1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 24 2009

«ከመጀመሪያው አንስቶ የማውቀው ጓደኛዬ ነው፤ አብረን ብዙ ተወዳድረናል፤ ማንም እንዲያሸንፈው አይፈልግም፤ እልኸኛ ነው።» ሲል ያስታውሰዋል ማርሽ ቀያሪውን አትሌት። ትናንት ሥርዓተ ቀብሩ አዲስ አበባ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል። ሻምበል ምሩጽ ይፍጠር። በሞስኮ ኦሎምፒክ አብሮት የተወዳደረ የያኔው አትሌት የአሁኑ አሠልጣኝን አነጋግረናል።

https://p.dw.com/p/2VAjH
Symbolbild Erstliga Fußball FC Arsenal
ምስል picture-alliance/Back Page Images

ስፖርት ታኅሳስ 24 ቀን 2009 ዓ.ም.

በትውስታ የዛሬ 36 ዓመት ነጎደ። ወደ ሌኒን ስታዲየም። ሞስኮ ኦሎምፒክ፤ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር 1980 ዓመት። ኬንያውያን በማይታወቁበት በወቅቱ የረዥም ርቀት ውድድር ገናኖቹ አውሮጳውያን ነበሩ። ለኢትዮጵያውያን ግን ተንበርክከዋል። በሞስኮው ኦሎምፒክ በዐሥር ሺህም ሆነ በአምስት ሺህ የሩጫ ውድድሮች አውሮጳውያኑ እጅ ሰጥተዋል።

በሁለቱም ውድድሮች ወርቆቹን ለሻምበል ምሩጽ ይፍጠር አስረክበዋል። በሞስኮው ኦሎምፒክ ውድድር 2ኛ እና 4ኛ የወጡ፤ ለምሩጽ ድልም ድጋፍ ያደረጉ ታሪክ የማይረሳቸው ሁለት ኢትዮጵያውያን ተወዳዳሪዎች አሉ። አትሌት መሐመድ ከድር እና ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ ከሻምበል ምሩጽ ይፍጠር ጋር  ጓደኝነታቸው የረዥም ጊዜ  ነው። በበርካታ ውድድሮች ላይም አንድ ላይ ተካፍለዋል። ከሀገር ውስጥ አንስቶ እስከ ሞስኮ ኦሎምፒክ ድረስ ከሻምበል ምሩጽ ጋር አብሮ የተወዳደረውአሰልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ  በሞስኮው ኦሎምፒክ የ10,000 ፉክክር ምሩጽ «ያን ትልቅ ዉጤት እንዲያመጣ በጋራ አብረን ያከናወንነው» ብሏል። «ምሩጽ አንተ ዝም ብለህ ትከታተላለህ፤ 1 ዙር ሲቀር ፈጣን ስለሆንክ ትወጣለህ እስከዛ ጠብቅ» ሲል አሰልጣኝ ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ የ1980 የሞስኮ አሎምፒክን ያስታውሳል። 

Äthiopien Trauerfeier Athlet Miruts Yifter
ምስል DW/Y. Gebre-Egziabher

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዛሬ በአጠቃላይ ስድስት ጨዋታዎች ነው የሚከናወኑት። ላይስተር ሲቲ ከሚድልስቦሮው ያደረገው ጨዋታ ያለምንም ግብ ተጠናቋል።

43 ነጥብ ይዞ በደረጃ ሠንጠረዡ ሁለተኛ የሚገኘው ሊቨርፑል ከሰንደርላንድ ጋር ያካሄደው የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ለቀረጻ ስቱዲዮ እስከገባንበት ሰአት ድረስ አንድ እኩል ነበር። ለሊቨርፑል የመጀመሪያዋን ግብ በ20ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ዳንኤል ስቱሪጅ ነው። ብዙም ሳይቆይ በ25ኛው ደቂቃ ላይ ሰንደርላንድ ያገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ዴፎ ከመረብ አሳርፏል። በ72ኛው ደቂቃ ላይ ሴዶ ማኔ ለሊቨርፑል ሁለተኛዋን ግብ ሲያስቆጥ ዴፎ እንደ መመጀመሪያው አጋማሽ በፍጹም ቅጣት ምት ሁለተኛ ግብ ከመረብ አሳርፏል። በዚህም ጨዋታው 2 ለ2 ተጠናቋል። ማንቸስተር ሲቲ ከበርንሌይ 2 ለ1፤ ኤቨርተን ከሳውዝሀምፕተን  3 ለ0 እንዲሁም ዌስት ብሮሚች ከሁል ሲቲ 3 ለ1 ወጥተዋል።

ለዛሬ ቀጠሮ ከተያዘላቸው ጨዋታዎች መካከል ማንቸስተር ዩናይትድ ከዌስትሀም ዩናይትድ ጋር የሚያካሂደው ጨዋታ ብቻ ይቀራል። ጨዋታው ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ይጀምራል። መሪው ቸልሲ ተስተካካይ ጨዋታውን የፊታችን ረቡዕ ከቶትንሀም ጋር ያከናውናል። 

ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው የኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ስምንተኛ ዙር የእግር ኳስ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን 1 ለo ድል በመንሳት ነጥቡን 14 ማድረስ ችሏል።  በሦስተኛነ ደረጃ ላይ  ከሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚበለጠው በግብ ልዩነት ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ በደጋፊዎች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም የመጀመሪያው አጋማሽ ግን ደከም ያለ አጨዋወት የታየበት ነበር። ቡናዎችን ለድል ያበቃውን ግብ በ26ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ ያሳረፈው ናይጄሪያዊው የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ኤኮ ፊቨር እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ በድረ-ገጹ ዘግቧል። መሪው ደደቢት እና አዳማ እኩል 17 ነጥብ ሲኖራቸው ልዩነታቸው የግብ  ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ