1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደተኞች የማዳኑ ተልዕኮ መዘዝ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 5 2009

ከአፍሪቃ ወደ አዉሮጳ ለመሰደድ ሲሉ በባህር ዉስጥ ለመስጠም አደጋ የሚጋለጡትን ለማዳን የተሰማራዉ ተልዕኮ አሉታዊ የጎንዮሽ ዉጤት እንዳስከተለ ተገለጸ። በሊቢያ የተመድ ልዩ ልዑክ ማርቲን ኮብለር እንደሚሉት የአዉሮጳ ኅብረት የባህር ላይ ተልዕኮ ከሚንቀሳቀስበት ርቀት ዉጭ ባለዉ አካባቢ ሕገወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎች የተለመደ ተግባራቸዉን ቀጥለዋል።

https://p.dw.com/p/2UGwT
Mittelmeer Schiffsunglück Flüchtlingsboot vor der libyschen Küste gesunken
ምስል picture-alliance/dpa/Italian Coast Guard

Kobler: 'Rettungsoperationen ziehen Schleuser an' - MP3-Stereo

የሕገ ወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎችን መረብ ለመከላከል በዓለም አቀፍ የባህር ላይ ያሠማራዉ ተልዕኮ አሉታዊ ዉጤት እንዳለዉ ተቺዎች እየጠቆሙ ነዉ። አዉሮጳ ለዚሁ ተግባር ሶፊያ በሚል ስያሜ ሜዲትራኒያን ባህር ላይ ተዕኮዋን አሠማርታለች፤ ግብረ ሠናይ ድርጅቶችም ባህር ዉስጥ የመስጠም አደጋ ያንዣበበባቸዉን ስደተኞች ለመታደግ ተመሳሳይ ተልዕኮ ዘርግተዋል። የዶቼ ቬለ የጀርመንኛ ቋንቋ ክፍል ባልደረባ ያን ፊሊፕ ሾልስ ያነጋገራቸዉ በሊቢያ የተመድ ልዩ ልዑክ ማርቲን ኮብለር የተባለዉን ትችት የሚያጠናክር አስተያየት ነዉ ያላቸዉ።

«ይህ ያልተፈለገ ዉጤት በእርግጥም አላቸዉ። የአዉሮፓ መርከቦች ከባህር ዳርቻ ሃገራቱ የባህር ክልል ከሆነዉ ከ12 ማይል ዞን ዉጭ ነዉ የሚንቀሳቀሱት። በዚህ ምክንያትም ሕገ ወጥ አሸጋጋሪዎቹ ሰዎቹን በዚያ በማይደርሱበት 12 ማይል ክልል ዉስጥ ያመጧቸዋል፤ እንደዉም ሰዎቹን እንዲያወጧቸዉ የጣሊያን የባህር ጠረፍ ጠባቂዎችን ሁሉ ደዉለዉም ይጠራሉ። እዉነት ነዉ ይህ ዘመቻ የመፍትሄዉ አካል እንዲሆኑ ሰዎቹን የመሳብ ሚና አለዉ። እናም የሊቢያ መንግሥታዊ ይዞታ መስመር እስካልያዘ ድረስ ሕገ ወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎቹ ተግባራቸዉን ሊያቆሙ አይችሉም።»

የሕገ ወጥ ሰዉ አሸጋጋሪዎቹን እንቅስቃሴ ለመግታት የሚደረገዉ የባህሩ ላይ ተልዕኮ አሉታዊ ዉጤት አስከትሏል ከተባለ፤ ይህን ተግባር ማስቆም ታዲያ እንዴት ይቻላል? ማርቲን ኮብለር፤

«በአንድ በኩል ጠንከር ያለ ርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል። ይህ ወንጀል ነዉ፤ እናም ሰዎቹ ወደ ሕግ ፊት እየቀረቡ መቀጣት አለባቸዉ። ለዚህ እርግጥ ነዉ ገለልተኛ ፍርድ ቤት ያስፈልጋል። ይህ ግን እስካሁን የለም። በሕገ ወጥ መንገድ አሸጋጋሪዎቹ ሰዎቹን ከሱዳና እና ኒዠር በሰሃራ በረሃ አቋርጠዉ እዚህ ድረስ ያመጧቸዋል። እዚህ ደግሞ በመጠለያ ጣቢያዎች አንዳንዴም መንግሥት በሚያንቀሳቅሰዉ መጠለያ ዉስጥ ይቀመጣሉ። ይህ ደግሞ አንዳንዴ የሰብዓዊ መብቶች የማይከበሩበት ሊሆን ስለሚችል እኛ ስጋት አለን።»

ማርቲን ኮብለር ላለፉት አንድ ዓመት ሊቢያ ዉስጥ ለተመድ ተልዕኮ ድጋፍ የሚሰጠዉን ተልዕኮ ሲመሩ ቆይተዋል። በዚህ ቆይታቸዉ ግን የታሰበዉን ያህል ማሳካት እንዳልተቻለ ነዉ የጠቆሙት።

Martin Kobler PK zu Libyen in Berlin
ማርቲን ኮብለርምስል picture-alliance/dpa/M. Messara

« በተልዕኮዬ ማብቂያ ላይ ያን ያህል ትልቅ የሚባል የሊቢያ መፍትሄ ላይኖር ይችላል። ይህ የአንድ ትዉልድ የቤት ሥራ ነዉ የሚሆነዉ። በዚህ ዓመት ባደረግነዉ ደስተኛ አይደለሁም፤ ለምሳሌ ስደትን በተመለከተ ማለት ነዉ። አዎንታዊም አሉታዊም ነገሮች አሉ። ሽብርተኝነት በመዋጋቱ ረገድ አዎንታዊ ዉጤት አለ። የስደቱ ጉዳይ ደግሞ አሉታዊ ነዉ። ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ሊቢያን በተመለከተ ጠንከር ያለ አካሂድ ቢኖረዉ እመኛለሁ። ምክንያቱም ጎረቤት ሀገር ናት። ከዚህ የአዉሮጳ ኅብረት አካል ወደሆነችዉ ወደ ማልታ የ30 ደቂቃ በረራ ብቻ ነዉ። በሌላ ፕላኔት ላይ አይደለችም።»

የወደፊቱን ስንመለከት በጎርጎሪዮሳዊዉ 2050 ዓ,ም አፍሪቃ 2.2 ቢሊየን ህዝብ ሊኖራት እንደሚችል የጠቆሙት ማርቲን ኮብለር ሕዝቧ ወደ ሰሜን ሊገፋ እንደሚችል ነዉ ግምታቸዉን የሰነዘሩት። በዚህ ጊዜም አዉሮጳ ሕዝብ በ73 ሚሊየን ሊቀነስ ስለሚችል ከወዲሁ ለዚህ መፍትሄ እንዲሆን ሰዎች በየትዉልድ ሃገራቸዉ ሊቆዩ የሚያስችላቸዉ ስልት ሊቀየስ ይገባልም ይላሉ። ሌላዉ ለማርቲን ኮብለር የቀረበዉ ጥያቄ ሊቢያ የከሸፈች መንግሥትና ሀገር ናት ማለት ይቻል ወይ? የሚል ነዉ፤

Libyen Kämpfe um letzte IS-Stellung in Sirte
ምስል Getty Images/AFP/M. Turkia

«ሊቢያ መንግሥትነቷን ያላረጋገጠች በትክክል አስቸጋሪ ሀገር ናት። ሆኖም ለዚህ መፍትሄ ለመፈለግ እየሠራን ነዉ። ሊቢያ ጠንካራ ተቋማት የሏትም። ከ42ቱ የጋዳፊ አምባገነናዊ ዓመታት በኋላ ሀገሪቱን አንድ አድርጎ ለመምራት በጣም አስቸጋሪ ሆኗል። ይህ ደግሞ በዛሬ እና በነገ መካከል አይወገድም።»

የሊቢያን ብሔራዊ የጦር ሠራዊት ለማቋቋም የታሰበዉ እንደታቀደ እስካሁን ባይሳካም በቅርቡ ግን ይሳካል የሚል ተስፋቸዉንም ገልጸዋል። አዉሮጳ ወደ ሊቢያ የጦር መሣሪያ መላክ እንደማይኖርባት ያመለከቱት በሊቢያ የተመድ ልዩ ልዑክ አክለዉም እያንዳንዱ የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሀገር በተናጠል የሊቢያን ኃይሎች በጦር መሣሪያ ላለመደገፍ የገቡትን ቃል ያከብራሉ የሚል ተስፋ እንዳላቸዉም አመልክተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ/ፊሊፕ ሾልስ

ኂሩት መለሰ