1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶሪያና እየተባባሰ የመጣው አመጽ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 17 2003

ሶሪያ እንደመሰነበቻዋ ስትናጥ ስትናወጥ ዋለች። ባሽር አላሳድ ዛሬም ጣታቸውን ውደ ውጭ ኃይሎች ቀስረዋል። ደቡባዊቷ የዳራ ከተማ ዛሬ ታንክ ዘምቶባታል። ቀውሱ ከተጀመረ ወዲህ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር 352 ደርሷል።

https://p.dw.com/p/RK8a
ምስል picture alliance/dpa

የእስልምናው ግዛት ማዕከል የነበረች ከሮማውያን እስከ ሞንጎላውያን፤ ከመስቀል ጦረኞች እስከ ቱርኮች ስትወረር ስትታገል ዘመን ዕድሜዋን ለክፍለዘመናት ያስቆጠረች ምድር። የሃይማኖትና ብሄረሰብ ብዝሃነት ጎልቶ ሚታይባት የኩርዶች መኖሪያ፤ የአርመኖች ማረፊያ፤የአስሪያን ህዝቦች መጠለያ፤ የክርስቲያኖች፤ የድሩዜዎች ማደሪያ፤ የአላዊቴ ሺአቶች መናሃሪያ፤ የሱኒዎች ምድር- ሶሪያ። ከፈረንሳይ ነጻ ከወጣች ከ1946 እ.ኤ.አ ጀምሮ የመካከለኛው ምስራቅ ትኩሳት የሚንጣት፤ ውስጣዊና ውጪያዊ ቀውሶች የሚያምሳት ሆናለች። ዘንድሮ የጀመራት ትርምስ በእርግጥ የሀገሪቱን ቀጣይ ዕድል ዕጣ ፈንታ ከሚወስንበት ምዕራፍ የተጠጋ መስሏል። ሰላም ጤናይስጥልን? መጋቢት መጀመሪያ ሳምንት አንስቶ ሶሪያን እያናወጣት ያለውንና ተባብሶ የቀጠለውን አመጽ መነሻችን መድረሻችን አድርገን፤ ለአፍታ አብረናችሁ እንቆያለን።

ሶሪያ በእርግጥ በሃይማኖቱም ሆነ በጎሳ አሰፋፈር ዥጉርጉር መልክ አላት ቢባልም የሙስሊም ዕምነት ተከታይ የሆኑት ሺአቶችና ሱኒዎች የበላይነት ይዝው የሚኖሩባት ናት። ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ማክተም በኃላ በ1963 እ.ኤ.አ ስልጣን የያዘው ባዝ ፓርቲ አባትና ልጅ ተከታትለው በመምራት 48 ዓመታት ተቆጠሩ። ሶሪያ በ1967 እ.ኤ.አ ከግብጽ ወግና እስራዔል ላይ ብረት ካነሳችና በተሽናፊነት በእጇ የነበረውን የጎላንን ኮረብታ ካጣች ወዲህ በምዕራቡ ዓለም ጥቁር መዝገብ ላይ በደማቁ ተቀምጣለች። ለእስራዔል የጎን ውጋት በመሆን ሃማስንና የሊባኖሱን ሂዝቦላ በማስታጠቅ በመልዕክተኞች በቀሏን እየተወጣች ተብላ ትከሰሳለች። በቀጠናው የእስራዔል ቀንደኛ ባላንጣ ሆኗ የተሰለፈችው ሶሪያ በሊባሎስ የውስጥ ጉዳይ በእጅ አዙር ጣልቃ እየገባች የፈለገችው ፖለቲካኛን ስታሾም፤ ያልፈለገችውን ስታሽርና ስታስገድል እየተባለችም ትወነጀላለች። በ2005 እ.ኤ.አ ከሊባኖስ ጦራን ካስወጣች በኃላም ተጽእኖ ማሳረፏ አልተቋረጠም። የቀድሞ የሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ራፊቅ ሀሪሪ ከ22 አጃቢዎቻቸውና ተከታዮቻቸው ጋር በቦምብ የጋዩበትን አደጋ አቀነባብራለች የሚለው ክስ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የነበራትን የሻከረ ግንኙነት የባሰ እንዲሆን አድርጎታል። ሶሪያ በመካከለኛው ምስራቅ ያላት ሚና እንደምዕራቦቹ እምነት በጎ ሆኖ ያልታየው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ከአባታቸው ስልጣኑን ወስደው ሶሪያን እየመሩ ያሉት ባሽር አላሳድ አባታቸው የጫኑትንና በመላው ሶሪያ ተግባራዊ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንዳጸኑ ቀጥለዋል። ዘንድሮ በእርግጥ ግማሽ ከፍለዘመን ሊደፍን ሁለት አመት ብቻ የቀረው ባዝ ፓርቲ ከሩጫው የሚገታበት ዘመን ላይ የተጠጋ መስሏል። የባሽር አላሳድ ስልጣንም እንዲሁ። ቱኒዚያ የጀመረው፤ አብዮት የአላሳድን ወንበር መነቅነቅ ከጀመረ አንድ ወር አለፈው። ሶሪያ ከውስጥ በተነሳ የህዝብ ዓመጽ ደም የሚፈስባት፤ ህይወት የሚጠፋባት ባለተራ ሆናለች።

Baschar al Assad bei seiner Rede in Damaskus Bashar Assad
ፕሬዝዳንት በሽር አላሳድምስል AP

የሶሪያው አመጽ የተጀመረው በእርግጥ የበሽር አላሳድ መንግስት እንዲፈርስ ለመጠየቅ ባለመ መልኩ አልነበረም። እንደ ሊቢያዋ ቤንጋዚ፤ የሶሪያዋ ደቡባዊ ከተማ ዳራ መጋቢት ሰባት ተቃውሞ ሲጀምር ከባዝ ፓርቲ ጋር እኩል ዕድሜ የያዘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ፤ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ለመጠየቅ ነበር። በወቅቱ ሰሜን አፍሪካን እያመሰ የነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ መሪዎችን እያፈናቀለ ነበርና በሽር አላሳድም ስጋት ገብአቶቸው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ ወዲያውኑ አስታወቁ። እንደበሽር እንደመንግስታቸው እምነትና ተስፋ ከቃል ያልዘለው፤ ወደ ተግባር ያልተለወጠው ውሳኔአቸው፤ ለተቃውሞ የወጣውን ህዝብ ወደ ቤቱ ይመለስ ነበር። ግን አልሆነም። ሶሪያ በአንጻራዊ ሁኔታ ውስጣዊ መረጋጋት ነበራት። በእርግጥ የአሁኑ መሪ አባት ሃፊዝ አላሳድ በ1982 እ.ኤ.አ ሃማ በተሰኘች ከተማ የሱኒ ሙስሊሞች ያነሱትን ተቃውሞ በሃይል ከደፈጠጡና 20 ሺህ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ አንድ ቀን ሊፈነዳ የሚችል የሱኒዎች አመጽ ይጠበቅ ነበር። ሶሪያ ሱኒዎች የሚበዙባት ብትሆንም መሪዎቿ ከሺአቶች ወገን ናቸው። በሽር አላሳድ የሚመሩት ህዝብ እሳቸውን እንደጠላት የሚመለከት በመሆኑ በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ ማድረግ የነበረባቸው በሶሪያውያን መሃል ክፍፍልን መፍጠር ነው። ቁጥጥሩ ከፍተኛ የሆነ፤ እስከታች ድረስ ሰንሰለቱ የጠበቀ የደህንነት መዋቅር ዘርግተው ህዝቡ ወለም ዘለም ሳይል ቀጥለጥ ብሎ እንዲገዛላቸው ማድረግን ነበር የመረጡት። ለዚህም አባታቸው የጣሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠበቅ ብሎ እንዲቀጥል አድርገዋል። በአባታቸው ያኮረፉት በእሳቸው ዘመንም እንደተከፉ የዘለቁት ሱኒዎች በእርግጥ ዘንድሮን ሊያልፉቸው አልፈቀዱም። የሰሜን አፍሪካው አብዮት የሰጣቸውን ወኔ ሰንቀው ተነሱባቸው።

ያለፈውን አንድ ወር ሶሪያ በአመጽ ሰነበተች። ደቡባዊቷ ከተማ ዳራ የፈነዳው አመጽ ሌሎቹንም ከተሞች አዳርሶ ከመዲናዎ ደማስቆ ዘልቋል። ተቃውሞው በመንግስት የለውጥ ጥያቄ ባይጀመርም ውሎ አድሮ ግን በሽር አላሳድ ስልጣናቸውን እንዲለቁ የሚጠይቅ ወደ መሆን ተቀይሯል። መንግስት ማሻሻያዎች እንደሚያደርግ ቃል መግባቱ፤ በተወሰነ ደረጃም እርምጃ መውሰዱ ተቃውሞውን ሊያበርደው አልቻለም። ባለፈው ሳምንት ላይ አመጹ የበረታባቸው በሽር አላሳድ ዋናው የህዝቡ ጥያቄ ነበር ያሉትን የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሻሩን አስታወቁ። ተቃዋሚዎች ግን የረኩ አልሆኑም። አመጹ ተፋፍሞ ቀጠለ። መንግስት አደባባይ በሚወጡ ሰልፈኞች ላይ የሚወስደው እርምጃም እየከፋ መጣ። ሶሪያ የለየለት ቀውስ ውስጥ ገባች።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከ120 በላይ ሆኗል። ባለፈው አርብ ዕለት ብቻ 70 ሰዎች ትገድለዋል። ዛሬ ጠዋት የሶሪያ ጦር በታንክ እየታገዘ፤ ዳራ የተሰኘችውን የአመጹ እምርት የሆነችዋን ከተማ ሲወር ሃያ ሰዎች መገደላቸው ተዘቧል። ርዕሰ ከተማዋ ደማስቆ በሚገኝ አንድ መንደርም ጦሩ ከበባ አድርጓል። ሶሪያ ወደ ከፋ የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳትገባ ፍራቻው ከፍ ብሎ በሚሰማበት በአሁኑ ጊዜ ተቃዋሚዎች ጥያቄአችው የባሽር አላሳድ ከስልጣን መውረድ እንደሆነ ያ ካልሆነ አመጻቸ።ውን እንደማያቆሙ ይናገራሉ። የሶሪያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አናስ አል አብደላ የህዝቡ ጥያቄዎች አምስት ናቸው ይላሉ።

«ህዝቡ እየጠየቀ የነበረው ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረገው ግድያ በአስቸኳይ እንዲቆም ነው። ከዚያ በኋላ አምስት ጉዳዮች እንዲፈጸሙ ይፈልጋል። አንደኛው አስቸኳይ አዋጁ አንዲነሳ ነው። ትላንት ይህ ተፈጽሟል። ሁለተኛው ጥያቄ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ነው። ሶስተኛ ተሰደው ያሉ የሶሪያ ፖለቲከኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አራተኛ አዲስ ፓርቲ እንዲመሰረትና አዲስ ህገመንግስት እንዲቀረጽ፤ በመጨረሻም አምስተኛና ዋናው ፕሬዝዳንታዊና የምክር ቤት ምርጫ የሚደረግበት ቀን ተቆርጦ እንዲገለጽለት ነው።»

በእርግጥ የሶሪያን ህዝብ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ተጭኖት የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በይፋ ተሽሯል። ፕሬዝዳንት በሽር አላሳድ ከአዋጁ መሻር በኋላ እፎይታን እንደሚያገኙ ያመኑበት ውሳኔአቸው ሀገሪቱን የሚረጋጋ ሲሉ ነበር የገለጹት።

«አንዳንዶች የአስቸኳይ ጊዜው አዋጅ መሻር ደህነታችንን አደጋ ላይ ይጥለዋል ብለው ይሰጋሉ። የእኔ እምነት ግን ተቃራኒው ነው። ጸጥታችን የተረጋጋ የህዝቡም ሰብዓዊ ክብርም ዋስትና ያለው ይሆናል።»

በሽር አላሳድ እንዳሉት ግን አልሆነም። አዋጁ ከተሻረ ወዲህ የአመጹ አድማስ መስፋት፤ የሚገደለው ሰው ቁጥርም መጨመር እንጂ እንደ አላሳድ ተስፋ የተሻለ ሰላም ሶሪያ አላገኘችም። የአዋጁን በይፋ መሻር ተከትሎ በአዋጁ ታገዶ የሰነበተውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን ለመጠቀም አደባባይ የወጣው ህዝብ የጠበቀው በእርግጥ እስርና ግድያ ነው።

Syrien Banias Proteste
ምስል AP

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የመነሳት ውሳኔ ተግባራዊ መሆን አለመሆኑን ለመፈተን የሚመስለው የረቡ ዕለቱ ሰልፍ መጨረሻው በአሰቃቂ ሁኔታ ተቋጭቷል። በእርግጥም የ48 ዓመቱ አዋጅ በተነሳ በ24 ሰዓት ውስጥ የተፈጸመው ግድያ ሶሪያውያንን የበለጠ አስቆጥቷል።

የሶሪያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ሪም ሃዳድ ሰልፈኛው ሰላማዊ ተቃውሞ ማድረግ ነበረበት። ፍቃድም ሊኖር ይገባል ይላሉ።

«ህዝቡ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቃውሞውን ቢገልጽ፤ ምንም ዓይነት ጥፋት በንብረት ላይ ባይፈጽም ኖሮ ሰልፉን ማድረግና ተቃውሞን ማሰማት ይችል ነበር። አስፈላጊ ቢሆን እንኳን እንዲበተን ነበር የሚደረገው። ግን ያን አላደረገም። ወደ ቤቱ እንዲገባ ከማድረግ ያለፈ እርምጃ አይወሰድም ነበር። በዚህ ላይ ትላንት በተደረገው ውሳኔ መሰረት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ፍቃድ መጠየቅ ነበረበት።»

ያለፈው ማክሰኞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በይፋ ከተሻረ በኋላ በተከታታይ በተደረጉት ተቃውሞች ላይ በጸጥታ ሃይሎች የተገደሉትን ለመቅበር የወጣው ህዝብ የቀብሩን ስነስርዓት ወደተቃውሞ ሰልፍ ለውጦታል። በተለይ ያለፈው አርብና ቅዳሜ በርዕሰ ከተማዋ ደማስቆ የቀብር ስነስርዓቱ ላይ በቁጣ የተቀጣጠለው ቀባሪ ከጸጥታ ሃይሎች ፊት ለፊት ነበር የገጠመው። አርብና ቅዳሜ በእርግጥ ደማስቆ የጦር አውድማ ትመስል ነበር።

120 ሰዎች በሁለቱ ቀናት ብጥብጥ መገደላቸው ተረጋገጠ። ሌላ ቁጣ ሌላ አመጽ። ዋናዋ የተቃውሞ ዕምብርት ዳራን ጨምሮ ትልልቆቹ የሶሪያ ከተሞች በተቆጡ ሶሪያውያን ተጥለቀለቁ።

የአይን እማኞች እንደገለጹት የጸጥታ ሃይሎች ይተኩሱ የነበሩት በቀጥታ ወድ ህዝቡ ነበር።

«በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰልፈኞች እዝራ በተሰኘችው ከተማ አደባባይ ወጥተው ነበር። ቁልፍ የሆነችው የሩዶም ግሃዚ ማዘዣ ነጥብ ጋር ሲደርሱ ታጣቂዎች መተኮስ ጀመሩ። ያለምንም ማስጠንቀቂያ ነበር ተኩሱን የከፈቱት።»

በእርግጥ የበሽር አስተዳደር ህዝባዊ ተቃውሞ ከገጠማቸው ጊዜ አንስተው ጣታቸውን የሚቀስሩት በውጪ ሃይሎች በተለይም በአሜሪካንና በእስራዔል ላይ ነው። ተቃዋሚዎችን ያስታጠቁ፤ ከጀርባቸው ሆነው ሶሪያን የሚበጠብጡ እንደሆኑ ከመክሰስ ወደ ኋላ ብለው አያውቁም።

«ሚስጢር የለም ። ግልጽ ነው። ሶሪያ በውጭ ሃይሎች የተጠነሰሰ ሴራ ሰለባ ናት። በአከባቢያችን ይህ መሰሉ ችግር የነበረ ነው። የውጭ ሃይሎች የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ነው የሶሪያ ችግር»

ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን በተመለከተም የበሽር አስተዳደር የውጭ ሃይሎች ፕሮፖጋንዳ ሲል ያጣጥለዋል። ሰሞኑን ደም ያፋሰሰው ግጭት ከተከሰተ በኋላ የበሽር አላሳድ መንግስት ቃል አቀባያው አህመድ አል ሀጂ ክሱ ሁሉ ውሸት ነው። እውነቱ በቅርቡ ይታወቃል ይላሉ።

« ሁሉም ሰው መንግስት ሰልፈኛው ላይ ተኩሷል። ገድሏልም ብሎ ሊያስብ ይችላል። የውጪ ሃይሎችም መንግስት ህዝቡን እይገደለ ነው ይላሉ። ግን ይህ ሁሉ ውሽት ነው። ምክንያቱም ማስረጃዎች አሉ። ከሆነም ያደረጉት ሰዎች ለፍርድ ይቀርባሉ። ይህ የሚባለው ሁሉ የሚደረገው ሴራ በሙሉ በውጭ ሃይሎች ገንዘብና የጦር መሳሪያ የሚከናወን ነው። ተክክለኛው ሀቅ ግን በቅርቡ ይወጣል።»

በርካቶች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ የበሽር አስተዳደር ሰላማዊ ሰልፍን ይፈቅዳል፤ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችንም በተወሰነ ደረጃ እውቅና ሰጥቶ ያከብራል የሚል ተስፋ ነበራቸው። የመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ተንታኝ ኦስማን ሙጃጄድ እንደሚሉት ግን ቀድሞውኑ አዋጁ ዘግይቶ ነው የተነሳው። ኦስማን ማሻሻያ እርምጃው ብጥብጥን መጠበቅ አልነበረበትም ሲሉም ይተቻሉ።

«ሰዎች በሽር አላሳድ ተራማጅ ናቸው። ለውጥ አድራጊ ናቸው ብለው ሊያስቡ ይችላሉ። ሌላው ቀርቶ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የበሽር አስተዳደር ማሻሻያ ማድረግ ይችላል ብለሎ ተስፋ አድርጓል። ይሁንና የበሽር ማሻሻያ የመጣው ከጥይት ወይም መሳሪያ በኋላ ነው»

ብዙዎች የአረቡ አለም የፖለቲካ ተንታኞች እንዳሰቀመጡት የበሽር አላሳድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማንሳት ውሳኔ ሁለት አላማዎች ነበሩት። አንደኛው ለህዝብ ጥያቄ መልስ የሚሰጥ መንግስት ሆኖ መታየት ሲሆን ሌላኛውና ዋናው ግን ተቃውሞ የሚያስነሳ ምንም ዓይነት ምክንያት በሶሪያ ምድር እንደማይኖር ማረጋገጥ ነበር። ሁለቱም አላማዎች በእርግጥ ኢላማቸውን አላገኙም። የበሽር አተስተዳደር ለህዝብ ጥያቄ መለስ ሰጥቷል የሚል እምነት ህዝቡ ዘንድ የለም። ሶሪያም ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት በኋላ ለተቃውሞ ምክንያት የማይኖርባት ሳይሆን የሚበረክትባት ሆና አርፋለች። አርብ ቅዳሜ ና ዛሬ የተፈጸመው ግድያ አለም አቀፉንን ማህበረሰብ አስቆጥቷል። የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በበሽር አላሳድ አስተዳደር ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጥያቄ አቅርቧል። አሜሪካ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ስለሚጣልበት ሁኔታ እያሰበችበት መሆኗን እስታውቃለች። ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የሰሞኑን የሶሪያ እርምጃ በጥብቅ እንዳወገዙት ኋይት ሀውስ አስታውቋል።

ሶሪያ አሜሪካና እስራዔል ላይ ጣትዋን ቀስራለች። በእርግጥ የሶሪያ የበሽር አላሳድ መዳከም ለእስራዔል ራስ ምታት የሆኑትን ሂዝቦላንና ሃማስን ያጠፋቸዋል የሚል ስሌት አሁን አሁን ከፍ ብሎ ይሰማል። እነ አሜሪካ ኢራንን ለማዳከም በቅድሚያ ሶሪያን መሰባበር አለብን ብለው የቀየሱት ስልትም ሳይሆን አይቀርም የሚል ትንተናም እየተሰጠ ነው። ሶሪያ ወደለየለት ብጥብጥ እንዳትገባ ስጋቱ ተጠናክሮ በሚሰማበት በአሁኑ ሰዓት የበሽር አስተዳደር ለማንኛውም ጸረ መንግስት እንቅስቃሴ ትዕግስት የሌለው መሆኑን ዛሬ መውሰድ በጀመረው እርምጃ ግልጽ አድርጓል።

አድማጮች የሶሪያን ወቅታዊ ሁኔታ የቃኘንበት የዛሬው ማህደረ ዜና በዚሁ ተጠናቋል። መሳይ መኮንን ነበርኩ። ጤና ይስጥልን።