1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማልያና ያልተፈታው የግዛት ሉዓላዊነት ውዝግብ፣

ማክሰኞ፣ ሰኔ 25 2005

ሶማልያ በራሷ ቆማ ራሷን ማስተዳደር ከተሣናት ከ 20 ዓመታት በላይ መቆጠራቸው አይዘነጋም። በመቅዲሹ ፣ የፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሙሐሙድ አስተዳደር በሰፊ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ርብርብ የተቋቋመው ፣ ባለፈው መስከረም ወር እንደነበረ የሚታወስ ነው። የሼክ

https://p.dw.com/p/190Jq

ሐሰን ሼክ ሙሐሙድ ሥልጣን መሠረት ጊዜያዊውና ብዙ ዐበይት ጉዳዮችን ክፍት አድርጎ ያስቀመጠው ህገ-መንግሥት ነው። ይህ ደግሞ ዓለም አቀፍ ዕውቅና የተሰጠውን የመቅዲሹውን ማዕከላዊ መንግሥትና የሶማልያን አካባቢያዊ መስተዳድሮች የሚመለከት ነው።

ሶማልያ ፣ ከ 20 ዓመታት በላይ ተግባሩን ማካሄድ የሚችል ማዕከላዊ መንግሥት ስላልነበራት ፣አንዳንድ አካባቢዎች፣ ራስን ችሎ የመቆም አቅማቸውን አጎልብተዋል። ሰሜን ምዕራባዊቷ ሶማሊላንድ ፣ የራሷን ነጻ መንግሥት ካወጀች ዓመታት ተቆጠሩ። ከፊል ራስ ገዝ መስተዳደር ያላት ሰሜን ምሥራቃዊቷ ፑንትላንድ፣ በደቡብ ሶማልያ የሚገኘው ጁባላንድ የተሰኘው ሌላው የሶማልያ አካል ነጻነት ለማወጅ የሚያደርገውን እንቅሥቃሴም በጥሞና ነው የምትከታተለው።

እንደ ፑንትላንድ ፕሬዚዳንቱት አብዲራህማን ሙሐመድ ፋሮሌ የአቅድና የዓለም አቀፍ ተራድዖ ሚንስቴር ፣ ምክትል ሚንስትር አህመድ ኢብራሂም አብዲራህማንም፣ ማዕከላዊውን የመቅዲሹ መንግሥት ሲነቅፉ፤ ለአካባቢያዊ መስተዳድሮች ለፑንትላንድ፤ ባለፉት ወራት ለተቋቋመው ጁባላንድም እንዲሁ፤ ተገቢውን ከበሬታ አልሰጠም ነው ያሉት።

«የሶማልያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሙሐሙድ፤ የፌደራል ህገመንግሥቱን የሚያከብሩ ከሆነ፣ የአካባቢዎቹን ግዛቶች ግንባታ ማደፋፈር ነው የሚኖርባቸው። ነገር ግን ለዚህ መሰናክል ሲፈጥሩ ነው የሚስተዋሉት። የጁባላንድ የሀገር ሽማግሌዎች፤ አንድ ፕሬዚዳንት መርጠዋል። መንግሥታዊ መዋቅርም ዘርግተዋል። ይሁንና የመቅዲሹ መንግሥት የግዛቶቹን ተቋማት አልተቀበላቸውም ። ይህ አቋሙም ያሳስበናል። »

Konflikte in Somalia
ምስል Bettina Rühl

ጉዳዩ ውስብስብ ያለ ነው። ጁባላንድና ስልታዊ ጠቀሜታ ያለው ወደቡ ኪሳማዩ፣2 የጎሳ ጦር አበጋዞችን ከሳምንታት በፊት ያዋጋ ነው። የተዋጉት ፣ የአህመድ አዶብና ኢፍቲን ሐሰን ባስቶ ሚሊሺያ ጦረኞች ሲሆኑ ፤ የመቅዲሹው መንግሥት የሁለቱንም ተፋላሚ ወገኖች መሪዎች የጁባላንድ ፕሬዚዳንትነታቸውን አይቀበልላቸውም። ይህ ደግሞ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ፑንትላንድን ያስቆጣ ነጥብ ሆኗል። እንደ ፑንትላንድ አመለካከት የመቅዲሹ አገዛዝ የፑንትላንድን መስተዳድር በበጎ ዓይን የሚመለከተው አልመሰለም። እዚህ ላይ ዓለም አቀፉ ተጽእኖም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ጎረቤት ሀገር ኬንያ፣ የጎሣ ጦር አበጋዝ አህመድ አዶብን በመደገፍ የመቅዲሹን ባለሥልጣናት ማናደዷ አልቀረም። ውዝግቡ ለምን እስከዚህ ተባብሶ እንደቀጠለ ፣ የዓለም አቀፉ የውዝግቦች ተንታኝ ድርጅት ባልደረባ ሴድሪክ ባርንስ---

«ችግሩ የተፈጠረው፣ የሶማልያ መንግሥት በተቋቋመበት ወቅት፣ አንዳንድ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ ሁኔታው በመቀጠሉ ነው። የችኮላው እርምጃ ውጤት አሁን ዋጋ የሚያስከፍል መስሏል። ማዕከላዊው መንግሥትና የሶማልያ ከፊል ሪፓብሊኮች ለአነዚህ ችግሮች መፍትኄውን መፈለግ ይኖርባቸዋል። »

ፑንትላንድ ሐሰን ሼክ ሙሐመድ ን የበላይ መሪ አድርጎ ለመቀበል ዝግጁ ብትሆንም፣ ሰፋ ያለውን የራሷን የፖለቲካ ድርሻ ማጣት አትፈልግም። ይሁን እንጂ ፣ የመቅዲሹ መንግሥት የጁባላንድን ኅልውና አለመቀበሉ የፑንትላንድን ከፊል ነጻ መስተዳድርንም አጠያያቂ አድርጎ እንደሚመለከት ምልክት ሰጪ ነው በማለት የጋሮዌ ባለሥልጣናት ተናደዋል።

ፌደራላዊ መዋቅር ያለው የሶማልያ መንግሥት እንዲቋቋም ህገ-መንግሥቱ ቢያስገነዝብም፣ የመቅዲሹ ባለሥልጣናት ጥብቅ ማዕከላዊ አገዛዝ ይኖር ዘንድ ይህን ተቃራኒ መንገድ መከተሉን የመረጡ መስለዋል። አሁንም ሴድሪክ ባርንስ---

«እጅግ መጥፎው ነገር የኪሳማዩና የጁባላንድ ውዝግብ ፣አሁን በተጨማሪ የጎሳ የበላይነት ማሳያ ነጥብ ሆኖ መቅረቡና ጉልህ ስሜታዊነትም መንጸባረቁ ነው። ይህን ውጥረት ለማርገብ በጣም ከባድ ነው የሚሆነው። »

Bildergalerie Somalia Sicherheitslage Shebab
ምስል Mohamed Abdiwahab/AFP/Getty Images

የጎሣ ማንነት ጥያቄ በሶማልያ እስካሁን ወሳኝነት ያለው ብርቱ ጉዳይ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። በጁባላንድ፣ የንዑሱ ዳሮድ ጎሣ አባል አዶብ ይበልጥ ተጠናክረው ተገኝተዋል። በፑንትላንድ አብዝሃው ኑዋሪ የዳሮድ ጎሳ አባል ነው። እንግዲህ እንዳመቺነቱ፤ በጁባላንድ የተሣካለት ፌደራሉ ግዛት በንዑሱ የዳሮድ ጎሣ ቁጥጥር ሥር ይውላል ማለት ነው። ይህ ከሆነ የተጠቀሰው ጎሣ በአገሪቱ በመላ ከሌሎች በላቀ ሁኔታ የበላይነቱን ለመያዝ አመቺ ሁኔታዎች ሊፈጠሩለት ይችላሉ። የመቅዲሹው ማዕከላዊ መንግሥት ከሁሉም ጎሣዎች የተውጣጡ አባላት ቢኖሩትም፣ በአመዛኙ የሐዊዬ አባላት ቁጥር በዛ ያለ ነው። ለዚህም ነው የኪሳማዮውን መስተዳድር ሲቋቋም ማየት የማይሻውና አምርሮም የሚቃወመው።

በአሁኑ ጊዜ አንድ የተረጋገጠ ጉዳይ ቢኖር፤ የጁባላንድ ውዝግብ በሶማልያ በናፍቆት ሲጠበቅ የኖረውንና ከሞላ ጎደል ሰላም የታየበትን የአስካሁኑን ሂደት የሚያናጋ መሆኑ ነው። ይህን ደግሞ የፑንትላንድ መስተዳድር አባላት ጠንቅቀው ያውቁታል።

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ