1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሊያና አሜሪካ

ሰኞ፣ ጥር 13 2005

አሁን አዲስ የተባለችዉ ሶማሊያ አዲስ እንዳልሆነች፥ እንዳልነበረች ሁሉ፥ አዲስ የተባለዉ ግንኙነትም አሮጌ ነዉ።የዋሽግተንና የሶማሊያ መሪዎች አሮጌዋን ሶማሊያና አሮጌዉን ግንኙነት «አዲስ» ለማለታቸዉ ግን ሠበብ ምክንያት አላጡም።

https://p.dw.com/p/17OYq
WASHINGTON, DC - JANUARY 17: Secretary of State Hillary Clinton (R) shakes hands with Somali president Hassan Sheikh Mohamud during a news conference on January 17, 2013 in Washington, DC. Secretary Clinton announced that the United States would recognize the Somali government for the first time in over 20 years, since the shooting down in Mogadishu of two American Black Hawk helicopters. (Photo by Justin Sullivan/Getty Images)
ሐሰንና ክሊንተንምስል Getty Images


210113
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦቦማ ትናንት በግል በገቡት ቃለ-መሐላ፥ ዛሬ በይፋ አዲስ በሚረከቡት፣ አሮጌ-ሥልጣቸዉ አዲስ የሚያዋቅሩት ካቢኔ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊተንን አያካትትም።የአሮጌዉ ፕሬዝዳት አዲስነት፣ የአሮጌይቱ ሚንስትር ጡረታ በሚታወጅበት ዋዜማ-ሐሙስ ግን ክሊንተን የሶማሊያን አዲስነት አወጁ።አሮጌዉ የሞቃዲሾና የዋሽግተን ግንኙነት እንዳዲስ ተጀመረ።አዲሱ የሶማሊያ መሪ በዋሽግተኖች መታወቅ፣ መወደሳቸዉ ለግላቸዉ ኩራት፣ የተገባላቸዉ ቃል ደግሞ ለሕባቸዉ ጥሩ ተስፋነቱ አላጠያየቀም።የቃል፥ ኩራት፥ ተስፋዉ ገቢራዊነት እንጂ አነጋጋሪዉ።ላፍታ እንነጋገር።
                    
ሐበሾች፣ ሮሞች፣ አረቦች፣ ቱርኮች አዉሮጶች አዲስ እያሏት አሮጌ አድርገዋት፣ አሮጌ-እያሏት አዲስ እንዳደረጓት፥ ገንብተዉ-እያፈረሷት፣ ገድለዉ እየሞቱባት አመታት ላስቆጠረችዉ ሶማሊያ ጥንትም፣ ድሮም፣ ዘንድሮም አሮጌም-አዲስምነች።ወይም ሁለቱንም አይደለችም።

በሁለት ሺሕ ዘጠኝ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) አዲስ የተመሠረተዉ የፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ መስተዳድር የአዲስና አሮጌን ልዩነት አጣምራ የያዘችዉን ሐገር አዲስ ለማድረግ የወሰነዉ ወይዘሮ ሒላሪ ክልተን በቀደም እንዳሉት ሥልጣን እንደያዘ ነበር።
                  
«ጥር ሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ሥገባ አል-ሸባብ አብዛኛዉን ሞቃዲሾን፥ደቡብና ማዕከላዊ ሶማሊያን ይቆጣጠር ነበር።ተጨማሪ ግዛቶችን የሚይዝ መስሎም ነበር።የሶማሊያ ሕዝብ ለርካታ ዓመታት እንደተጠቃ እንደተገለለ ነበር።ይሕን ለመለወጥ ፈለግን።»

ሶማሊያ የዛሬ መልክና ቅርፅ ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የተቀየሰዉ ግን በአስራ-ዘጠነኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን የብሪታንያና የኢጣሊያ ቅኝ ገዢዎች መሐመድ አብደላሕ ሐሰንን የመሳሰሉ የሐገሬዉ ተወላጆች የመሩትን ጠንካራ የፀረ-ቅኝ ገዢ ተፋላሚ ሐይልን ደፍልቀዉ ምሥራቅ አፍሪቃዊቱን ሐገር ሲሸነሽኗት ነበር።

በቅኝ አገዛዝ ዘመን ለሁለት ተገምሠዉ የነበሩት ሶማሌዎች ነፃ ወጥተዉ፥ ዳግም ተዋሕደዉ፥ ነፃ ባሉት አሐዳዊ መንግሥት ሲተዳደሩ ሶማሊያ እንደገና አዲስ መባሏ አልቀረም።የጉዟዋ አቅጣጫ ግን ቅኝ ገዢዎች ከቀየሱላት ጎዳና የወጣ አልነበረም።የሞቃዲሾና የዋሽግተን ግንኙነት የተጀመረዉም ያኔ ነበር።ግንኙነቱ ከመፍካት፥ መደብዘዙ፥ ከመጠንከር፥ መመንመኑ የአምባሳደሮች ልዉዉጡ ከመቋረጥ-መቀጠሉ በስተቀር አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳት ሐሰን ሼክ መሐሙድ ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት እንደነበረ ነበር።
                    
«ዩናይትድ ስቴትስና ሶማሊያ፥ ሶማሊያ ነፃ ከወጣችበት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ግንኙነት አላቸዉ።የረጅም ጊዜዉ ግንኙነት ምልክቶችና ምሳሌዎች አሁንም ሶማሊያ ዉስጥ ይታያሉ።የአሜሪካ የሠላም ጓዶች ሶማሊያ ዉስጥ የገነቧቸዉ ትምሕር ቤቶች አሁንም ድረስ አገልግሎት ይሰጣሉ።»

እና አሁን አዲስ የተባለችዉ ሶማሊያ አዲስ እንዳልሆነች፥ እንዳልነበረች ሁሉ፥ አዲስ የተባለዉ ግንኙነትም አሮጌ ነዉ።የዋሽግተንና የሶማሊያ መሪዎች አሮጌዋን ሶማሊያና አሮጌዉን ግንኙነት «አዲስ» ለማለታቸዉ ግን ሠበብ ምክንያት አላጡም።

በሺሕ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ዘጠኝ በመፈንቅለ መንግሥት ቪላ ሞቃዲሾን የተቆጣጠሩት ሜጄር ጄኔራል መሐመድ ዚያድ ባሬ ሶማሊያን እንደቀዳሚ-ተከታዮቻቸዉ፥ እንዲሕ እንዳሁኑም «አዲስ» ብለዋት ነበር። ባሬ አንዴ ሶሻሊስትነትን፣ አንዴ አረብነትን፣ ሌላ ጊዜ ካፒታሊስትነትን ባፈራረቁባት ቁጥር፣ አሮጌ አዲስ እንዳሏት፣ ትንሽነቷን አስረስተዉ ኢትዮጵያን ወረዉ በታላቅነት እንዳሳበጧት ቁል-ቁል ነዷት።

አሜሪካዊዉ አምባሳደር ጀምስ ኬየፍ ቢሾፕ ከዋሽግተን ሞቃዲሾ የገቡት ዚያድ ባሬ በያኔ ጠላታቸዉና የጠላቶቻቸዉ ደጋፊ በኢትዮጵያዉ ፕሬዝዳት በኮሎኔል መንግሥቱ ሐይለ ማርያም ቋንቋ «አፍንጫቸዉን» ተመተዉ «እብጠታቸዉ በሟሸሸበት» ወቅት ነበር።

ቢሾፕ-እንዲያዉ ገደ ቢስ ብጤ ናቸዉ።ወደ ሞቃዲሾ ከመቀየራቸዉ በፊት በላይቤሪያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ነበሩ።የፕሬዝዳት ሳሙኤል ኬንዮ ዶ አገዛዝን በሐይል ለማስወገድ የሚፋለሙት የያኔዎቹ አማፂያን የሞንሮቪያን ቤተ-መንግሥት ለመቆጣጠር ርዕሠ-ከተማይቱን ሲያጠቁ አሜሪካዊዉ አምባሳደር  ጓዝ-ሰነዳቸዉን ጠቅልለዉ፥ ረዳት የበታቾቻቸዉን አስከትለዉ ሞንሮቪያን ጥለዉ ዋሽንግተን ገቡ።ሐምሌ ነበር።1991።

የአምባሳደር ቢሾፕ ዳግም ሹመት ልክ እንደ ሞንሮቪያ ከዛሬ-ነገ አማፂያን ተቆጣጠሯት ከምትባለዉ ሞቃዲሾ ነበር።የተፈራዉ አልቀረም።«ገደ-ቢሱ» አምባሳደር ትልቂቱ ሐገራቸዉ በመላዉ ዓለም ከነበሯት የኤምባሲ ፅሕፈት ቤቶች ሁሉ በስፋት ከትልቁ ኤምባሲ በገቡ በወራት እድሜ፥ ሞቃዲሾን ጥለዉ መዉጣት ግድ ሆነባቸዉ።ጥር 1991።

ቢሾፕ የሌሎች ሐገራት አቻዎቻቸዉን፥ አማካሪ፥ ረዳት የበታቾቻቸዉን በጥቅሉ ከሁለት መቶ ሰማንያ ከሚበልጡ የዉጪ ዜጎች ጋር ጥለዉት ከወጡ ወዲሕ ያ-በሰማንያ ጋሻ መሬት ላይ የተንጣለለዉ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ አምባሳደር የሚባል አሜሪካዊ ገብቶበት አያዉቅም።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተንና ፕሬዝዳት ሐሰን መሐሙድ በቀደም የሁለቱን ሐገራት ግንኙነት አሮጌ-ከማለታቸዉ እኩል አዲስ የማለታቸዉ አንዱ ምክንያት አምባሳደር ለመለዋወጥ መወሰናቸዉን ነዉ።

ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሒላሪ ክሊንተን እንዳሉት ግን ሶማሊያንም ሆነ የዋሽግተን-ሞቃዲሾን ግንኙነት አዲስ የሚያሰኘዉ ብዙ አዳዲስ ምክንያት፥ ምልክቶች አሉ።ተስፋም ጭምር።
                  
«ለዚያ ለተሻለ ጥሩ መፃኤ ዕድል መሠረት መጣሉን አይተናል።ዛሬ ደግሞ ወደ ጥሩዉ የሚያደርሰንን እርምጃ ወስደናል።ዩናይትድ ስቴትስ ከ1991 ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሶማሊያ መንግሥት ዕዉቅና መስጠቷን ሳዉጅ በደስታ  ነዉ።»

ክሊንተን ለሶማሊያና ለሶማሊያዎች የተሻለ ጥሩ መፃኤ ዕድል ያሉት ተስፋ የአሸባብ ከትላልቅ ከተሞች መባረሩ፥አዲስ የሶማሊያ ሕገ-መንግሥት መፅደቁ፥ ምክር ቤት መሰየሙ፥ ጠቅላይ ሚንስትርና ፕሬዝዳት መመረጣቸዉን ነዉ።ሶማሊያ ከዚሕ የደረሰችዉ ደግሞ የኦባማ መስተዳድር ሥልጣን በያዘ ማግሥት በቀየሰዉ መርሕ መሠረት ከተቀረዉ ዓለም በጣሙን ከአፍሪቃ ሕብረት ጋር ተባብሮ በመሥራቱ እንደሆነ ክሊንተን አስታዉቀዋል።

በርግጥም ለዉጡ፥ የለዉጡ ምክንያትም እዉነት ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ለፕሬዝዳት ሐሰን መሐሙድ መንግሥት እዉቅና መስጠቷ ደግሞ ISS በሚል ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ አንድሪዉ አሳሞሐ እንደሚሉት ለሶማሊያ መንግሥት ታላቅ ድል ነዉ።
                    
«እዉቅና መሠጠቱ ራሱ በአዲሱ የሶማሊያ አመራር ላይ የሆነ ፍላጎትና ተስፋ መኖሩን በግልፅ የሚናገር ነዉ።ይሕ መንግሥት በተመሠረተበት ወቅት የሚገጥመዉ ፈተና ሲበዛ አሳሳቢ ነበር።የሶማሊያን ያለፈ ታሪክና ችግር የሚያዉቁ በርካታ ወገኖች የአዲሱን መንግሥት ፅናት እስከ መጠራጠር ደርሰዉም ነበር።ሥለዚሕ አሁን (አሜሪካ) ዕዉቅና መስጠቷ ሌሎች ተዋኞችም በሐገሪቱና በአዲሱ አመራር ላይ ያላቸዉን ተስፋ እንዲያፀኑ  ያደርጋል።»  

ዚያድ ባሬን ከስልጣን ያስወገዳቸዉ የአማፂያን ዉጊያ የድሕረ-ነፃነትዋንም፣ የዚያድ ባሬዋንም አንዲት ግን ብዙ-ጊዜ ብዙ ዓይነት አዲስ፣ አሮጌ የተባለችዉን ሶማሊያን እስከ ዛሬ ከምትዳክርበት እልቂት ፍጅት የዶለ፣ ከነፃት በሕላ አሮጌ የነበረዉን የተከፋፈለች ሶማሊያን እንዳዲስ ያሰፈነም ነዉ።

የዩናይትድ ስቴትስና የተባባሪዎችዋ ድጋፍ፥ የአፍሪቃ ጦር ዉጊያ የቀድሞዉን የዩኒቨርስቲ መምሕር ለፕሬዝዳትነት ያበቃ ለዉጥ ማምጣቱ አላጠራጠረም።ዩናይትድ ስቴትስ አሸባብን ለሚወጋዉ የአፍሪቃ ሕብረት ጦር 650 ሚሊዮን ዶላር ረድታለች።ለሶማሊያ ፀጥታ አስከባሪዎች 130 ሚሊዮን ዶላር ሰጥታለች።ባለፉት ሁለት ዓመታት ለሰብአዊና ለልማት ርዳታ ከአራት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ አዉጥታለች።

ለሶማሊያ ስደተኞች መርጃ ደግሞ ከሁለት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ረድታለች።ሶማሊያ ግን ዛሬ አዲስ ከተባለች አዲስ የሆነችዉ ዚያድ ባሬን-ከሥልጣን ስታስወግድ፣ ከርስ በርስ ጦርነነት ስትዘፈቅ፣ ከሁሉም በላይ በነፃነት ማግሥት አሮጌ በነበረዉ ልዩነት እብዙ ቦታ ስትሸነሸን ነዉ።ሺሕ ዘጠኝ መቶ ዘጠና አንድ።ዛሬም እንደተከፋፈለች ነዉ።

ፕሬዝዳት ሐሰን መሐሙድ የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን የያዙት በጎሳ መሪዎች፥ በፖለቲከኞች፥ በተዘዋዋሪ ይሁን እንጂ ሶማሊያን ባደቀቀዉ ጦር በተሳተፉ በጦር አበጋዝ ድጋፍ እንጂ በሶማሊያ ሕዝብ ቀጥታ ድምፅ ተመረጠዉ አይደለም።

ከሐሰን በፊት አብዲ-ቃሲም ሳላድ፥ አብዱላሒ ዩሱፍ፥ ሼሕ ሸሪፍ ሼሕ አሕመድ የሽግግር ከሚል ቅፅል ጋር ለፕሬዝዳትነት የተመረጡትም እንደዚያዉ ነበር።ሐሰን የፕሬዝዳትነት ሥልጣኑን የያዙት ግን ዩናይትድ ስቴትስና ተከታዮቿ አሸናፊና ተሸናፊ ባለበየበት በአፍሪቃኒስታኑ የአስር-ዓመት ጦርነት በተሰላቹበት፥ የአረብ-ሕዝባዊ አመፅን ሒደት-ዉጤት በሚያስታምሙበት፥ በምጣኔ ሐብት ኪሳራ በደቀቁበት፥ ደካማ-ይሁን ጠንካራ፥ ብቻ ሁነኛ ታማኝ ደጋፊ በሚሹበት ወቅት መሆኑ በርግጥ ልዩ ነዉ።አዲስም ጭምር።
                         
ዩናይትድ ስቴትስ በልዩ ትኩረት በምትፈልገዉ ልዩ ሰዓት የተመረጡት ፕሬዝዳት ከሚመሯት ሶማሊያ ጋር የሚኖራት ግንኙነት ደግሞ «አንዱ የሌላዉን ሉዓላዊነት በሚያከብሩ በሁለት ሐገራት መካካል ያለ» -ግንኙነት ነዉ።አሉ ክሊንተን በቀደም።
                     
«ዛሬ የማዕዘን ድንጋይ የተጣለበት ነዉ።የጎዞዉ መጨረሻ አይደለም።ከዚያ ለመድረስ ግን መሠረታዊ እርምጃ ነዉ።የሶማሊያን ሉዓላዊነት እናከብራለን።በጋራ መሥራት ሥለምንችልበት ሁኔታ ግልፅ እና የአቻ-ለ-አቻ ዉይይታችንን እንቀጥለለን።»

በዩናይትድ ስቴትስ የጦር አዉሮፕላኖች የታጀቡት የፈረንሳይ ሔሊኮብተሮች የሶማሊያን የአየር ክልል ጥሰዉ ታጋች ሰላይ ለማስለቀቅ ከአሸባብ ጋር ዉጊያ የገጠሙት ግን ፕሬዝዳት ሐሰን መሐሙድ ወደ ዋሽግተን ለመጓዝ ሻንጣቸዉን ሲቀረቅቡ ነበር።የ«ሉዓላዊት» ሐገራቸዉ የአየር ክልል መጣሱን ያዉቁት ይሆን? «የሉዓላዊት» ሐገራቸዉን ግዛት፥ የ«ሉዓላዊ» መንግሥታቸዉን ሕልዉና የሚጠብቀዉ የዩጋንዳ፥ የብሩንዲ፥ የጅቡቲ፥ የኬንያና የኢትዮጵያ ጦር ነዉ።

ምናልባት ከነገ-ጀምሮ የቀድሞዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር የሚባሉት ክሊንተን የገቡትን ቃል፥ ገቢራዊነት፥ የሰጡት ተስፋ እዉንነት እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ለማየት-አይችሉም።የሶማሊያ የሉዓላዊነት ብያኔ ከማጠያየቁ እኩል ግን የሐገር መሪነትን ሸክም ከሰወስት ወር በላይ የማያዉቁት ሐሰን መሐሙድ አዲስና አሮጌን በማታዉቀዉ ሐገር አዲስ ተስፋ የፈነጠቀዉን ቃል-ተስፋ ገቢር ማድረጋቸዉን ለማየት በርግጥ ጊዜ መስጠት ግድ ነበር።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ

 


 




 

Ugandan African Union peacekeepers patrol the outskirts of Mogadishu on September 12, 2012. Somalia's president survived an assassination bid today, just two days into his new job, when bomb blasts claimed by Islamist rebels rocked the Mogadishu hotel where he was meeting Kenya's foreign minister. Al-Qaeda linked Shebab insurgents claimed responsibility for Wednesday's attack in which two blasts rocked the hotel where the new president was staying. AFP PHOTO/SIMON MAINA (Photo credit should read SIMON MAINA/AFP/GettyImages)
የዩጋንዳ ጦር-ሞቃዲሾ 2012ምስል MICHELE SIBILONI/AFP/Getty Images
Refugee Children collecting scrape materials in a place full of waste in Mogadishu on July 20, 2012 so as to sell and the money they get to manage their needs; Sanitation in Somalia in one of the poorest one in the world, the rubbish can be gotten in every where in the city and it causes diseases reach to the lowest category living families who can?t get clean water.AFP PHOTO/ABDIRASHID ABIKAR (Photo credit should read ABDIRASHID ABIKAR/AFP/GettyImages)
ሞቃዲሾምስል ABDIRASHID ABIKAR/AFP/GettyImages
A U.S. Marine stands on a truck as they drive through the "Green Line" dividing north and south Mogadishu in Somalia 12 December 1992 in the first food distribution convoy secured by U.S. troops. The U.S. is sending some 30,000 troops to protect the food convoys. (Photo credit should read MICHEL GANGNE/AFP/GettyImages)
የአሜሪካ ጦር-ሞቃዲሾ 1992ምስል Michel Gangne/AFP/GettyImages