1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስደትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኤርትራ

Merga Yonas Bulaሰኞ፣ የካቲት 7 2008

በታህሳስ ወር አጋማሽ ላይ የጀርመኑ አለማቀፍ የልማት ትብብር ሚንስትር ጌርድ ሙሌር ከዉጭ ጉዳይ፣ ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ የተወጣጡ ልዑካንን አስከትለዉ ለሁለት ቀናት ኤርትራን ጎብኝተዋል።

https://p.dw.com/p/1HuZd
Karte Ethiopia und Eritrea ENG

[No title]

በጉብኝታቸዉ ወቅት የሁለትዬዎሹን ስምምነት እና የልማት ትብብሩ እንዳለ ሆኖ ስደትና ኤርትራ ዉስጥ ያለዉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዋና የዉይይት ነጥብ ነበር።የጀርመን መንግስት ለስደቱ እዛዉ ኤርትራ ዉስጥ የሚበጀዉን መፍትሄ ማፈላለግ ነዉ የሚል አቋም ሲኖረዉ፤ ለዚህም ከኤርትራ መንግስት ጋር አብሮ ለመሥራት እንዳቀደ ተገልጿል።


ይሁን እንጂ ይህን በተመለከተ ከጉብኝቱ መልስ የልዑካን ቡድኑ አባል ከሆኑት አንዱ ሚዜሬኦር (Misereor) የተሰኘዉ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የእርዳታ ድርጅት፤ የጀርመን እና የኤርትራ መንግሥት ስደትን አስመልክቶ ያካሄዱትን ድርድር ተችቷል። የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ማርቲን ብሮኬልማን-ሲሞን፣ የጀርመን መንግስት የስደተኞችን ቁጥር ለመቀንስ ሲል የኤርትራን መንግስት ይረዳል ሆኖም ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል የሰዉ መብት መጣስ የለበትም ይላሉ።


የኤርትራ መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚተች እና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለስደት የዳረገዉ ዋነኛ መንስኤም ይህ መሆኑን የተለያዩ ዘገባዎች ያመለክታሉ። የጀርመን መንግስት የሚታየዉ የስደተኛ ፍልሰት ሀገሪቱን አጣብቂኝ ዉስጥ ስላስገባት የስደተኛ ምንጭ በሆኑ አካባቢዎች ሁኔታዉን ባለበት የመቆጣጠር ሥራን ተያይዞታል። ተቺዎች ግን ድርድሩ እንደኤርትራ ባሉ ሃገራት የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ሊያባብስ ይችላል ብለዉ ይሰጋሉ። ግን መሆን ያለበት ይላሉ ብሮኬልማን-ሲሞን፣ << አሁን መደረግ ያለበት ዉይይት መጀመር ነዉ። ምክንያቱም ከ20 ዓመት በላይ በጀርመንም ሆነ በኤርትራ መንግሥት ባለስልጣናቶችም በኩል ምንም ዓይነት ንግግሮች አለነበሩም። እኔም የማስበዉ እንዲሁም በኤርትራ የሚገነዉ የእኛ ቤተ ክርስቲያንም የወሰደዉ አቋም ንግግር መጀመር አለበት የሚል ነዉ። ምክንያቱም ይህ አገሪቱ ዉስጥ ያለዉን የሰብዓዊ መብት ረገጣም ሆነ የግለሰብ መብቶች ይዞታ እንዲሻሻል ሊያግዝ ይችላል።>>

Italien Flüchtlinge aus Eritrea vor Abflug aus Italien
ምስል DW/M. Williams


ኤርትራ በኤኮኖሚ ልማትም ሆነ በምግብ አቅርቦት ችግር እንዳለባት እና የኑሮ ሁኔታዎች ከዚህ የበለጠ መሻሻል እንደሚኖርባቸዉ ብሮኬልማን-ሲሞን ለዶቼ ቬሌ ገልጸዋል። አክለዉም ወጣቶቹ አገሪቱን ጥለዉ የሚሰደዱትበት ምክንያትም የኑሮ ዘይቤዉ አስቸጋር በመሆኑ እንደሆነም አመልክተዋል። ለዚህም የኤርትራ መንግሥት ይህንን ችግር ለማቃለል ዝግጁነቱን ማሳየት እንደሚኖርበት በመጠቆም፤ የጀርመን መንግሥት ማድረግ አለበት ያሉትን እንዲህ ስሉ ያብራራሉ፣ << የጀርመን መንግስት የኢኮኖሚ እና የልማት ትብብር ከኤርትራ መንግሥት ጋር ለማድረግ ፍላጎቱን ካሳየ በኤርትራ በኩልም ተመሳሳይ ፍላጎት መታየት አለበት፣ ማለትም የብሄራዊ ዉትድርና አገልግሎትን በተመለከተ በሩን ለለዉጥ መክፈት አለበት። ይህን አንዱ ምክንያት ነዉ። ብዙ ሰዎች አገሪቱን ጥለዉ የሚሰደዱበት ምክንያት የወደፊት ህይወታቸዉንል ከ10 እና ከእዛ በላይ በሚወስድ አገልግሎት ዉስጥ ማጥፋት አይፈልጉም።>>


የኤርትራ መንግሥት ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ እሱ ግዚ የሚነግረን ይሆናል ሲሉ ብሮኬልማን-ሲሞን ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል። ወደ አዉሮጳ ከፈለሰዉ ኅብረተሰብ በከፍተኛ የስደተኛ ቁጥር ኤርትራ ከእነሶርያ እና አፍጋኒስታን ጋር እንደምትሰለፍ ዘገባዎች ያሳያሉ። በፈረንጆቹ 2015 መጀመርያ አካባቢ ወደ 3,582 ኤርትራዉያን ጥገኝነት እንደጠየቁት የጀርመኑ የስደትና ስደተኞች ጉዳይ ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

Sprachkurs für Flüchtlinge aus Syrien Eritrea Iran Irak Deutschkurs Deutsch lernen
ምስል picture-alliance/dpa/H.Schmidt

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ