1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማልያና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ

ሐሙስ፣ መጋቢት 24 2007

በሶማልያ የፖለቲካው ውዝግብ ገና መላ አልተገኘለትም፣ ኧል ሸባብ በበኩሉ ከዕለት ወደ ዕለት የሽብር ተግባሩን አጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ መፍትኄ ነው ብሎ ያተኮረው በአብራሪ የለሽ የጦር አይሮፕላኖች (Drones)ጭምር በሚታገዘው

https://p.dw.com/p/1F2B9
ምስል picture-alliance/epa/S. Y. Warsame

በወታደራዊው ርምጃ ላይ ነው። የአውሮፓው ሕብረት በበኩሉ፤ የሶማልያን ጦር ሠራዊት በፀጥታ አጠባበቅ ረገድ ብቁ ይሆን ዘንድ በማሠልጠን ላይ ይገኛል። የአውሮፓው ሕብረት ባሠማራው የኢጣልያ ቡድን ውስጥ የፖለቲካ አማካሪ በመሆን ይሠሩ ዘንድ ከጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ተልከው የነበሩትና በ 5 ወራት ውስጥ ተስፋ ቆርጠው ያቋረጡት ስቴፋን ብሩዑነ ፣ አውሮፓ፤ ዩናይትድ ስቴትስና በአጠቃላይ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፣ የመቅዲሹ ጉዳይ እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል ይላሉ ።

Kindersoldat vor Kämpfen in Somalia
ምስል picture-alliance/dpa/epa Albadri

ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ፣ እምን ላይ ነው ያልተሣካለት ወይም የፈለገውን ማከናወን የተሣነው? እምን ላይ ይሆን? በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ፣ በሰላምና የጸጥታ ጉዳይ ጥናት(IPSS)ተጋባዥ ፕሮፌሰር ፣ በጂቡቲ የ ኢጋ ድ ባልደረባ በመሆን እንዲሁም ፤ በመጨረሻ መቅዲሹ ውስጥ የአውሮፓው ሕብረት የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው ለሠሩት ለእሽቴፋን ብሩዑነ በመጀመሪያ የቀረበላቸው ጥያቄ ነበር።

«የሁኔታው ፍጹም አስቸጋሪነት በግልጽ የሚታየው ፤ መደራደር የሚያስችሉትን ጉዳዮችና በውጭ የሚገኙ የጉዳዩ ተከታታዮች ይዞታ በጥሞና ሲመረምሩት ነው። በጦር ኃይል ተጠናክሮ በሚጠበቀው አይሮፕላን ማረፊያ ፣ አሸዋ የተሞሉ ዶንያዎች በተደረደሩበት ፣ የተባበሩት መንግሥታት ተወካዮች ተጠጋግተው መቀመጥ ፣ ግድ ይሆንባቸዋል። ወደ መቅዲሹ ወረድ ብሎ ለማጥናት ፣ ስለተመክሮም ለመናገር የማይቻል ነገር ነው። እኔ በበኩሌ፤ በ 5 ወራት ቆይታዬ አንድ ጊዜ ብቻ ነው ለ 2 ሰዓት ከተማ ውስጥ «ቪላ ሶማልያ» በተሰኘው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አንዳንድ ነገሮች ለመታዘብ የቻልሁ።»

በሶማልያ ፤ ባፋጣኝ ሰላም እንዲሠፍን ማድረግ የሚቻልበት ዕድል የተመናመነ ነው። ዘወትር የኃይል ርምጃ በሚንጸበረቅበት ከተማም ሆነ አገር የሁሉን ጥቅም ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መፍትኄ ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ ፣ ከእነምልክቱም አይታይም ። ዋናው ተቀዳሚ ችግር የጸጥታ አጠባበቅ ነው፤ ይሁንና እሽቴፋን ብሩዑነ እንደሚሉት ፤ ያለፖለቲካ መፍትኄ ሌላውን ችግር መፍታት ያስቸግራል።

Somalia Sicherheitskräfte in Mogadischu
ምስል Reuters/F. Omar

«የውጭ ተደራዳሪዎች ስላላቸው መላ የመሻት ጥረት በአጠቃላይ ማለት የምችለው ወሰን ያለው ፤ የተገደበ ነው። በሶማሌዎች መካከል፤ ያለውን ውዝግብ ለመፍታት፤ በደፈናው መላ የመሻቱ አጋጣሚ የተለያዩ ሐሳቦችን ግምት ውስጥ ማስገባቱ በአጠቃላይ መፍትኄ የማግኘቱ ነገር ከባድ ነው። በደፈናው ፤ ሁሉም ግምት ውስጥ የገባ፤ ገደብ የተጣለበት ነው።»

ዋናዎቹ የሶማልያ ችግሮች በእርግጥ የትኞቹ ናቸው ? መፍትኄዎቹስ ምንድን ናቸው ይላሉ?

«ዐበይት የፖለቲካ ነጥቦቹ በግልጽ የሚታወቁ ናቸው። ፀረ ሽብር ትግል፣ ሥርዓት አልበኝነትና የመሳሰሉት ናቸው። በሌላ በኩል፣ በእርግጥ 20 ዓመት የተደረገው ጉዞ ድርድሩ የፖለቲካ ፍሬ አለማፍራቱን ነው የሚያሳየው። እኔ እንደማስበው በአጭር ጊዜ ውስጥም የሚሆን አይደለም። ከእያንዳንዱ ተደራዳሪየሚሰነዘሩ ሐሳቦች፤ ወደፊትም የሚቀርቡ ፣ ከተቃዋሚዎች የሚቀርቡ እርስ በርስ የሚጣረሱ ሐሳቦች ፤ ከዚህ ሌላ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በይፋ ከሚያራምደው የሽምግልና ጥረት ባሻገር ፣ አሸባብን መውጋት ያሻል፣ ካስፈለገም፣ በአብራሪ የለሽ አይሮፕላን ጭምር የሚል ሲሆን ከኬንያ በኩል ደግሞ ለዘብ ያለ አቋም ያላቸውን የአሸባብ አባላት ለማነጋገር ሙከራ መደረጉ የታወቀ ነው። የእኔ ሐሳብ፤ ረጅም ጊዜ ከኢጋድ ጋር ሠርቼአለሁ ፣ ሐሳብም ተለዋውጬአለሁና «ያለጦር ሠራዊት መፍትኄ አይገኝም ግን ወታደራዊ መፍትኄ አይገኝም» የሚሰኝ አባባል አለ። የአሸባብ ደጋፊዎችን አባብሎ አሠላለፋቸውን እንዲያስተካክሉ ወይም እንዲለውጡ ማግባባት ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ --በጦር መሣሪያ ብቻ የሚለው ፍጹም መፍትኄ አያስገኝም።»

al-Shabaab Kämpfer in Somalia
ምስል picture alliance/AP Photo/Sheikh Nor

የ ኢ ጋ ድ የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ የነበሩት ፕሮፌሰር እሽቴፋን ብሩዑነ ፣ የውጭዎቹ ፤ ለምሳሌ ዩናይትድ ስቴትስና ና አውሮፓ ለሶማልያ መፍትኄ የሚበጅ ስልት ባይኖራቸው ኢ ጋ ድ የተሻለ ሸምጋይ ሆኖ ለውዝግቡ መላ የሚያገኝ ይመስሎታል ወይ ? ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ--

«ኢ ጋ ድ እንደ አንድ የአካባቢ ድርጅት በበነባቤ ቃል ይቻለዋል ማለት --ይቻል ይሆናል። ለሶማልያ ጉዳዮች መፍትኄ ለማግኘት ተጽእኖ የማሳደሩ ግፊት ውስንነት ያለው ነው። የ ኢ ጋ ድ ድርሻ ማወያያ መድረክ መሆኑ ነው።የፖለቲካ ውሳኔዎች ተጋሪ ሆኖ ግን ሰላም ማውረድ የሚቻለው አይመስለኝም።»

በመጋቢት 2008 በሕገ መንግሥቱ ላይ ውሳኔ-ሕዝብ ፤ ከዚያም በቀጣዩ ዓመት በመጸው ምርጫ እንዲካሄድ እቅድ አለ ። ይህ እቅድ የሚሠምር ይመስላል ወይ?

«የመጀመሪያውን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሶማልያ ለማካሄድ በአንዳንድ ቴክኒካዊ ችግሮች ሳቢያ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅet ጊዜ ማጓተት አይበጅም፤ እያለ ያስጠነቀቃል በሌላ በኩል በፖለቲከኞቹ ላይ ግፊት ማድረጉ ዋጋ እንዳለው ይታሰባል ነው የሚባለው»።

ተክሌ የኋላ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ