1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማልያ እና ጊዚያዊ ሁኔታዋ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 20 2001

በሶማልያ የሚታየው ውዝግብና ገሀዱ ሁኔታ ካለፉት በርካታ ወራት ወዲህ በተጠናከረው የባህር ላይ ውንብድና ሰበብ ብዙም ሲነሳ ባይሰማም፡ የአክራሪዎች ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ ነው። የህዝብዋም ችግር እንዲሁ።

https://p.dw.com/p/HfmF
ምስል AP Photo/Mohamed Sheikh Nor

ሀገሪቱን ለማረጋጋት ተቀናቃኞቹ ወገኖች ሁሉ የሚሳተፉበት መንግስት ምስረታ አስፈላጊ ነው፣ ይህንን የተገነዘቡት የሶማልያ የሽግግር መንግስት ፕሬዚደንት ሼክ ሻሪፍ ሼክ አህመድ ይቻላቸው ዘንድ ከተቀናቃኞቻቸው ጋር አብረው ለመስራት በወቅቱ ጥረታቸውን አጠናክረዋል።

የሶማልያ መዲና ሞቃዲሾ አሁንም ከጥቃት ነጻ አልሆነችም። በአውሮጳውያኑ ዓመት 2009 መጀመሪያ ላይ መንበሩን ከባይዶዋ ወደ ሞቃዲሾ ባዛወረው የሶማልያ የሽግግር መንግስት ምክር ቤት ላይ ከጥቂት ቀናት በፊት በተጣለ የሞርታር ጥቃት ባካባቢው ይኖሩ የነበሩ ስምንት ሲቭሎች መገደላቸውን ያይን ምስክሮች ገልጸዋል።

መንበሩን አስመራ ያደረገውና የጅቡቲን የሰላም ስምምነት ያልተቀበለው በሼክ ሀሰን ዳሂር አዌስ የሚመራው ህብረት ለሶማልያ ዳግም ነጻነት እና ብዙውን የሶማልያ ከፊል የተቆጠጠረው አል ሸባብን የመሳሰሉ አክራሪ ቡድኖች ከሽግግሩ መንግስት ጋር ተባብረው እንዲሰሩ የማግባባቱ ተግባር፡ ምንም እንኳን ሼክ አዌስ ሀሳቡን እንደማይቀበሉ በተደጋጋሚ ቢናገሩም፡ አዲሱ የሶማልያ ፕሬዚደንት ሼክ ሻሪፍ ሼክ አህመድ በወቅቱ ትልቅ ትኩረት የሰጡት ጉዳይ መሆኑን በሽግግሩ መንግስት ምስረት ላይ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱት የቀድሞው የኬንያ መንግስት ባለስልጣንና አሁን ለአፍሪቃ ው’ዝግቦች መፍትሄ በሚያፈላልግ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የሚሰሩት አምባሳደር ቤቱዌል ኪፕላጋት ገልጸዋል።

« በሶማልያ የተለያዩትን ቡድኖች የሚያቅፍ መንግስት ለመመስረት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አውቃለሁ። የሽግግሩ መንግስት ፕሬዚደንት ሼክ ሻሪፍ ሼክ አህመድ በዚሁ ጥረታቸው ላይ አብረዋቸው የሚሰሩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ሰይመዋል። እነዚህ ባለስልጣናት አሁን ለስልጠና እዚህ ናይሮቢ ይገኛሉ። »

የሶማልያ ፕሬዚደንት ሼክ ሻሪፍ ሼክ አህመድ ለጀመሩት ለዚሁ ጥረታቸው ዓለም አቀፍ ርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጹት አምባሳደር ኪፕላጋት በሶማልያ የጸጥታና የመልሶ ግንባት ጉዳይ ላይ ባለፈው ሳምንት በብራስልስ ቤልጅየም የመከረው ዓለም አቀፉ የለጋሽ ሀገሮች ጉባዔ ለዚችው ሀገር ሁለት መቶ ሚልዮን ዩሮ ለመስጠት መስማማቱን እንደ ጥሩ ምልክት አይተውታል። ርዳታው በተጨባጭ ምን እንደሚመስል አምባሳደር ክፕላጋት ሲያብራሩ፡

« ባጠቃላይ በሶማልያ ያለውን የጸጥታ አውታር ማጠናከር፡ ማለትም፡ የጸጥታ ጥበቃ መኮንኖጭን እና ፖሊሶችን እየመለመሉ የማሰልጠኑን ተግባር ማሻሻልን ይመለከታል። እንደሚታወቀው፡ መንግስትንና ህዝብን መከላከል ያልተቻለበት ሁኔታ እስካሁን ድረስ ትልቁ የጸጥታው አውታር ድክመት እንደሆነ ይገኛል። »

ይህ በዚህ እንዳለ፡ ዩኤስ አሜሪካ በአሸባሪነት ዝርዝርዋ ውስጥ ያስገባቻቸው ሼክ አዌስ ከጥቂት ቀናት በፊት በስደት ይኖሩባት ከነበረችው አስመራ ወደ ሶማልያ የተመለሱበት ድርጊት የሽግግሩ መንግስት ሀገሪቱን ለማረጋጋት በጀመረው ጥረቱ ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል አምባሳደር ኪፕላጋት ቢገልጹም፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አጋጣሚውን በመጠቀም ሁለቱን ተቀናቃኝ ወገኖች ለማስማማት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ገምተዋል።

« እርግጥ፡ ሼክ ሀሰን ዳሄር አዌስ አንድንድ ርምጃ ከወሰዱ፡ ወደ ሀገር መመለሳቸው ችግር ሊፈጥር ይችል ይሆናል። ግን፡ አክራሪዎቹ ቡድኖች ከሽግግሩ መንግስት ጋር እንዲሰሩና በሶማልያም መረጋጋት እንዲያስገኙ የጎሳ መሪዎች፡ የሀገሪቱ መንግስትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፡ ሁሉም፡ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ እርግጠኛ ነኝ። ከዚያ በኋላ ምርጫ ሊያካሂዱና ያሸነፈው ወገን ስልጣኑንን ሊይዝ ይችላል። የሀገሪቱ ስልጣን ግን በኃይሉ ርምጃ መያዝ አይኖርበትም። »

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በወቅቱ ካለፉት በርካታ ወራት ወዲህ በሶማልያ የባህር ጠረፍ የተጠናከረውን የባህር ላይ ውንብድናን በመታገሉ ተግባር ላይ ቢያተኩርም፡ የችግሩ መፍትሄ ያለው የባህር ላይ ውንብድናን በመታገሉ ላይ ሳይሆን፡ ካለፉት አስራ ስምንት ዓመታት ወዲህ ማዕከላዩ መንግስት ተጓድሎዋት የምትገኘዋን ሶማልያን በማረጋጋቱ ሂደት ላይ መሆኑን በመገንዘብ፡ ምዕራቡ ዓለም ለዚሁ ችግር መፍትሄ በማስገኘቱ ረገድ የአፍሪቃ ህብረትና የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት፡ በምህጻሩ ኢጋድን ከመሳሰሉ ድርጅቶች ጋር አብሮ ተባብሮ የሚሰራበትን ሁኔታ ለማጠናከርና የተሻለ ውጤት ለማስገኘት አቀዶዋል። ይህም፣ በአምባሳደር ኪፕላጋት አመለካከት፣ ሊበረታታ የሚገባ ዕቅድ ነው።

AA/RTR

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ