1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞች፤ አዉሮጳና አፍሪቃ

ሐሙስ፣ ጳጉሜን 5 2007

ብዙ ኬንያዉያን ጀርመኖችን የዉጪ ሰዉ ይጠላሉ ብለዉ ያምናሉ።ያሁኑ የጀርመን እርምጃ፤ ኦዊኖ እንደሚሉት ግን የጀርመንን ነባር ገፅታ ለመለወጥ ጠቃሚ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1GUgk
ምስል picture-alliance/dpa/D. Kurokawa

[No title]

ዉሮጳ ጦርነት፤ ጭቆናና ድሕነት ከጠናባቸዉ አካባቢዎች በሚሸሸዉ ስደተኛ «መጨናነቅዋ» በተደጋጋሚ እየተነገረ ነዉ።ከዓለም ትልቁ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ የሚገኘዉ ግን አዉሮጳ አይደለም።ዳዳዓብ-ኬንያ እንጂ።ሰሜን ምሥራቅ ኬንያ በሚገኘዉ በዚሕ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሶማሊያዉን ጦርነት የሸሹ 650 ሺሕ ስደተኞች ሠፍረዋል ተብሎ ይገመታል።የዶቸ ቬሌዋ አንትየ ፓሰንሐይም እንደዘገበችዉ ርዕሠ-ከተማ ናይሮቢ ዉስጥም በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የሶማሊያ ዜጎች ይኖራሉ።የፓሰንሐይምን ዘገባ ነጋሽ መሐመድ እንደሚከተለዉ አሰባስቦታል።

ጀርመናዊት ናት።ጋዜጠኛ።«ናይሮቢ ዉስጥ» ትላለች የሰሞኑ ገጠመኟን ስትፅፍ-ወተት ለመግዛት ኪዮስክ ልገባ፤ ገበያ አዳራሽ ወይም ትምሕርት ቤት ልጎብኝ-ሁሉም አንድ ነገር ይጠይቀኛል፤«ጀርመናዊ ነዎት» እያለ።ሁሉም አንድ አስተያየት ይሰጠኛል «ብዙ ስደተኛ እያስተናገዳችሁ ነዉ---አይደል» የሚል።

የተማሪ ማይክም አስተያየት የተለየ አልነበረም።«የጀርመኗ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሥደተኞችን ለመቀበልና ለመርዳት ቃል መግባታቸዉን በዜና ሰምቼያለሁ።እዚሕ የምንኖረዉ በብዙ ስደተኞች መሐል በመሆኑ ጀርመኖች የሚሰማቸዉን በትክክል እንረዳዋለን።» እያለ ቀጠለ።ማይክ።

Flüchtlingslager Dadaab Kenia
ምስል AP

የጀርመን ጋዜጠኞች ግን ሥለ ትልቁ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ፤ እነማይክን ሥለከበቡት ስደተኞች ወይም ሥለነማይክ ኑሮ ብዙም ሲዘግቡ አይደመጡም።

የአስራ-ሰባት ዓመቱ ወጣት የሚኖረዉ ኢስትሌግሕ በተሰኘዉ የናይሮቢ መንደር ነዉ።መንደሩ «ትንሿ ሞቃዲሾ» በሚል ቅፅልም ይታወቃል።የሶማሊያ ስደተኞች መገበያያም ነዉ።ከግመል ሥጋ እስከ ክላሺንኮቭ ጠመንጃ---የሌለ ነገር የለም።በአስር ሺሕ የሚቆጠሩ የሶማሊያ ስደተኞች እዚያ ይኖራሉ፤ ይሰራሉ፤ ይሸጣሉ-ይለዉጣሉም።

አንዳድ ኬንያዉያን ኢስትልግሕ ብዙ አይወዱትም ይባላል።ማይክ ግን መዉደዱን እንጂ መጥላቱን አያዉቅም።

«ጎረቤቴ ሥደተኛ ነዉ።ልክ እንደወንድማማቾች ነን።ከሌላ ሐገር ሥለመጣ ዝቅ አድርጌ አልመለከተዉም።የሱ ጥፋት አይደለም።መቻቻል አስፈላጊ ነዉ።»

ARD የተሰኘዉ የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ የናይሮቢ ቅርንጫፍ ሾፌር ቪክቶር ኢትዮንጎ ደግሞ አንዳድ የአዉሮጳ መንግሥታት ስደተኞች ወደ ሐገራቸዉ እንዳይገቡ የከለከሉበት ምክንያት አይገባቸዉም።

እርግጥ ነዉ ስደተኞች ልክ እንደ ትምሕርት ቤት የሚስተናገዱበት ደንብ ሊኖር ይገባል ይላሉ ኬንያዊዉ ሾፌር፤ ግን ኬንያን የመሰለች ደሐ ሐገር ዓለም አቀፉ ዕርዳታ እየተደረገላት 650 ሺሕ ስደተኛ እያስተናገደች፤ ብዙ ማድረግ የሚችሉት ያዉሮጳ መንግሥታት ድንበራቸዉን እንዴት ያጥራሉ? ጠየቁ ሾፌሩ።

Straßenszene in Eastleigh
ምስል Bettina Rühl

«የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ልክ እንደ ትምሕር ቤት ነዉ።ደንብ ያስፈልገዋል።መንግሥታቱ ግን ጥሩ ነገር አላደረጉም።ስደተኞች እንዳይገቡባቸዉ ትላልቅ አጥር ያጥራሉ።»

ይሁንና የኬንያ «የኤኮኖሚ ጉዳይ» የተሰኘዉ የኬንያ አጥኚ ተቋም ባልደረባ ክዋም ኦዊኖ እንደሚሉት ጀርመን ከኬንያ መማር የሌለባት አንድ ነገር አለ።

«ስደተኞች በብዛት ሲመጡ፤ እዚሕ እኛ እንዳደረግ ነዉ በተዘጋ መጠለያ ጣቢያ ዉስጥ ማስፈር አይጠቅምም።ስደተኞቹ ከሕዝቡ እንዳይቀየጡ ያደርጋል።»

ኦዊኖ እንደሚያምኑት አፍሪቃም ሆነ አዉሮጳ ልዩነት የለዉም።ሥደተኛዉ ፈጥኖ እንዲሰራ ከተደረገ የየአስተናጋጁን ሐገር ምጣኔ ሐብት ለማሳደግ ይረዳል።«ኔሽን» በተባለዉ የኬንያ ጋዜጣ በቅርቡ ባሳተሙት መጣጥፍ ጀርመን በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ስደተኞችን ለማስተናገድ መፍቀድዋን «ጀርመን ዳግም ከተዋሐደች ወዲሕ ከወሰደቻቸዉ እርምጃዎች ሁሉ ታላቁ በጎ እርምጃ በማለት አወድሰዉታል።

ብዙ ኬንያዉያን ጀርመኖችን የዉጪ ሰዉ ይጠላሉ ብለዉ ያምናሉ።ያሁኑ የጀርመን እርምጃ፤ ኦዊኖ እንደሚሉት ግን የጀርመንን ነባር ገፅታ ለመለወጥ ጠቃሚ ነዉ።

«በዚሕ ቀዉስ ጀርመን የወሰደችዉ እርምጃ መጥፎዉን ገፅታዋን ለመቀየር ጥሩ አጋጣሚ ነዉ። እንደዚያ አይደለንም።ይሕ ከባድ ፖለቲካዊ ዉሳኔ ነዉ።ከሞራል አኳያ ሲታይ ግን እርምጃዉ ተገቢ መሆኑን እንገነዘባለን።»

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሠ