1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያና መገናኛ ብዙኀኗ

ዓርብ፣ ሐምሌ 5 2005

በሶማሊያ የግል መገናኛ ብዙኀኗ ቁጥርከቀድሞው እየጨመረ በመሄድ ላይ ነው ። የጋዜጠኞች ቁጥርም አድጓል ። በተለይ የመዲናይቱ የመቅዲሾ ነዋሪዎች የሚያዳምጡ የሚያዩዋቸው የቴሌቪዥንና የራድዮ ጣቢያዎች የሚያነቧቸው ጋዜጦችም በዝተዋል ። የሶማሊያ መገናኛ ብዙኀን ስርጭቶች አሁን ውጭ ላሉ ሶማሊያውያንም እየደረሱ ነው ።

https://p.dw.com/p/1975t
ምስል picture alliance / dpa

የሶማሊያ መዲና መቅዲሾ ነዋሪዎች የሚያነቧቸው ጋዜጦች ቁጥር አሁን ወደ 6 ተጠግተዋል ። የራድዮ ጣቢያዎቹ ቁጥር 23 ፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ ደግሞ 9 ደርሰዋል ። የጋዜጣ የቴሌቪዥንና የራድዮ ጣቢያዎቹ ቁጥር አሸባብ መቅዲሾን ያስተዳድር በነበረበት ወቅት ከነበሩት በእጥፍ አድገዋል ። ሶማሊያዊው ጋዜጠኛ መሐመድ ኦማር ሁሴን መቅዲሾ የሚሰራ ጋዜጠኛ ነው ። መሐመድ እንደሚለው ከግል መገናኛ ብዙኀን ባለቤቶች አብዛኛዎቹ ውጭ የሚኖሩ ሶማሊያውያን ናቸው ።

« መቅዲሾ ውስጥ በውጭ ዜጎች የተያዘ የመገናኛ ብዙኀን የለም ። መገናኛ ብዙኀኑ እዚህ መቅዲሾ በሚገኙ የአገሬው ሰዎች ነው የተቋቋሙት ። የአንዳንዶቹ ባለቤቶች መቀመጫ ደግሞ አውሮፓ ነው ። ከባለቤቶቹ አብዛኛዎቹ ውጭ አገር የሚኖሩ ሶማሌዎች ናቸው ። »

ሌላው ሶማሊያዊ ጋዜጠኛ ሁሴን አዌስ እነዚህ ሶማሌዎች አሁን ያለውን አጋጣሚ በመጠቀም የእስከዛሬውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት እየሞከሩ ነው ይላል ።

Karte Somalia mit Jubaland und Puntland

«ባለፉት 20 ዓመታት መገናኛ ብዙሃን በመንግሥት እጅ ነበር ። አሁን ግን ገንዘብ ያላቸው ሶማሌዎች በመስኩ የተሠማሩት ስለሃገሪቱ እንቅስቃሴ ለህዝቡ ለመዘገብ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ ስላገኙት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ነው ። »

ጋዜጠኛ ሁሴን አዌስ መገናኛ ብዙኀኑ የሚያሰራጭዋቸውን መረጃዎች ይዘት ያን ያህል መጥፎ የሚባል አይደሉም ሲል ጋዜጠኛ መሐመድ ደግሞ የሶማሊያ የግል መገናና ብዙሃን ብዙ ይጎላቸዋል ብሏል ። እንደ መሐመድ የሚያሰራጩት ዜናም ሆነ ዝግጅት በአብዛኛው ሙያው የሚጠይቀውን ደረጃ አያሟሉም ። ባለቤቶቹም በሥራው ላይ ተፅእኖ ያደርጋሉ ።

« መገናኛ ብዙኀኑ በሙሉ ማለት ይቻላል ከዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ብዙኀን ደረጃ ጋር ሲነፃፀር በጣም ደካማ ናቸው ። ደካማ ናቸው ስል የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርን ጠብቀው አይሠሩም ማለቴ ነው ። ለምሳሌ የአንድ ራድዮ ጣቢያ ባለቤት ዜናው እንዲቀርብ በሚፈልግበት መንገድ ነው ጋዜጠኛው ዜናውን የሚሠራው ። የዜናውን ይዘት የሚወስኑት ዘጋቢዎቹ ሳያሆኑ የራድዮ ወይም የቴሌቪዥን ጣቢያው ባለቤቶች ናቸው ። የዜናው አርትኦት የሚሠራው በጋዜጠኞች ሳይሆን በጣቢያው ባለቤቶች ነው ። አፍራሽ ይሁን ገንቢ ጉዳያቸው አይደለም ። »

Bildergalerie Muttertag International Somalia
ምስል Mohamed Abdiwahab/AFP/Getty Images

በሶማሊያ የራድዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥር እንደማደጉ ሁሉ የጋዜጠኞችም ቁጥር ጨምሯል ። የሶማሊያ ጋዜጠኞች ሕብረት እንደሚለው በመቅዲሾ ብቻ ከ6 ዓመት በፊት 100 የነበረው የጋዜጠኞች ቁጥር አሁን ወደ 300 ከፍ ብሏል ። እውቅና የተሰጠው የጋዜጠኖች ማሰልጠኛ በሌለባት በሶማሊያ ለጋዜጠኞቹ ቁጥር መጨመር አንጋፋ ጋዜጠኞች የሚያከናውኑት ተግባር አስተዋጽኦ ማድረጉን መሐመድ ያስረዳል ።

« መቅዲሾ ውስጥ ልምድ ያላቸው በዚያድ ባሬ ዘመን ይሠሩ የነበሩ አንጋፋ ጋዜጠኞች አሉ ። እነዚህ ጋዜጠኞችም ፣ ጋዜጠኛ መሆን የሚፈልጉ ሶማሌዎችን የሚያሠለጥኑበት ጣቢያዎች አሏቸው ። በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ መገናኛ ብዙኀን እስከ 6 ወር ለሚበልጥ ጊዜ እየተለማመዱ በሙያው የሚሠማሩም አሉ ። ሆኖም በሶማሊያ እውቅና የተሰጠው የጋዜጠኞች ማሠልጠኛ የለም ። »

Somalia Mogadischu US-Militär 1992
ምስል Michel Gangne/AFP/GettyImages

ጦርነት ባደቀቃት ሶማሊያ የሚገኙ መገናኛ ብዙኀን ተፈላጊነት በሃገር ውስጥ ብቻ አይደለም ። በተለያየ የዓለም ክፍል የሚገኙ ሶማሌዎችም ዘመኑ ባመጣቸው ቴክኖሎጂዎች የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀንን ይከታተላሉ ። ይህም እንደ ሁሴን አዌስ ለመገናኛ ብዙሃኑ ቁጥር መጨመር አንዱ ምክንያት ነው ።

« በሶማሊያ ራድዮ ጣቢያዎች ብቻ ሳይሆኑ ድረ ገጾችም እየበዙ ነው ። ምክንያቱም ዜናው ሃገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ሃገር ውስጥም ሆነ ውጭ የሚሠሩ ሶማሌዎች በቀጥታ ሥርጭት አማካይነት በሃገራችን ስላለው እንቅስቃሴ እንዲያውቁ ለማድረግ ነው ። ለዚህ ነው አሁን እየበዙ የሄዱት ። »

የሶማሊያ መገናና ብዙኀን ቁጥር ማደግ እስየው ቢያሰኝም ፣ ሁሌም ከመገደል ሥጋት ጋር የሚሠሩት የሃገሪቱ ጋዜጠኞች ዕጣ ፈንታ አሳዛኙ ገፅታ ነው ።

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ