1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶሪያ ሠላም የተነፈገች ምድር

ሰኞ፣ ጥቅምት 22 2008

በቪየናዉ ሥብሰባ የልዕለ ሐያላኑን መንግሥታት ጨምሮ የአስራ-ሰባት ሐገራት ሚንስትሮች፤ የሁለት ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።ወይይቱ ለስምምነት ባይበቃም ተወያዮች ከስምምነት እስኪደረሱ ዉይይቱን እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

https://p.dw.com/p/1GyTy
ምስል Getty Images/AFP/J. Klamar

ሶሪያ ሠላም የተነፈገች ምድር

የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ፤ የኋላዉ የሶሪያ ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ ኮፊ አናን ድፍን ዓለም የሚያዉቀዉን አዉቀዉ፤ የሚለዉን እንደ ዲፕሎማሲዉ ወግ ደግመዉ የልዩ መልዕክተኝነቱን ሥልጣን ለመልቀቅ ስድስት ወር ፈጅቶባቸዉ ነበር።አናንን የተኩት ላሕዳር ብራሒሚ ዓለም የሚያዉቅ፤ የሚለዉን፤ የቀድሞ አለቃቸዉ፤የደገሙትን አሰልሰዉ፤ ያደረጉትን ለመድገም ዓመት ከመንፈቅ ደክመዋል። ብራሒሚን የተኩት ስቴፋን ዶሞኒግ ደ ሚስትራ የሚሉትን ለማወቅ እስኪሉት መጠበቅ አለብን።ጦርነቱን ከዉጪ የሚያጋግሙት ግን ጠባቸዉ ሲከር፤ድንበራቸዉ በስደተኛ ሲበረገድ ዓለም የሚያዉቀዉን-ለማወቅ፤ ዲፕሎማቶቹ የደገሙ፤ያሰለሱትን ለመቀበል የፈቀዱ መስለዋል።የዋሽግተን-ሞስኮ፤ የቤጂንግ-ብራስልስ ሐያላን፤ እነሆ መልካም ፍቃዳቸዉ ሆኖ የቴሕራን-ሪያድ ታማኞቻቸዉን አስከትለዉ ዉይይት ጀምረዋል። ዉጤቱ ያዉ በነሱዉ ፍቃድ የሚበየን ነዉ።ግን ስንቱ አለቀ? ስትስ ማለቅ ይኖርበት ይሆን?

አርብ፤ ቪየና-የሳዑዲ አረቢያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አድል አል ጀባርን በስብሰባዉ ላይ ከሚሉ፤ከሚሰሙት እኩል በጣም ያሳሰባቸዉ የሚቀመጡበት ሥፍራ ነበር።በቅርብ የሚያዉቋቸዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞች በዲፕሎማሲ ዕዉቀት፤ ችሎታቸዉ ብዙ የሚያደንቁ፤የሚያወድሷቸዉ የሐብታሚቱ ሐገር ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በርግጥ አይናፋር አይዳሉም።በዚያ ሥብሰባ ላይ ግን የኢራን አቻቸዉን አይን ማየት አልፈለጉም።

አል-ጀባር ከትልቁ፤ ዉብ፤የደልቃቆች ሆቴል ምቹ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፤ ከኢራኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር መሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ ርቀዉ የሚቀመጡበትን ሥፍራ-ሲያማትሩ ሰሜናዊ-ምዕራብ ሶሪያ ኢዲሊብ ከየዕለት ምሷ-የመጀመሪያዉ ወረደባት።የአዉሮፕላን ቦምብ።

Österreich vor Syrien-Konferenz in Wien Lawrow und Kerry
ምስል picture-alliance/dpa/A. Shcherbak

ርዕሠ-ከተማ ደማስቆ አጠገብ የሚገኙ መንደሮች ለዚያን ቀን ሚሳዬል ነዉ-የተዘዛባቸዉ።ማርፈጃዉ ላይ መንደሮቹን ያንቀረቀበዉ ሚሳዬል አርባ ገደለ።ብዙ አቆሰለ።ደማስቆን ከሆምስ ጋር በሚያገናኛዉ ሥልታዊ አዉራ መንገድ ላይ በምትገኘዉ ማሒም በተባለች ከተማና አካባቢዋ በተደረገ ዉጊያ ደግሞ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS በምሕፃሩ) ብሎ የሚጠራዉ ቡድን የመንግሥት ጦርን አሽንፎ-ሥልታዊዉን አዉራ ጎዳና ተቆጣጥሮታል።

ከማለዳዉ እስከ ቀትር በቆየዉ ዉጊያ የሞተ፤ የቆሰለዉ ሰዉ ብዛት በዉል አልታወቀም።ከሶሪያ፤ እስከ ሩሲያ፤ ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ ብሪታንያ፤ ከሳዑዲ አረቢያ እስከ ዮርዳኖስ፤ ከፈረንሳይ እስከ ቱርክ፤ ከቀጠር እስከ ባሕሬን የአስራ-ሰባት መንግሥታት የጦር ጄቶች በሚተራመሱባት ሐገር፤ ከ20 በላይ ደፈጣ ተዋጊዎችና የመንግሥታት ወታደሮች በሚራኮቱበት ምድር፤ አንዱ ሌላዉን መዉቀስ ማዉገዙን እንጂ የአርቡን ቦምብ የጣለዉ ጄትን-የማንነት ሚሳዬሉን ያወነጨፈዉ ወገን የትኛዉነን በዉል ማወቅ አይቻልም። ሕዝብ ግን ያልቃል።ይቆስላል፤ ይሰደዳል።አራት ዓመት ከመንፈቅ።-

ሕዝባዊ አመፅን ተላብሶ በ2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) የተቀጣጠለዉን የሶሪያዉ ጦርነት ለማስቆም፤ እንደማንኛዉም ጦርነት ሁሉ የብልሆቹ፤ የሠላም ወዳዶቹ መንገድ አንድ፤ ግልፅና ድፍን ዓለም የሚያዉቀዉ ነዉ።ተፋላሚዎችን ማስታረቅ።

 

በሐያላን መንግሥታት የሚገፋዉ ዓለም አቀፍ ማሕበር ዓለም የሚያዉቀዉን፤ ሰላም ወዳዶች የሚመኙትን፤ ሕይወት የሚያተርፈዉን ብልሐት ለመሞከር አንድ ዓመት ፈጀበት።ዓለም አቀፉ ድርጅት ለጦርነቱ ሠላማዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ የቀድሞ መሪዉን ኮፊ አናንን የካቲት 2012 በልዩ መልዕክተኝነት ሲሾም፤ ጦርነቱ ከሶሪያዎች አልፎ፤ ባካባቢዉ የበላይነታቸዉን ለማረጋገጥ፤ ጥቅማቸዉን ለማስከበር፤ ቂማቸዉን ለመበቀል፤ የሚሹ ሐይላት ተሞጅረዉበት ነበር።

ያም ሆኖ ትልቁ ዲፕሎማት ሠላማዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ ትላልቁ ዓለም መስማማቱ የተስፋ ጭላንጭል መፈንጠቁ አልቀረም ነበር።ግን ብዙ አልቆየም።በስድስተኛ ወሩ ተጨናጎለ።አናንንም ተስፋ ቆረጡ።ነሐሴ 2012

Russland Syrien Sukhoi Su-34
ምስል picture-alliances/Ministry of Defence of the Russian Federation

«እየተባባሰ የመጣዉ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እና የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አንድ አቋም አለመያዙ ተልዕኮዬን በተገቢዉ መንገድ እንዳልወጣ እንቅፋት ሆኖብኛል።ደም መፋሰሱ ግን እንደቀጠለ ነዉ።በአብዛኛዉ በሶሪያ መንግሥት እንቢተኝነትና ባለ ሥድስድት ነጥቡን ዕቅድ ገቢር ለማድረግ በማቅማማቱ ምክንያት እና የተቃዋሚዎቹ ወታደራዊ ዘመቻ በመጠናከሩ (ጥፋቱ ተባብሷል።) ሁሉም በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ አለመተባበር ምክንያት የመጣ ነዉ።እኛ በምንፈልገዉ ወቀት፤ የሶሪያ ሕዝብ አጣዳፊ መፍትሔ በሚሻበት ጊዜ፤ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉስጥ አንዱ በሌላዉ ላይ ጣቱን መቀሰሩና፤ መወቃቀሱ እንደቀጠለ ነዉ።»

አሉና ሥልጣን ለቀቁ።

አናን የሶሪያ ተፋላሚዎችንና አስታጣቂዎቻቸዉን ለማስታረቅ በሚሞክሩበት ወቅት በጦርነቱ የተገደለዉ ሕዝብ ሠላሳ ሺሕ አልደረሰም ነበር።የቱርክ፤የግሪክ ባሕሮች በስደተኞች አስከሬን አልጎደፉም ነበር።ዛሬ የዓለም አንደኛ አስጊ አሸባሪ ሥለሚባለዉ( ISIS) የሚታወቅ ብዙም አልነበርም።

በአናን ምትክ ሌላዉ ትልቅ ዲፕሎማት ላሕዳር ብራሒሚ ሌላ ሙከራ እንዲያደርጉ የዓለም ሐያል ተቀናቃኝ ሐያላት ሲፈቅዱ፤ በየፊናቸዉ ጊዜ ለመግዛት፤ አንዳቸዉን ሌላቸዉ በዲፕሎማሲዉ መስክ ለማሳጣት ዓልመዉ ወይም የዲፕሎማሲ በር ጨርሶ እንዳይዘጋ ፈልገዉ ወይም በሌላ ምክንያት ሊሆን ይችላል።ለሶሪያ ሠላም ከልብ አስበዉ ነዉ-ብሎ ግምት ግን ለብዙ ታዛቢዎች ምክንያት አልነበረም።

ብራሒሚ ድፍን ዓለም ከ2011 ጀምሮ የሚያዉቀዉን፤ አዉቀዉ እንደ ኮፊ አናን ተልዕኳቸዉን በ«በቃኝ» ለማቆም ከመስከረም 2012 እስከ ግንቦት 2014 መዳከር ነበረባቸዉ።ዓመት ከስምንት ወር።ዉጤት?

«የሟቹ ቁጥር እያሻቀበ ነዉ።የሕዝቡ ስቃይ ከፍተኛ ነዉ።የተከበሩ ፕሬዝደንት፤ የሶሪያ መፃኤ ተስፋ የሚገነባዉ በራሷ ዜጎች እንጂ በሌላ በማንም አይደለም።የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ድጋፍ ግን ምትክ የማይገኝለትና አስቸኳይ ነዉ።ያ ድጋፍ ዉጤማ የሚሆነዉ ግን ሁሉም ወደ አንድ አቅጣጫ ሲጎትት ብቻ ነዉ።»

ብራሒሚም እንደ አናን መጡ፤ ሔዱ።ስቴፋን ዶሞኒግ ደ ሚስትራ ተተኩ።ጦርነቱም ብሶ ቀጠለ።ብራሒሚ ሥልጣን ሲለቁ በጦርነቱ የተገደለዉ ሕዝብ ቁጥር ከ90-እስከ መቶ ሺሕ ተገምቶ ነበር።ጦርነቱን ሽሽት ወደ ኢራቅ፤ ቱርክ፤ዮርዳኖስ እና ሊባኖስ የተሰደደዉ ሕዝብ ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲያስታዉቅ ጉድ አሰኝቶ ነበር።

Syrien Pianist Aeham Ahmad in Damaskus
ምስል Johannes-Wasmuth-Gesellschaft e.V./Niraz Saied

ኮፊ አናን የ«ፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት»፤-ብለዉ በግልፅ የጠቀሱት፤ ብራሒሚ «ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ» በማለት ያድበሰበሱት ተቀናቃኝ ሐያሉ ዓለም ምክር፤ ማስጠንቀቂያዉን ሠምቶ፤ እልቂቱን ለማስወገድ ያኔም እስካሁንም አልፈቀደም።ሶሪያ ዛሬ የአሜሪካ፤የሩሲያ፤ የአዉሮጳ፤ የአረብ የቱርክ የጦር ጄቶች ቦምብ ያዘንቡባታል።በብዙ ስም የሚጠሩ ፤ የብዙ ሐገራት ዜጎችን ያካተቱ ታጣቂዎች ሕዝብ ይፈጁ፤ እርስ በርስ ይፋጁ፤ ሐብት ንብረቷን ያወድሙባታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚገምተዉ እስካለፈዉ ሐምሌ ድረስ ብቻ ከ310 ሺሕ በላይ ሰዉ አልቆባታል።ሁለት መቶ ሐምሳ ሺሕዉ ሠላማዊ ሰዉ ነዉ።የሶሪያ ዜጎች አስከሬን ከቱርክ፤ከግሪክ፤ ከሜድትራኒያን ባሕሮችን ዕለት በዕለት ይለቀማል።የደቡብና የምሥራቅ አዉሮጳ መንገዶች፤የምዕራብና የሰሜን አዉሮጳ መጠለያ ጣቢያዎች በሶሪያ ስደተኞች ተሞልተዋል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዳስታወቀዉ 11 ሚሊዮን ሶሪያዊ አንድም ተፈናቅሏል፤ አለያም ተሰዷል።የሶሪያ ሕዝብ ከጦርነቱ በፊት 22 ሚሊዮን ነበር።

ከሞት አምልጠዉ አዉሮጳ ለመግባት የታደሉ ሶሪያዊ ባለፈዉ አርብ እንዳሉት ዓለም ባሻዉ የመዘወር አቅም ያላቸዉ ሐይላት አሸናፊና ተሸናፊ ለማይገኝበት ጦርነት አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለመብለጥ ሲሉ እልቂት ፍጅቱን ማጋጋማቸዉ በርግጥ አሳዛኝ ነዉ።ያም ሆኖ የተፋላሚ ሐይላት ደጋፊዎች ዘንድሮ በአምስተኛ ዓመታቸዉ ፊት ለፊት ለመነጋገር መወሰናቸዉ ብዙ ታዛቢዎች እንዳሉት ከምንም የሚሻል ነዉ።ባለፈዉ አርብ ቪየና-ኦስትሪያ ላይ በተደረገዉ ስብሰባ ላይ የተካፈሉት የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይማየር እንዳሉት ደግሞ የተፋላሚ ሐይላት ደጋፊዎች የድርድርን አስፈላጊነት አምነዉ መወያያታቸዉ ጥሩ ጅምር ነዉ።

«የሶሪያዉን ጦርነት ለማስወገድ ሁሉም ወገን የየራሱን አስተዋፅኦ ለማበርከት ከፈቀደ እና በድርድሩ ከተሳተፈ ስብሰባዉ ጥሩ ዉጤት ያመጣል።በዛሬዉ (ስብሰባ) ሁሉም ወገን ለፖለቲካዊ መፍትሄ የመጀመሪያዉን እርምጃ ከወሰደ ) እልባት ማግኘት አይገድም።»

Jordanien Zaatari Flüchtlingslager
ምስል Getty Images/AFP/K. Mazraawi

የሳዑዲ አረቢያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አድል አል-ጀባር ከኢራኑ አቻቸዉ ጎን መቀመጡን ቢጠየፉትም በሞስኮ-ዋሽግተኖች ግፊት አንድ ጠረጳ ከበዉ ለመቀመጥ ተገድደዋል፤ ወይም ፈቅደዋል።በቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን ለአርባ ዘመን በኑክሌር ሳይቀር የተፋጠጡት፤ በቅርቡ ደግሞ እንደ ሶሪያዉ ሁሉ በዩክሬ ጦርነት ጦርነት ሰበብ በጠብ የሚፈላለጉት፤ በማዕቀብ የሚቀጣጡት፤ በስለላ የሚሻጠሩት የሩሲያና የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትሮች እንደ ጥሩ ወዳጅ እየተሳሳቁ፤እየተጨባበጡ፤ እየተቀላለዱ በጋራ ሲመክሩ የቴሕራን-ሪያድ ባለሥልጣናት ለመተያየት እንኳን መጠያየፋቸዉ በርግጥ አስቂኝ፤ ግራ-አጋቢ፤ አስተዛዛቢም ነዉ።

በቪየናዉ ሥብሰባ የልዕለ ሐያላኑን መንግሥታት ጨምሮ የአስራ-ሰባት ሐገራት ሚንስትሮች፤ የሁለት ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል።ወይይቱ ለስምምነት ባይበቃም ተወያዮች ከስምምነት እስኪደረሱ ዉይይቱን እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል።

«ልዩነታችን ዲፕሎማሲዉን የሚያደናቅፍና የመጨረሻ መፍትሔ እንዳይገኝ የሚያዉክ መሆን የለበትም።ዛሬ እዚሕ የተደረሰበት ዉሳኔ ጠቃሚ ጎኑም ይሕ ነበር።ልዩነት መኖሩ ባይካድም ቁጭ ብሎ መነጋገር እና አዉነተኛዉን ድርድር ባስቸኳይ መጀመር አስፈላጊ ነዉ።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ።አስራ-ስምንት እንግዶቻቸዉን ያስተናገዱት የኦስትሪያዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዜባስቲያን ኩርትስም ጠንከር ያለ ተስፋ ነዉ ያላቸዉ።

Syrien Idlib Flüchtlingslager
ምስል picture-alliance/dpa/AA/C. Genco

ተስፋዉ መያዝ መዛቱን ለማወቅ ቢያንስ የሚቀጥለዉን ሰብሰባ መጠበቅ ግድ ነዉ።እስከዚያዉ ግን ሶሪያ አምስት ዓመት እንደለመደችዉ ትወድማለች።ሕዝቧ፤-ያልቃል፤ ይሰደዳልም።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ