1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርታዊ አጫጭር ዜናዎችና ዝውውር

ሰኞ፣ ሐምሌ 21 2006

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የበጋ ወራት ፍልሚያ ሊጀመር የቀሩት 19 ቀናት ግድም ነው። የዓለም ታላላቅ የእግር ኳስ ቡድኖች የተጨዋቾች ዝውውር ላይ ተጠምደዋል። በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ የወጣቶች ፉክክር ኢትዮጵያ ሦስተኛ ሆና አጠናቃለች።

https://p.dw.com/p/1Ckry
ምስል picture-alliance/dpa

ታላላቆቹ ቡድኖች ከወዲሁ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾችን በእጃቸው ለማስገባት በሚሊዮናት የሚቆጠሩ ዶላሮችን በማፍሰስ ተጠምደዋል። በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ የወጣቶች ውድድር ኢትዮጵያ ሦስት የወርቅ እና ሦስት የብር ሜዳዮችን በመሰብሰብ የሦስተኛነት ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ማንቸስተር ዩናይትድ የሮማው አማካይ ኬቪን ስትሩትማንን በእጁ ለማስገባት 79 ሚሊዮን ፓውንድ ማዘጋጀት እንዳለበት እንደተነገረው ዘ ሠን የተሰኘው ጋዜጣ አትቷል። የ24 ዓመቱ ሆላንዳዊ አማካይ በደረሰበት የጉልበት ግጭት ከመጋቢት ወር አንስቶ አልተጫወተም።

የቤልጂየሙ ተከላካይ የ27 ዓመቱ ጃን ፈርቶንጌን ለቶትንሐም አዲስ ውል እንደሚፈርም ገለጠ ሲል ደግሞ ዴይሊ ሚረር አትቷል። የሪያል ማድሪዱ የክንፍ ተጫዋች የ26 ዓመቱ አንጌል ዲ ማሪያ ለማንቸስተር ዩናይትድ መሰለፍ እንደሚፈልግ መግለፁን ዴይሊ ስታር አስነብቧል። 45 ሚሊዮን ፓውንድ የተገመተለት አርጀንቲናዊ ወደ በርናባው ተመልሶ ለሪያል ማድሪድ መጫወት እንደማይፈልግ ገልጿል።

ኢንተር ሚላን ከሮማ ለማስመጣት 15 ሚሊዮን ፓውንድ ያስወጣው ጣሊያናዊ አጥቂን ሳውዝ ሐምፕተኖች እንዲወስዱት ለማስቻል ልዑካናቱን እንደሚልክ ተጠቅሷል ሲል ያስነበበው ዴይሊ ሜይል ነው። ተጨማሪ የዝውውር ዜናዎችን ይዘናል። ወደ በኋላ ላይ እንመለስበታለን።

Champions League Manchester United - Bayern München
ምስል Reuters/Stefan Wermuth

አትሌቲክስ

በአትሌቲክስ ማኅበር ፌዴሬሽን የዓለም ወጣቶች ፉክክር ኢትዮጵያ በስድስት ሜዳሊያ የሦስተኛነትን ደረጃ በማግኘት አጠናቀቀች። ዩናይትድ ስቴትስ ኦሬጋን ግዛት ውስጥ ለተከታታይ ስድስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የዓለም አቀፍ አትሌቶክስ ፉክክር የተጠናቀቀው ትናንት ነው። በውድድሩ ኢትዮጵያ በ5000 የሴቶች እና የወንዶች ፉክክር ዓለሚቱ ሄሮዬ እና ዮሚፍ ቀጀልቻ በአንደኛነት እንዲሁም በ1500 ሜትር የኢትዮጵያ የሴቶች ሩጫ ክብርወሰን ባለቤት የሆነችው ዳዊት ሥዩም በ1500 ሜትር ቀዳሚ ሆነው በማጠናቀቅ ሦስት የወርቅ ሜዳዮችን አስገንተዋል። በሴቶች እና በወንዶች የ5000 ሜትር ሩጫ ዓለሚቱ ሐዊ እና ያሲን ሐጂ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳይ ሲያስገኙ፤ በሴቶች የ1500 ሜትር የሩጫ ፉክክር ጉዳፋ ፀጋዬ ተጨማሪ ብር አስገኝታለች። በእዚህ ውድድር ዩናይትድ ስቴትስ 11 ወርቅ፣ 5 ብር እና 5 ነሐስ በማግኘት አንደኛ ወጥታለች። ኬንያ በ4 ወርቅ፣ 5 ብር እና 7 ነሐስ ሜዳዮች ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች።

የብስኪሌት ሽቅድምድም፤

በሰሜናዊ ብሪታንያ ዮክሻየር ወረዳ ትናንት በተካሄደው የቱር ደ ፍሯንስ የብስክሌት ሽቅድምድም የካዛክስታኑ ብስክሌተኛ ቪንሴንሶ ኒባሊ አሸናፊ ሆኗል። የቪንሴንሶ ኒባሊ ድል ያነቃቃው የካዛክስታን መንግስት የቱር ደ ፍሯንስ ሽቅድምድምን በመካከለኛው እስያ ምድሩ ለማዘጋጀት ፍላጎት እንዳለው ዛሬ ይፋ አድርጓል። የካዛክስታን የብስክሌት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ካይራት ኬሊምቤቶቭ ዛሬ ለአዣንስ ፍሯንስ ፕሬስ እንደተናገሩት ከሆነ፤ ሀገራቸው ካዛክስታን የዘንድሮውን ውድድር እንዳዘጋጀችው ብሪታንያ የቱር ደ ፍሯንስን ማሰናዳት ትሻለች። ካዛክስታን በሚቀጥለው ዓመት የሚከናወነውን የዓለም ወጣቶች የብስክሌት ሽቅድምድም እንድታሰናዳ ተመርጣለች። በቀጣዮቹ ስድስት ዓመታት ውስጥ ግን የቱር ደ ፍሯንስ ውድድርን ለማሰናዳት ቆርጣ መነሳቷን ይፋ አድርጋለች።

የአርሰናል ቡድን
የአርሰናል ቡድንምስል imago/Colorsport
ከሊቨርፑል የተሸጠው ሉዊስ ሱዋሬዝ
ከሊቨርፑል የተሸጠው ሉዊስ ሱዋሬዝምስል picture-alliance/dpa

በሐንጋሪው የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ትናንት የሬድቡል አሽከርካሪው ዳንኤል ሪካርዶ አንደና በመሆን አጠናቋል። ፈርናንዶ አሎንሶ በፌራሪ ተሽከርካሪው ሁለተኛ ሲወጣ፤ ሌዊስ ሀሚልተን በመርሴዲስ ተሸከርካሪው ከኋላ ተንደርድሮ በመክነፍ ሦስተኛ ለመውጣት ችሏል።

ጁቬንቱሶች የአጥቂ ክፍላቸውን ለማጠናከር የቸልሲው አጥቂ ሮሜሉ ሉካኩ ላይ አይናቸውን ጥለዋል። ሆኖም የ21 ዓመቱ ወጣት ቤልጂየማዊ አጥቂን በእጃቸው ለማስገባት ሪያል ማድሪዶች ተፎካካሪ ሆነው ቀርበዋል ሲል ኤ ኤስ አስነብቧል። የባርሴሎናው የቀኝ ተመላላሽ የ31 ዓመቱ ዳኒ አልቬስን ለመሸጥ ቡድኑ ዝግጁ እንደሆነ የስፔን ጋዜጦች አስነብበዋል። ብራዚላዊው ዳኒ አልቬስ ባለፈው የውድድር ዘመን አራት ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ፤ ስድስት ኳሶች ግብ እንዲሆኑ አመቻችቶ መስጠቱም ተዘግቦለታል። ዳኒ አልቬስን ምናልባት ሊቨርፑል በተለይ ደግሞ ማንቸስተር ዩናይትዶች ሊወስዱት ይችላሉ ተብሏል።

ማንቸስተር ዩናይትድ ኤ ኤስ ሮማን ዩናይትድ ስቴትስ ዴንቨር ውስጥ ለወዳጅነት ገጥሞ 3 ለ 2 ባሸነፈበት የቅዳሜው ጨዋታ ሆላንዳዊው አሠልጣን ቫን ጋል በቡድናቸው አቋም ደስተኛ እንዳልነበሩ ገልጠዋል። የፕሬሚየር ሊጉ ከመጀመሩ በፊት ማሻሻል የሚገባን ነገሮች አሉ ብለዋል። «በማሸነፋችን ደስተኛ ነኝ፤ ሆኖም ጥሩ ጨዋታ አልነበረም» ብለዋል የማንቸስተሩ አሠልጣኝ። የክንፍ ተመላላሽ ቦታው የሳሳ እንደነበር ጠቁመዋል። ምናልባት የባርሴሎናው የቀኝ ተመላላሽ ዳኒ አልቬስን ማንቸስተር ዩናይትዶች ሊወስዱት ይፈልጋሉ ከተባለው ጋር የአሠልጣኙ ፍላጎት የሚጣጣም ይመስላል።

አርሰናል የመሀል ክፍሌን በሚገባ ይመራልኛል ሲል ተስፋ የጣለበት ታዳጊ ወጣት ነው፤ የ17 ዓመቱ ጀርመናዊ ጌዲዮን ዘላለም። ቋሚ መኖሪያቸውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረጉት በትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑት አባቱ የዩናይትድ ስቴትስ ዜግነት ለማግኘት አመልክተው ተቀባይነት እንዳገኙ ከወራት በፊት ዋሽንግተን ፖስት ዘግቦ ነበር። እናም የአርሰናሉ አማካይ ጌዲዮን ዘላለም ለተወለደበት እና ዜግነት ለያዘበት ጀርመን፣ ለዩናይትድ ስቴትስ አለያም ለአባት ሀገሩ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ የመጫወት ዕድል አለው።

18 ዓመት ከሞላው በኋላ ለየትኛው ሀገር ተሰልፎ እንደሚጫወት ግን አሁንም ድረስ አልወሰነም። ከትናንት በስትያ ቡድኑ አርሰናል ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከኒው ዮርክ ሬድ ቡልስ ጋር ተጫውቶ 1 ለ ባዶ ከተሸነፈ በኋላ ጌዲዮን ዘላለም ለየትኛው ሀገር ተሰልፎ ሊጫወት እንደሚችል ተጠይቆ ከውሳኔ ላይ እንዳልደረሰ ተናግሯል። የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን አሠልጣኝ ጀርመናዊው የርገን ክሊንስማን በስልክ ደውሎ እንዳነጋገረው ሆኖም ምንም የተለየ ነገር እንደሌለ ጊዲዮን ለጋዜጠኞች አስታውቋል።


ጌዲዮን «በእዚህ ቅፅበት ትኩረቴ ሁሉ የአርሰናል ዋናው ቡድን ውስጥ ሰብሬ በመግባት መጫወት ነው» ብሏል። አያይዞም «ሁለቱም ታላላቅ ሃገራት ናቸው፤» አለ ከጨዋታው መልስ፤ «አሜሪካ እየገሰገሰች ነው፤ ጀርመን ድሮውኑም ታላቅ ሀገር ነው። የትኛውንም ሀገር ልምረጥ ጥሩ ምርጫ ነው የሚሆነው። » ብሏል። አሁንም ድረስ ግን በርካታ ኢትዮጵያውያን እግር ኳስ አፍቃሪያን ጌዲዮን ኢትዮጵያን ምርጫው ያደርግ እና ያስደምመን ይሆናል ሲሉ ተስፋ መጣላቸው አልቀረም።

ጌዲዮን ዘላለም በቅዳሜው የአርሰናል እና ኒው ዮርክ ሬድ ቡልስ ጨዋታ ለ45 ደቂቃ ያህል ተሰልፎ ለመጫወት ችሏል። በእርግጥ በእዚህ ጨዋታ ከህፃንነቱ አንስቶ ሲከታተሉት የነበሩት የአርሰናሉ አሠልጣኝ አርሰን ቬንገር እና ቲየሪ ኦንሪ ያወሩለትን ያህል ብቃቱን ማሳየት እንዳልቻለም ተዘግቧል። ጌዲዮን እስካሁን በብሔራዊ ደረጃ ከ15 ዓመት፣ 16 እና 17 ዓመት በታች የጀርመን እግር ኳስ ቡድን ውስጥ ለመካተት ችሏል።

ሊቨርፑል የክሮሺያው የመሀከል ተመላላሽ ዲየን ሎሬንን ከሳውዝ ሐምፕተን በ20 ሚሊዮን ፓውንድ የረዥም ጊዜ ውል ለማስፈረም መቻሉ ዛሬ ተዘግቧል። ዲየን ሎሬን ለሊቨርፑል መፈረሙ የረዥም ጊዜ ህልሙ እንደነበር አልሸሸገም። «ባለፈው ጊዜ አንፊልድ ሜዳ ላይ መጥቼ ስጫወት አንድ ቀን እዚህ ለሊቨርፑል እጫወት ይሆናል ስል ለእራሴ ተናገርኩ።» ሲል ህልሙ መሳካቱን በደስታ ገልጿል።

ዲየን ሎሬን ወደ ሊቨርፑል የመጣበት ክፍያ እስካሁን ሊቨርፑል ለተጨዋቾች ካወጣው ውዱ እንደሆነ ተነግሮለታል። ከእዚህ ቀደም ቡድኑ ለተጫዋች ዝውውር ያወጣው ትልቁ ክፍያ 18 ሚሊዮን ፓውንድ ሲሆን፤ ክፍያውም ፈረንሣዊው ማማዱ ሳክሆን ከፓሪስ ሳንጀርሜይን ለማስመጣት የወጣ ነበር።


የፕሪሚየር ሊጉ ዋንጫን ለጥቂት ከእጁ የተነጠቀው ሊቨርፑል ከቀናት በኋላ በሚጀመረው የፕሬሚየር ሊግ ፍልሚያ ኃያል ተፎካካሪ ለመሆን የቆረጠ ይመስላል። ሊቨርፑል በእዚህ የበጋ ወራት ብቻ ሦስት ተጨዋቾችን ለማስፈረም ተሳክቶለታል። እንግሊዛውያኑ ሪኪ ላምበርት እና አዳም ላላናን ተከትሎ ዲየን ሎሬን ሦስተኛው ፈራሚ ሆኗል። ቀደም ሲል ሊቨርፑል የጀርመን ከ21 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊው አማካዩ ኤምሬን ከባየር ሌቨርኩሰን እንዲሁም ሠርቢያዊው የክንፍ ተመላላሽ ላዛር ማርኮቪችን ከቤኔፊካ ማስፈረሙ ይታወሳል። ቤልጂየማዊው አጥቂ ዲቮክ ኦሪጂ የጤና ምርመራ ተደርጎለት በቅርቡ ወደ ሊቨርፑል ሊቀላቀል እንደሚችል ተጠቅሷል። የኪውፒአር አጥቂ ሎይች ሬሚን ለማስመጣት ይደረግ የነበረው ጥረት ግን መክሸፉ ተነግሯል።

ሊቨርፑሎች ድርድሩ የተቋረጠው ሬሚ አስፈላጊውን የሕክምና ምርመራ ባለማድረጉ ነው ቢሉም፤ ውስጥ አዋቂዎች ግን ፋቢዮ ቦሪኒ በሊቨርፑል ለመቆየት በመወሰኑ የተነሳ ነው ድርድሩ የፈረሰው ብለዋል። ሊቨርፑል አሁን የስዋንሲ ሲቲው አጥቂ ዊልፍሬድ ቦኒ ላይ አይኑን ጥሏል። የኡራጉዋዩ ተናካሽ አጥቂ ሉዊስ ሱዋሬዝን በ128 ሚሊዮን ዶላር ለባርሴሎና የሸጡት የሊቨርፑሉ አሠልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ተጨዋቾች ለመግዛት ቆንጠር የሚያደርጉበት ካዝናቸው ገና አልተሟጠጠም። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሊቨርፑል 36 ሺህ ታዳሚ በተገኘበት የቺካጎው የወዳጅነት ግጥሚያ ዛሬ ኦሎምፒያኮስን ገጥሞ በራሂም ስተርሊንግ ግብ አሸናፊ ሆኗል።


ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዳንኤል ሪካርዶ በፎርሙላ አንድ ሽቅድድም
ዳንኤል ሪካርዶ በፎርሙላ አንድ ሽቅድድምምስል picture-alliance/dpa

አርያም ተክሌ