚ መሳሪያዎች አንዱ ይህ ነዉ።

ሌላዉ ሰነዶች ከአንድ የዓቶም ቅንጣት ወደሌላ የሚሸጋገሩበት ስነቴክኒክ TELEPORTATION የተሰኘዉ ሲሆን ይህም አስተማማኝና ፈጣን የኮምፕዩተር ዓይነቶችን ለማስተዋወቅ ወሳኝነት ያለዉ እጅግ ጠቃሚ የፈጠራ ዉጤት መሆኑ ተመሥክሮለታል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ