1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኛው ሣይንቲስት በጀርመን

ረቡዕ፣ ጥቅምት 3 2008

ጦርነት፣ መከራ እና ሰቆቃን ሸሽተው ወደ ጀርመን ከሚመጡ ስደተኞች መካከል ሣይንቲስቶችም ይገኙበታል። ስደተኞቹ ጀርመን እንደገቡ በቅድሚያ እንዲረጋጉ ይደረጋል። እናም አስፈላጊውን ሕክምና ካገኙ በኋላ ጥያቄዎች ይከተላሉ።

https://p.dw.com/p/1GmxM
Dr. Muhammad Rashid mit Kindern im Garten
ምስል privat

ስደተኛ ሣይንቲስቶች በጀርመን

ከጥያቄዎቹ ውስጥ ጀርመን ምን ምን መሥራት እችላለሁ የሚለው አንዱ ነው። ይህ ጥያቄ ከከፍተኛ ተቋማት የተመረቁ ምሁራን እና ሣይንቲስቶችንም የሚመለከት ነው።

ሙሐማድ ራሺድ እጅግ ከፍተኛ ብቃት ካላቸው የሶሪያ ስደተኞች አንዱ ነው። የኩርድ ዝርያ ያለው ይኽ ሶሪያዊ ሣይንቲስት ተወልዶ ያደገው፣ ከአንደኛ ደረጃ አንስቶ በሥነ-ቅመማ ትንታኔ ዲፕሎማ እስኪያገኝ ድረስ የተማረው እዚያው አሌፖ ውስጥ ነው። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2004 የሶሪያ መንግስት ለዶክትሬት ዲግሪው ከፍተኛ ሥልጠና እንዲያገኝ ወደ ቻይና ይልከዋል። በቻይና የከፍተኛ ትምህርት ቆይታው ያስመዘገበው ውጤት እጅግ አመርቂ ነበር። የኩርዶች መኖሪያ በሆነው የሶሪያ ግዛት አለመረጋጋት በነገሰበት በዚያን ጊዜም እንኳ ያስመዘግብ የነበረው ውጤት ድንቅ ነበር።

«ቻይና እያለሁ ወደ ሀገሬ ሶሪያ መመለስ አልችልም የሚል ሐሳብ ፈፅሞ በውስጤ አልነበረም። በእውነቱ ዶክትሬቴን ከያዝኩ በኋላ ብመለስ ኖሮ ጥሩ ሥራ ተዘጋጅቶ ሳይጠብቀኝ አይቀርም ነበር።»

Laborantin selektiert Pflanzenkeime
ምስል DW/F. Schmidt

ሆኖም ግን ለሰባት ዓመታት ከሀገሩ ርቆ ይከታተል የነበረው የዶክትሬት ትምህርቱ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ ሀገሩ ሶሪያ በእርስ በእርስ ግጭት ትዘፈቃለች። በዚያኑ ወቅት ሙሐማድ ሕይወት ውስጥ ሌላ አሳዛኝ ነገር ይከሰታል። ሩቅ ተጉዛ በሰው ሀገር አብራው ብዙ ነገሮችን ያሳለፈችው ባለቤቱ እጅግ ኃይለኛ በሆነ ነቀርሳ ትታመማለች። በስድስት ወራት ቆይታ ብቻ ሕይወቷ ያልፋል። የዚያን ጊዜ የነመሐሙድ ወንድ ልጅ ሰባት ዓመቱ ነበር፤ ስድስቱን ዓመት የኖረው ቻይና ውስጥ ነው።

ታናሺቱ ግን እዛው ቻይና ውስጥ ነው የተወለደችው። ለሦስቱ ወደ ሀገር ቤት ሶሪያ መመለስ ፈፅሞ የማይታሰብ ነበር። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2011 የሙሐማድ ራሺድ ወንድም ከሶሪያ ጦር ሰራዊት አፈንግጦ የተሰወረበት ዓመት ነበር። እናም በወንድሙ መጥፋት የተነሳ ሙሐማድ ወደ ሶሪያ ፈፅሞ መመለስ አይችልም ነበር።

«ወንድሜ ከሲቪሎች በተቃራኒ ቆሞ መዋጋት አልፈለገም ነበር። እናም ስሜ መዝገብ ውስጥ መስፈሩን ከጓደኞቼ ሰማሁ። ቻይና ሳለሁ የትምህርት ወጪዬን የሚሸፈንልኝ ከሶሪያ ነበር። ከዛ በኋላ ግን የሶሪያ መንግሥት ከእንግዲህ ለአንተ ገንዘብ የሚባል ነገር የለም አለ። ለፈጣሪ ምሥጋና ይግባውና ለመጨረሻ ዓመት ወጪዬ የቻይና መንግሥት ገንዘብ ሰጠኝ። እናም ዶክትሬቴን አጠናቀቅሁ።»

እንደ ሙሐማድ ራሺድ ሁሉ በርካታ የሶሪያ ተማሪዎች ጀርመን ውስጥ ይኖራሉ። በምኅፃሩ ዳድ (DAAD )በመባል የሚታወቀው፦ የጀርመኑ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ልውውጥ አገልግሎት ተቋም ከመንግሥታት ጋር በመተባበር በሚሰጠው የትምህርት ዕድል ሶሪያውያኑም ተጠቃሚዎች ናቸው። ይሁንና በ2011 ዓም የእርስ በርስ ጦርነቱ ሶሪያ ውስጥ ሲፈነዳ የከፍተኛ ትምህርት ተከታታዮቹ በቀጥታ ወደ ጀርመን ይመጣሉ።

በምኅፃሩ ዳድ (DAAD )በመባል የሚታወቀው፦ የጀርመኑ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ልውውጥ አገልግሎት ተቋም
በምኅፃሩ ዳድ (DAAD )በመባል የሚታወቀው፦ የጀርመኑ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ልውውጥ አገልግሎት ተቋም

ዳድ በወቅቱ ለዚህ ብሎ ያዘጋጀው ገንዘብ አልነበረም፤ ግን ደግሞ ጀርመን የመጡትን እጅግ የሰለጠኑ የሶሪያ ስደተኞች ሜዳ ላይ ሊጥላቸውም አልፈለገም። እናም የጀርመን መንግሥት ጦርነቱን ሸሽተው ለመጡት የከፍተኛ ትምህርት ተከታታይ ስደተኞች ለየት ያለ ርዳታ መርሐ-ግብር በማዘጋጀት አብዛኛዎቹ ትምህርታቸውን በስኬት እንዲያጠናቅቁ ማድረጉን ክርስቲያን ኹዩልሾዮርስተር ይገልጣሉ።

የዳድ የመካከለኛው ምሥራቅ መርሐግብር ኃላፊው ክርስቲያን ኹዩልሾዮርስተር ለየት ያለ ርዳታ ያገኙት ተማሪዎች በመላው ዓለም የሚፈለጉ መሆናቸውን ገልጠዋል። የሶሪያ የትምህርት ሥርዓት ምርጥ ምርጦቹን ወደ ውጭ ሰዷል ማለት ይቻላል።

«በጣም ጎበዝ የሆኑት ወደ ሕክምናው ዘርፍ፣ ምህንድስናው አለያም የተፈጥሮ ሣይንስሱ ይገባሉ። ሶሪያ ውስጥ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ብቃት ያላቸው መሀንዲሶች፤ በምንሰጠው የትምህርት ዕድል መርሐ-ግብር ተጠቅመው ደረጃውን የጠበቀ ማስተርስ ከሠሩ፤ በኋላ ላይ ሥራ ያገኙ ይሆን የሚለው ብዙም አያስጨንቀኝም።»

ጀርመን ውስጥ ለሚኖሩት የከፍተኛ ትምህትርት ተከታታይ ሶሪያውያን ተማሪዎች ዳድ አዲስ መርሐ-ግብርም ጀምሯል። ሶሪያውያኑ ጀርመን ከመምጣታቸው አስቀድሞ የትኛውም ሀገር ይኑሩ የት ለሶሪያ የአመራር ሥልጠና በተሰኘው መርሐ-ግብር መሳተፍ ይችላሉ። መርሐ-ግብሩ በገንዘብ የሚደገፈው በጀርመን ውጭጉዳይ መሥሪያ ቤት ነው።

የጀርመንኛ ቋንቋ ትምህርት
የጀርመንኛ ቋንቋ ትምህርትምስል picture-alliance/dpa

ከሶሪያ ፈልሰው ዮርዳኖስ ውስጥ ለሚገኙ ሣይንቲስቶች እና የከፍተኛ ትምህርት ተከታታዮች እዛው ባሉበት ዩኒቨርሲቲ የከፍተኛ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁበትንም መንገድ ዳድ አመቻችቷል።

ጀርመን ውስጥ የሚገኘው ፍራውንሆፈር ጌዜልሻፍት(Frauenhofer-Gesellschaft) የተሰኘው ማኅበር በበኩሉ በሣይንሱ እና በምርምሩ ዘርፍ እጅግ በከፍተኛ ደረጃ የትምህርት ብቃት ያላቸው ሶሪያውያንን መፃዔ ጀርመን ውስጥ ለማመቻቸት ጥረት ያደርጋል። ሙይንሽን የሚገኘው የምርምር ተቋም ይኽን ዕቅድ ስኬታማ ለማድረግ የሰው ኃይል እንዳደራጀ የተቋሙ ባልደረባ ቤአተ ኮህ ይናገራሉ።

«በአንድ መልኩ ትኩረት የምናደርገው በሥራው ዓለም ልምዳቸውን ከፍ ለማድረግ የሚሹ ሠልጣኞችን ነው። በአሁኑ ወቅት በተለይ አዲስ ሠልጣኞችን የሚመለከት የገንዘብ ድጋፍ የምናገኝበትን መስመር እያበጀን ነው። በሌላ መልኩ ደግሞ በእርግጥም በሥራው መስክ ለመሰማራት ቀድሞውንም ብቃት ያዳበሩ ግን ደግሞ ከሥራው ጋር የበለጠ ለመዋሀድ የሚፈልጉትም ላይ እናተኩራለን። ለአብነት ያህል በፍራውንሆፈር የምርምር ተቋም ወይንም ሌላ ቦታ በሚገኝ የሣይንስ ምርምር እንዲሳተፉ እናደርጋለን። »

ሶሪያዊው ስደተኛ ሣይንቲስት ሙሐማድ ራሺድ ከፍራውንሆፈር በርካታ የምርምር ተቋማት ውስጥ በአንዱ እግሩን መትከል ይፈልጋል። ከሁለት ዓመታት በፊት ነበር የዶክትሬት መመረቂያ ጽሑፉን ቻይና ውስጥ እንዳጠናቀቀ ወዲያውኑ ወደ ጀርመን የመጣው። ፈተናው ካለፈ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ነበር በፍራንክፉርት አንድ የሣይንስ ውይይት ላይ እንዲሳተፍ የተጋበዘው። ልጆቹን ወደ ጀርመን ለማስመጣት የቻለው ግን ከስድስት ወራት የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ በኋላ ነው።

ዶ/ር ሙሓማድ ራሺድ እና ሁለት ልጆቹ
ዶ/ር ሙሓማድ ራሺድ እና ሁለት ልጆቹምስል privat

ይኽን ሁሉ ውጣ ውረድ አሳልፎም ቢሆን የዶክትሬት ማዕረጉ ጀርመን ውስጥ ዕውቅና እንዲሰጠው በመታገል ላይ ይገኛል። ያ እስኪሳካ ድረስም ጀርመን ውስጥ በዶክትሬት ማዕረጉ መጠቀም አይፈቀድለትም። ሆኖም ለዶክትሬት ማዕረጉ በሠራው ምርምር ተወዳድሮ ሥራ መቀጠር ይችላል። ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አለያም ትልልቅ መሥሪኢ ቤቶች ውስጥ ሥራ አግኝቶ ለመቀጠር እየጣረ ነው።

«ለጀርመኖቹም ሥራ መፈለጉ ቀላል እንደማይሆን እገምታለሁ። ፋብሪካዎች ውስጥ ለመቀጠር አመልክቼ ነበር እስካሁን ግን የሚደርሰኝ መልስ ማመልከቻዬ ውድቅ መሆኑን የሚገልጽ ብቻ ነው። አሁን ግን ከሚቀጥለው ሣምንት አንስቶ ቦን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በውኃ ዘርፍ የተከፋይ ሰልጣኝ ሥራ ቦታ አግኝቻለሁ።»

በሥነ-ቅመማ የትንታኔ ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪ የያዘው ሶሪያዊው ሣይንቲስት ሙሐመድ ራሺድ በአሁኑ ወቅት የጀርመንኛ ቋንቋ ለመልመድ ትግል ገጥሟል።

«ቋንቋው አስቸጋሪ ነው፤ ግን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ምርምር ስጀምር ጀርመንኛ ብዙ ጀርመንኛ ቋንቋ የሚያስፈልገን አይመስለኝም። ምናልባት የምርምር ጽሁፌን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፌ አሳካው ይሆናል።»

ልጆቹን ለብቻው ለሚያሳድገው ሣይንቲስት አባት አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው። ወደ አሌፖ የሚመለስበት መንገድ ተዘግቷል። ልጆቹ ሶሪያን አያውቋትም። በአንድ ዓመት ቆይታ ብቻ እንኳን ጀርመን መኖራቸው እንደቤታቸው ተሰምቷቸዋል። ወንድዬው ልጅ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስድስተኛ ክፍል ገብቷል። ታናሽ እህቱ ሁለተኛ ክፍል ናት። ጀርመንኛ ለሁለቱ ልጆች ከሣይንቲስት አባታቸው በበለጠ ይቀላቸዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ