1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማልያና ጊዜያዊ ሁኔታዋ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 27 2002

እ ጎ አ ከጥር ወር 1991 ዓ ም አንስቶ ፣ በሥርዓት አልበኛነትና በሥልጣን ተፎካካሪዎች የምትታመሰው ሶማልያ፤ ገና መፍትኄ አላገኘችም።

https://p.dw.com/p/P2wr
ምስል AP

አብዛኛውን ደቡባዊውንና ማዕከላዊውን ሶማልያ የተቆጣጠረው አክራሪው ታጣቂ ኃይል፤ ኧል ሸባብ ፣ ከሌላው አጋሩ ሂዝቡል እስላም ከተሰኘው ጋር ሆኖ፤ ባለፉት 10 ቀናት ገደማ መቅዲሹ ውስጥ ባካሄደው የማጥቃት ዘመቻ፤ ከ 150 በላይ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል። ተክሌ የኋላ፤

የ«አሚሶን»ን ቃል አቀባይ ሻለቃ ባሪግዬ ባ ሆኩንና የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑትን EJ Hogendoorn ን በማነጋገር የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

ሰላም ለማስከበር ወደ ሶማልያ የተላከው የዩጋንዳ ጦር፣ ሰሞኑን መቅዲሹ ውስጥ ከባድ ሁኔታ አጋጥሞት መሰንበቱ የታወቀ ነው። የዛሬው ውሎውስ ምን ይመስላል? ወደ መቅዲሹ ስልክ በመደወል ያነጋገርናቸው፤ በሶማልያ የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል(AMISON) ቃል አቀባይ፣ ዩጋንዳዊው፤ ሻለቃ ባሪግዬ ባ ሆኩ--

«እርግጥ ነው የኃይል እርምጃም ሆነ ሁከት የጨመረ መስሎ ታይቷል። ይሁን እንጂ ይህን ያህል የሚያሠጋ የሚያሥፈራ አይደለም። በዚህ አገር የሚሆነውን፤ የሚደርሰውን---ለሚያውቁት ማለት ነው! ይህ ደግሞ ሊያጋጥም ይችላል ብለን የምንጠብቀው ነበረ። እንዲሁ ከሰማይ ዱብ ያለ ነገር አይደለም። ምንጊዜም የምንቀሳቀሰው፣ የመንግሥት ወታደሮችንና የአሚሶን ን ወታደራዊ ይዞታ አጠናክረን ነው።»

የመቅዲሹ ኑዋሪዎች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

«አለመታደል ሆኖ፤ ይህን በመሰለው ሁኔታ በአመዛኙ ለሥቃይ የምናደረገው እኛና ህዝቡ ነው። መዘንጋት የሌለበት ይህች ሀገር፤ መሠረታዊ ልማቱ፤ ኤኮኖሚዋ የወደመ መሆኑ ነው። ህዝቡ ከአጅ ወደ አፍ በሆነ የአህል እርዳታ ነው የምንከላወሰው። የሰብአዊ ይዞታው ከባድ ነው። ብርድ ልብስ፤ ምግብ፤ ውሃና መድኃኒት የላቸውም።»

ሶማልያ ሰላም ካጣች 20 ዓመት ሊደፍን የቀሩት 4 ወራት ገደማ ብቻ ናቸው። ባለፉት 10 ቀናት ገደማ የመዲናይቱ ኑዋሪዎች ፣ ኧል ሸባብ፤ በከፈተው የማጥቃት እርምጃና ከአፍሪቃው ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በተወሰደው አፀፋ ኢታመሱ ነው የሰነበቱት። ለዘለቄታው አገሪቱ ምን ቢደረግ ነው የሚበጃት?የዓለም አቀፍ ችግሮች ውዝግቦች አጥኚ ቡድን (ICG)የአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ ተመልካች EJ Hogendoorn---

«እንደምናምነው፣ ዞሮ-ዞሮ፣ የሚፈለገው፣ ለሶማልያ ዘላቂ መፍትኄ ማስገኘት ሲሆን፣ ይህ ደግሞ፣ ከአክራሪው እስላማዊ ድርጅት ጋር በመወያየት ነው ሊከናወን የሚችለው። ዓለም -አቀፉን ማኅበረሰብ ለማግባባት ስንሞክር የነበረው፤ ፌደራዊውን የሽግግር መንግሥት በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ኃይሎች ጋር ይመክር ዘንድ ይበልጥ እንዲያግባቡት ፤ ግፊት እንዲያደርጉበት ነው። ይህንም ሲያደርግ ነው ሥልጣኑን ሰፋ ማድረግ የሚቻለው።»

በአፍሪቃ ኅብረት ፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ና በአውሮፓው ኅብረት የሚደገፈው የሶማልያ ይሽግግር መንግሥት ፤ አሁን በሚታየው ሂደት የሽንፈት ፅዋ ይቀምስ ይሆን?

«ፌደራዊው የሽግግር መንግሥት የሚወገድ (የሚወድቅ) አይመስለኝም። ተጨባጩ ይዞታ እንደሚያሳየው ኧል ሸባብ የአሚሶንን ጦር ኃይል አያሸንፍም። ብዙ ውጊያ ቢካሄድም ፍጥጫው ይቀጥላል እንጂ ሌላ የሚሆን ነገር የለም።»

የኢትዮጵያ ወታደሮች ሶማልያ ግዛት ውስጥ ስለመታየታቸው ተባራሪ ወሬ ይሰማል። የመግባታቸው ጉዳይ እውነት ከሆነ፣ ይበጃል ወይስ ጉዳት ይኖረዋል?

«እስከምናውቀው ድረስ፣ ኢትዮጵያ ከሶማልያ ጋር ወደሚያዋስናት ድንበር ጥቂት ወታደሮች ስለመላኳ ተዓማኒነት ያለው ዘገባ ቀርቧል። ባለፈው ጊዜም ተመሳሳይ ድርጊት ፈጽመዋል። እዚህ ላይ ፤ ኢትዮጵያ በውጊያው ጣልቃ ብትገባ ጥሩ አይሆንም። በሚገባ የሚጠቅመውም ኧል ሸባብን ነው የሚሆነው። ምክንያቱም፤ በአጠቃላይ ፤ አብዛኞቹ ሶማሌዎች፤ በጣም ነው ፣ የኢትዮጵያን ሶማልያ መግባት የሚቃወሙት።»

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ