1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ሚያዝያ  30 ቀን፣ 2009 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ሚያዝያ 30 2009

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት በመድፈኞቹ 2 ለ 0 ድል የተመታው ማንቸስተር ዩናይትድ ለሻምፒዮንስ ሊግ የነበረው ተስፋ ደብዝዟል። ሊቨርፑል በሜዳው ወሳኝ ጨዋታ አድርጎ ነጥብ ጥሏል። ቸልሲ ዋንጫውን በእጁ ሊያስገባ ተቃርቧል። ከእንግዲህ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። በፕራግ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል በድል ኾነዋል።

https://p.dw.com/p/2cdB3
Symbolbild Erstliga Fußball FC Arsenal
ምስል picture-alliance/Back Page Images

ስፖርት ሚያዝያ 30፤ 2009

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ትናንት በመድፈኞቹ 2 ለ 0 ድል የተመታው ማንቸስተር ዩናይትድ ለሻምፒዮንስ ሊግ የነበረው ተስፋ ደብዝዟል። ሊቨርፑል በሜዳው ወሳኝ ጨዋታ አድርጎ ነጥብ ጥሏል።  ቸልሲ ዋንጫውን በእጁ ሊያስገባ ተቃርቧል። ከእንግዲህ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ማሸነፍ ይጠበቅበታል። የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ቶማስ ቱህል ቡድኑን ሊሰናበቱ መኾኑ እየተነገረ ነው፤ ምክንያት? ከቡድኑ ሥራ አስፈጻሚ ጋር አለመግባባታቸው ነው ተብሏል። በፕራግ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል በድል ኾነው አምሽተዋል።

ዛሬ ማታ ሚድልስቦሮውን የሚገጥመው ቸልሲ አማካኝ ንጎሎ ካንቴ በብሪታንያ እግር ኳስ ጸሓፍት ማኅበር የዓመቱ ምርጥ እግር ኳስ ተብሎ ዛሬ ተሰይሟል።  340 አባላት ባሉት ማኅበር ለሽልማቱ ታጭቶ የነበረው የቡድን አባሉ ኤደን ሐዛርድን አሸንፎ ነው ንጎሎ ካንቴ ተሸላሚ የኾነው። ባለፈው ወርም በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማኅበር በኩል ለተሸለመው ለንጎሎ ካንቴ ይኽ የዛሬው ሽልማት ኹለተኛ መኾኑ ነው። «ለዚህ ሽልማት መብቃት ለእኔ ታላቅ ክብር ነው» ሲል ንጎሎ ካንቴ በሽልማቱ ወቅት ተናግሯል።

ንጎሎ ካንቴ ወደ ቸልሲ ቡድን ዘንድሮ የተዘዋወረው ካለፈው የጨዋታ ዘመን የዋንጫ አሸናፊ ከላይስተር ሲቲ ቡድን ነው። የዝውውር መጠኑም 32 ሚሊዮን ፓውንድ ወይንም 41,5 ሚሊዮን ዶላር ይጠጋል። በአሁኑ ወቅት በአንቶኒዮ ኮንቴ በሚመራው ቡድን ውስጥ ወሳኝ ተጨዋች ተደርጎ ይወሰዳል። ለፉክክር የቀረበው ሌላኛው የቸልሲ ተጨዋች ኤደን ሐዛርድ ከ2 ዓመት በፊት የብሪታንያ እግር ኳስ ጸሓፍት ማኅበር እና የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማኅበር ሽልማቶች ጣምራ አሸናፊ ነበር። የቶትንሐም ሆትስፐሩ አማካይ ዴሌ ዓሊ በዘንድሮው ሽልማት ኤደን ሐዛርድን ተከትሎ ሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል።

England Fußball Manchester United vs. Leicester City
ምስል Reuters/J. Cairnduff

ከትናንቱ የ2 ለ0 ሽንፈት በኋላ ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሬሚየር ሊጉ አራተኛ ኾኖ በመጨረስ የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ የመኾን ተስፋው ደብዝዟል። አሰልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ በአርሰን ቬንገር በሚመራው አርሰናል ሽንፈት ከቀመሱ በኋላ በሰጡት መግለጫ «ከእንግዲህ ማንቸስተር ዩናይትድ አራተኛ ኾኖ መጨረሱ የማይቻል ነው» ብለዋል።

ዩናይትዶች ምናልባት የሚቀጥለው ዙር የሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ ሕልማቸው በአውሮጳ ሊግ ግጥሚያ በኩል እውን ይኾን ይኾናል። ማንቸስተር ዩናይት ለግማሽ ፍጻሜው የአውሮጳ ሊግ ግጥሚያ ሐሙስ ዕለት የሚገናኘው ከስፔኑ ሴልታ ቪጎ ጋር ነው። ሴልታቪጎ በላሊጋው 84 ነጥብ ይዞ መሪ ከኾነው ባርሴሎና በ40 ነጥብ ተልቆ ደረጃው 12ኛ ነው።

ማንቸስተር ዩናይትድ የፊታችን ሐሙስ ከሴልታቪጎ ጋር የሚያደርገውን ግጥሚያ አሸንፎ ግንቦት 17 ለሚከናወነው የፍጻሜው ፍልሚያ ይደርስ ይኾናል። በፍጻሜው የሚገጥመው ግን የፈረንሳዩ ሊዮንን ባለፈው ሳምንት ረቡዕ 4 ለ1 ያንኮታኮተው የሆላንዱ አያክስ አምስተርዳምን አለያም ራሱ ሊዮንን ነው። አያክስ አምስተርዳም በደች አንደኛ ዲቪዚዮን ደረጃ ሰንጠረዡ 2ኛ ሲኾን፤ ምናልባትም ዋንጫውን የመውሰድ ተስፋ ሳይኖረው አይቀርም።

ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሬሚየ ሊጉ ትናንት ጉድ የኾነው በአርሰናሎቹ ዳኒ ዌልቤክ እና  ግራኒት ሻቃ ነው። መድፈኞቹ  በሜዳቸው በተቀዳጁት የ2 ለ0 ድል ነጥባቸውን 63 በማድረስ 5ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ በሁለት ነጥብ  ብቻ ተበልጠዋል። ዩናይትድ የትናንቱ ግጥሚያው 35ኛው ሲኾን፤ ለአርሰናል ግን 34ኛው ነበር። ሦስት ጨዋታዎች የሚቀሩት ማንቸስተር ዩናይትድ 4ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ከማንቸስተር ሲቲ በ4 ነጥብ ይበለጣል።

70 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሠንጠረዡ ላይ ሦስተኛ የኾነው ሊቨርፑል በበኩሉ ትናንት በሜዳው ወሳኝ ነጥብ ጥሏል። 10ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ሳውዝሐምፕተን ጋር ገጥሞ ያለምንም ግብ ተለያይቷል። ሊቨርፑል ትናንት ያደረገው ጨዋታ 36ኛው ነው። ከማንቸስተር ሲቲ በላይ ኾኖ 3ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው እና ሁለት ጨዋታዎች ብቻ ለሚቀሩት ሊቨርፑል  ትናንት አርሰናል ማንቸስተር ዩናይትድን ማሸነፉ ጠቅሞታል። ማንቸስተር ዩናይትድ ባይሸነፍ ኖሮ አራተኛ የመውጣት ዕድሉን በማስፋት ለሊቨርፑል ስጋት መኾን ይችል ነበር።

Premierleague - FC Liverpool - FC Watford
ምስል picture-alliance/Office Sports Photography/S. Stacpoole

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከተከናወኑ የፕሬሚየር ሊጉ ግጥሚያዎች መካከል ቅዳሜ ዕለት ማንቸስተር ሲቲ 16ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ክሪስታል ፓላስን ገጥሞ 5 ለ0 ድባቅ መትቷል።  ቶትንሐም በአንጻሩ ባለፈው ዐርብ በዌስትሐም 1 ለ0 ቢሸነፍም፤ 77 ነጥብ ይዞ ሁለተኛ ደረጃውን እንዳስጠበቀ ነው። 

ቡንደስ ሊጋ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የቦሩስያ ዶርትሙንድ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኽል የዘንድሮ ውድድር ሲጠናቀቅ ከቡድኑ ጋር ያላቸው ግንኙነት ሊያበቃ እንደሚችል ዛሬ ተዘግቧል። አሰልጣኙ በቡድኑ ለመቆየት የፈረሙት ውላቸው የሚያከትመው ገና በሚቀጥለው ዓመት ነበር። ኾኖም ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሐንስ ዮኣሂም  ቫትስከ ጋር በመጋጨታቸው በቡድኑ አንድ ዓመት እንደማይቆዩ ጭምጭምታዎች ተሰምተዋል። በአሰልጣኙ እና በቡድኑ ሥራ አስፈጻሚ መካከል አለመግባባት የተፈጠረው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ለሻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍጻሜ የነበረው ግጥሚያ ከቦንቡ ፍንዳታ በኋላ ይደረግ ወይንስ ይሰረዝ በሚለው ነጥብ ላይ ነበር።

ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከፈረንሳዩ ሞናኮ ቡድን ጋር የነበረው ግጥሚያ የቡድኑ አውቶቡስ ላይ የፈንጂ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ተሰርዞ ጨዋታው የተከናወነው በበነጋታው ነበር። በወቅቱ አሰልጣኝ ቶማስ ቱህል ውድድሩ እንዲዘገይ ፈልጌ ነበር ብለዋል። የዶርትሙንድ ሥራ አስፈጻሚ ሐንስ ዮኣሂም  ግን የአሠልጣኙን ማስተባበያ ሐሰት ብለውታል። በውድድሩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በሞናኮ 3 ለ2 መሸነፉ ይታወሳል። በእርግጥ ጨዋታው በወቅቱ ባይከናወን ኖሮ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከፍተኛ ገቢ በማጣት ኪሣራ ሊደርስበት ይችል ነበር።

1. Bundesliga 32. Spieltag |  Borussia Dortmund v TSG 1899 Hoffenheim - Bundesliga
ምስል Getty Images/Bongarts/M. Hitij

በቡንደስ ሊጋው የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች፦ ፍራይቡርግ ሻልከን ትናንት 2 ለ0 ሲያሸንፍ፤ ሐምቡርግ  ከማይንትስ ጋር ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ቅዳሜ ዕለት ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሆፈንሃይምን 2 ለ1 አሸንፎ የሦስተኛ ደረጃውን ተረክቦታል።  በመሪው ባየር ሙይንሽን በ10 ነጥብ የሚመራው ላይፕትሲሽ ሔርታ ቤርሊንን 4 ለ1 አደባይቷል። አይንትራኅት ፍራንክፉርት በቮልፍስቡርግ 2 ለ0 ድል ሲነሳ ኢንግሎሽታድት ከባየር ሌቨርኩሰን ጋር አንድ እኩል ተለያይተዋል። ባለፈው የጨዋታ ዘመን ወደቡንደስ ሊጋው የመጣው ኢንግሎሽታድት 17ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ጠርዝ ላይ ከሚገኘው ዳርምሽታድት ጋር አምና ወደነበሩበት  ዲቪዚዮን ለመመለስ በቋፍ ላይ ይገኛሉ።

ለሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ የመልስ ፍልሚያ ጁቬንቱስ ከሞናኮ ጋር ነገ  ይጋጠማል። በመጀመሪያው ግጥሚያ ባለፈው ረቡዕ ጁቬንቱስ ሞናኮን ያሸነፈው 2 ለ0 ነው። ሁለቱ የስፔን ኃያላን ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲኮ ማድሪድ ደግሞ ከነገ በስትያ ረቡዕ ይገናኛሉ። በላሊጋው አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ሪያል ማድሪድ በግብ ክፍያ ብቻ ተበልጦ ከመሪው ባርሴሎና እኩል 84 ነጥብ ሰብስቧል። ለሻምፒዮንስ ሊግ የሚገጥመው አትሌቲኮ ማድሪድ በበኩሉ በ6 ነጥብ ተበልጦ በላሊጋው ደረጃው ሦስተኛ ነው።

አትሌቲክስ

በፕራግ ማራቶን የሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን ትናንት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ በመውጣት ድል ተቀዳጅተዋል። ኢትዮጵያዊው አትሌት ገብረጻድቅ አብራሃ 1ኛ በመውጣት ለድል የበቃው 2:08:47 በመሮጥ ነው። ብዙ ወርቅነህ እና መኳንንት አየነው ሁለተኛ እና ሦስተኛ ኾነው ተከታትለው ገብተዋል። በሴቶች ውድድር የአንደኛነት ድሉ ለኬኒያዊቷ አዪባይ ቢኾንም ኢትዮጵያውያቱ አማኔ በሪስ እና ታደለች በቀለ ተከታትለው ሁለተና እና ሦስተኛ ደረጃ አግኝተዋል። በአጠቃላይ ውጤቱ ኢትዮጵያውያን በሴትም በወንድም ገነው የወጡበት ነበር ማለት ይቻላል።

Eliud Kipchoge kenianischer Marathonläufer
ምስል picture-alliance/augenklick/firo Sportphoto

ናይክ የተሰኘው የስፖርት ዕቃዎች አምራች ድርጅት «Breaking2» በሚል ባዘጋጀው ፕሮጀክት ተሳታፊ የኾኑት ሦስት አትሌቶች የፕሮጀክቱን ግብ ማሳካት አልተቻላቸውም።  

ጣሊያን ሞንዛ ከተማ ውስጥ ቅዳሜ ዕለት በተከናወነው ውድድር ኬንያዊው ሯጭ ኤሊውድ ኪፕቾጌ ለድል ቢበቃም የፕሮጀክቱን ዕቅድ በጥቂት ሰከንዶች ሳያሳካ ቀርቷል። ናይክ ሚስጥራዊ በኾነ መልኩ ባመረተው የሩጫ ጫማ፣ አልባሳት እና የውሃ አቅርቦት በመታገዝ አትሌቶቹ የማራቶን ሩጫን ከ2 ሰአት በታች በመሮጥ ያጠናቅቃሉ ሲል አቅዶ ነበር።  ያን ግን ሊያሳካ አልቻለም። ኬንያዊው ሯጭ ኤሊውድ ኪፕቾጌ 42,195 የማራቶን ሩጫውን ያጠናቀቀበት ሰአት 2:00:25 ነው። 

ይኽ ሰአት ፈጣኑ ሰአት ተብሎ ተመዝግቧል። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (IAAF) ግን በተለያዩ ምክንያቶች ለውድድሩ ይፋዊ ዕውቅና አልሰጠውም።  በናይክ ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊው ለሊሳ ዲሳሳ እና ኤርትራዊው ዘረሰናይ ታደሰም ተሳታፊ ነበሩ። ዘረሰናይ ማራቶኑን ያጠናቀቀው በሁለት ሰዓት ስድስት ደቂቃ ከ51 ሰከንድ ሲኾን፤ ለሊሳ በበኩሉ የፈጀበት ሁለት ሰዓት ከ14 ደቂቃ ከ10 ሰከንድ ነው። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ