1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞች በግሪክና መቂዶንያ ድንበር-ኢዶሜኒ

ዓርብ፣ የካቲት 25 2008

በግሪክና በመቂዶንያ ድንበር ኢዶሜኒ በሚባለዉ ቦታ ላይ ከ 10 ሺህ በላይ ስደተኞች ሰፍረዉ ይገኛሉ። መጠለያም ተሰርቶላቸዉ እየኖሩ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1I7Rp
Griechenland Flüchtlinge an der Grenze zu Mazedonien bei Idomeni
ምስል Reuters/M. Djurica

[No title]


የዶቼ ቬለዋ ካሪን ዜንስ ተዘዋዉራ እንዳየችዉ የስደተኞቹ የአኗኗር ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶአል። ከሁሉም በላይ በሽዎች ለሚቆጠሩ ስደተኞች የሚሆነዉን ምግብ ቀቅሎና አሰናድቶ ማደል እንዲሁም የመፀዳጃና የመሳሰሉት ችግሮች ፤ በጤና ላይ ሁሉ ቀዉስ እያስከተለ መሆኑ ተዘግቦአል። ይህንም ሁኔታ የርዳታ ሰጭ ክፍሎች ተገንጥበዉ ማስጠንቀቅያ አስተላልፈዋል። የካሪንን ዘገባ የበርሊኑ ወኪላችን አዘጋጅቶታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዉሮጳ ኅብረት ለቱርክ 95 ሚሊየን ዩሮ ርዳታ ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ። ቱርክ ይህን የገንዘብ ርዳታ ከኅብረቱ የምታገኘዉ ወደአዉሮጳ ለመሻገር የሚመኙ ስደተኞችን ከድንበሯ እንዳያልፉ ለማገድ በገባችዉ ዉል መሠረት ነዉ። ኅብረቱ ዛሬ ገንዘቡን ለመስጠት መዘጋጀቱን ይፋ ቢያደርግም ዘገባዎች እንደሚሉት ግን ቱርክ እስካሁን ቃል በገባችዉ መሠረት የሚተመዉን የስደተኞች ጎርፍ በአግባቡ አላገደችም የሚለዉ ስጋት እንዳለ ነዉ። የኅብረቱ የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር ዲሚትሪ አብራምፖሎስ አዉሮጳ ይህን ችግር ለመፍታት ቱርክን እንደሚፈልጋት ብራስልስ ላይ ዛሬ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ኅብረቱ ለአንካራ ከሚሰጠዉ ገንዘብ 55 ሚሊየኑ ቱርክ ዉስጥ የሚገኙ ሶርያዉያን ወጣቶች መደበኛ ትምህርት ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ነዉ። ቀሪዉ ገንዘብ በዓለም የምግብ መርሃግብር በኩል 735ሺህ የሚገመቱት የሶርያ ስደተኞች የምግብ እርዳታ እንዲቀርብ እንደሆነም ተገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለም የሶርያ ድንበር ላይ የምትገኘዉ ኪሊስ የተሰኘች የቱርክ ከተማ ከኗሪዎቿ ቁጥር በላይ ሶርያዉያን ስደተኞችን በሰላማዊ መንገድ በማስተናገዷ የኖቤል ሽልማት ሊሰጣት እንደሚገባ ከንቲባዋ እያሳሰቡ ነዉ። የኪሊስ መደበኛ ኗሪዎች 90ሺ ሲሆኑ 120 ሺህ የሶርያ ስደተኞችን እያስተናገደች እንደሆነ ተገልጿል። በቱርክ ምክር ቤት የገዢዉ AKP ፓርቲ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አይሃን ሰፈር ዑሽቱን ጥያቄዉን በይፋ አቅርበዋል።

Griechenland Idomeni by Night Group tents
ምስል DW/D. Cupolo

«ኪሊስ በእዉነቱ መልካም ነገሮች የሚደረጉባት ከተማ ናት፤ የሰላም እና የወንድማማችነት ከተማ ናት። ይህ መልካምነት የሰላም የኖቤል ሽልማት ዘዉድ ቢደፋ ብለን እንመኛለን።» ከከተማዋ ኗሪዎች አንዱ በበኩላቸዉ ኪሊስ ዉስጥ ስላለዉ መረጋጋት እንዲህ ይላሉ። በአራት የተለያዩ ቦታዎች አመፅና አለመረጋጋት ነበር፤ ኪሊስ ግን ይህ የለም። እንዲህ ያለ ነገር እንዳይከሰት በምንችለዉ ሁሉ ለመከላከል እንሞክራለን።»


ይልማ ኃይለሚካኤል / ሸዋዬ ለገሠ


አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ