1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞችን ለመታደግ የቆረጡት ጀርመናዊ ካፒቴን

Eshete Bekeleዓርብ፣ ጥቅምት 26 2008

የንግድ መርከብ ካፒቴን የነበሩ ጀርመናዊ የሜድትራኒያንን ባህርን በአደገኛ ሁኔታ በማቋረጥ ወደ አውሮጳ ለመግባት ሲሞክሩ አደጋ ላይ የሚወድቁ ስደተኞችን በግል መርከብ ለመታደግ ለመታደግ ተስፋ አድርገዋል። ጥረታቸው ሙሉ በሙሉ ከለጋሾች እና ሃሳባቸውን ከሚደግፉ ሰዎች በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ነው።

https://p.dw.com/p/1H1J9
Rettungsaktion von Ärzte ohne Grenzen Mittelmeer
ምስል DW/K. Zurutuza

[No title]

የአውሮጳ መገናኛ ብዙሃን ላለፉት ወራት በየቀኑ ማለት በሚቻል ደረጃ አንድን ጉዳይ ሲዘግቡ ከርመዋል። አውሮጳን ያሳሰበው የተገን ጠያቂዎችና ተሰዳጆች ቀውስ።

ጋዜጠኞቹ ሁኔታው ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ መሆኑን ይናገራሉ። በየአገሮቻቸው የተፈጠረውን አለመረጋጋትና ጦርነት ለመሸሽ የሞከሩ ከ3,000 በላይ ሰዎች ከጥር ወር ጀምሮ በሜድትራኒያን ባህር ሰጥመው መሞታቸውን የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) አስታውቋል። የድርጅቱ ቃል -አቀባይ ጆዔል ኒልማን «ሁኔታው መሻሻል ለማሳየቱ ምልክት የለም። የአየር ሁኔታው ሲቀዘቅዝ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አሳስቦናል።»ሲሉ ተናግረዋል።

ሴቶች፤ ወንዶችና ሕጻናትን ከአቅማቸው በላይ የጫኑና ደረጃቸውን ያልጠበቁ ጀልባዎች በደቡባዊ አውሮጳ በብዛት እየታዩ መሆኑን ኒልማን ጨምረው ተናግረዋል። ሁኔታው የተባባሰው ስደተኞችን የመታደግ ሥራ ሲከውን የነበረው « ማሬ ኖስትሩም» የተባለው ግብረ ኃይል በሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ ምክንያት ተግባሩን ካቆመ በኋላ ነበር። ውሳኔዉን ተከትሎ የተፈጠረው ቀውስ የቀድሞው የንግድ መርከብ ካፒቴን ክላውስ ቮገል «ኤስኦኤስ ሜድትራኒያን» የተሰኘውን ሥራ ለመጀመር ወሰኑ። ክላውስ ቮገል ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ከለጋሾች በሚያገኙትና ክራውድ ፈንዲግ ተብሎ በሚጠራው የድረ-ገጽ ገንዘብ መሰብሰቢያ ለመደጎም አቅደዋል።

Pressebilder MOAS EINSCHRÄNKUNG
ምስል MOAS/Darrin Zammit Lupi

« ገንዘቡን ከብዙ ሰዎች እንሰበስባለን። የክራውድ ፈንዲግ ዘመቻ አለን። ከሶስት ሺህ በላይ ሰዎች የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉልን ሲሆን አሁንም በሜድትራኒያን ባህር ላይ የሚደረገውን የመታደግ ተግባር ለመደገፍ ፈቃደኛ ከሆኑ ሰዎች ሁሉ እንሰበስባለን።»

የ51 ዓመቱ ጀርመናዊ በመርከባቸው ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን በማካተት የሜድትራኒያንን ባህር ለማሰስ አቅደዋል። በፍለጋቸው ለአደጋ የተጋለጡ ስደተኞችን በመጫን ደህንነታቸው ወደሚጠበቅበት ያደርሳሉ። እቅዱ አንድ ጊዜ ከተጀመረ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለመታደግ ያስችላል። በመርከቡ ላይ ሆስፒታል ሁሉ ይኖረዋል። የኢኮኖሚ ባለሙያው ቶማስ ፒኪቲ ከሃሳቡ ጅማሮ አንስቶ ተሳትፎ እያደረጉ ነው።

ፒኪቲ «አውሮጳ ስደተኞችን ለመቀበል በርካታ መንገዶች አሏት ብዬ አምናለሁ። ራስ ወዳድ መሆን የለብንም። በተለይ ደግሞ ከዚህ ቀደም ስደተኞችን ለመቀበል የነበረንን ችሎታና መልካም ፈቃድ ስናስብ። ከ2008ቱ የፋይናንስ ቀውስ በፊት አውሮጳ በዓመት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችን ትቀበል እንደነበር ለሰዎች ማስታወስ እፈልጋለሁ። »በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የክላውስ ቮገል እቅድ በመጪው ታህሳስ ወር ሲጀመር በዋንኛነት በሊቢያና ኢጣሊያ መካከል በሚገኘው የዓለም አቀፍ የውሃ ክልልና በሚፈለግበት ሁሉ የሚሠራ ይሆናል።

«በመርከባችን በተቻለ ፍጥነት እንንቀሳቀሳለን። አስር ሠራተኞችና ስድስት የህክምና ባለሙያዎችና ጥቂት የመታደጉን ሥራ የሚሠሩ ተጨማሪ ሰዎች አሉት። ከደቡባዊ ሲሲሊ የምንነሳ ሲሆን በክረምቱ በሙሉ ሰዎችን እንታደጋለን። በጀርመንና ፈረንሳይ በሚገኙ ሲቪል ማህበራት ድጋፍ ይደረግልናል። ሰዎች ይህ ተግባር አስፈላጊ መሆኑንና ሰዎችን ለመታደግ ደግሞ የፖለቲካ ውይይት መጠበቅ እንደሌለብን ያውቃሉ።»

በዚህ ዓመት ወደ ግሪክ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አሻቅቧል። አስቸጋሪው የሜድትራኒያን የክረምት ወቅት እየደረሰ ቢሆንም አገራቸውን ጥለው ወደ አውሮጳ የሚገሰግሱት ግን በአስቸጋሪው የአየር ሁኔታና አሰቃቂ ጉዞ አልተገቱም። ብዙዎቹ ጀልባዎች በኃይለኛ ንፋስና ማዕበል ይዋጣሉ። ባለፈው ወር በአንድ ቀን ብቻ 85 ውሽልሽል ጀልባዎች ሌስቦስ ከተሰኘው ስ ከተሰኘው የግሪክ ደሴት ደርሰዋል።

Rettungsaktion von Ärzte ohne Grenzen Mittelmeer
ምስል DW/K. Zurutuza

«ይህ ለወደፊት ለሲቪል ማህበራትም ጥሩ እድል ነው። በሜድትራኒያን ጉዳይም እርስ በርሳቸው ለሚቆራቆሱ አገራት ጥሩ ነው።» የሚሉት በብራስልስ በእቅዱ መደበኛ ያልሆነ ውይይት ሲደረግ የተሳተፉት የጀርመን ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲና የፓርላማ አባሉ አርኒ ላይት ናቸው። ፖለቲከኛው ይህ እቅድ «ስደተኞችን ከባህር ላይ በመታደጉ ጥረት የዜጎች ሲቪል ማህበራት ተሳትፎ ሲያደርጉ ዘላቂ ጥምረት ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ።»ሲሉም ተናግረዋል።

ኤስኦኤስ ሜድትራኒያን የተባለውን የክላውስ ቮገል እቅድ ሥራ ላይ ለማዋል 1.2 ሚሊዮን ዩሮ ያስፈልጋል። እስካሁን ከሚያስፈልገው ገንዘብ ግማሽ ያህሉ ብቻ የተሰበሰበ ቢሆንም ካፒቴን ቮገል በቅርቡ እንደሚጀመር ባለሙሉ ተስፋ ናቸው።

እሸቴ በቀለ/ኔተን ሞርዚ

ሸዋዬ ለገሰ