1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶሪያ፤ የኃያል፤ ቱጃሮች መፋለሚያ ምድር

ሰኞ፣ ጥር 30 2008

የፖለቲካ ተንታኞች ደጋግመዉ እንዳሉት እስካሁን አሸናፊም ተሸናፊም ያተለየበት ጦርነት የሚቆመዉ ሞስኮ እና ዋሽግተን፤ ቴሕራንና ሪያድ፤ ጠባቸዉን ሲያበርዱብቻ ነዉ። እነዚሕ ኃይላት ሠላም እንዲያወርዱ መሻኢኽ፤ ቀሳዉስት አሁንም ይፀልያሉ፤ ይማፀናሉም

https://p.dw.com/p/1Hred
ምስል Getty Images/D. Kitwood

ሶሪያ፤ የኃያል፤ ቱጃሮች መፋለሚያ ምድር

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ-ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ «የኛዋ ተወዳጅዋ» ይሏታል። ሶሪያን። እንደ ጦር፤ ፖለቲካዉ ታሪክ የሮሞች፤ የቱርኮች፤ የአረቦች፤ የአዉሮጳ-አሜሪካኖች ድል-ሽንፈት ታሪክ፤ ከታሪካዊቱ ሐገር ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነዉ። የአይሁድ፤ የክርስትና የእስልምና ሰበካ፤ ስርጭት ክፍፍል ሲወሳ-የዚያች ሐገር እና የዜጎቿን ተሳትፎ አለማንሳት አይቻልም። ካፒታሊስት፤ ከኮሚንስት፤ አረብ-ካይሁድ፤ ፋርስ-ካረብ፤ ምዕራብ ከምሥራቅ፤ ፅንፈኛ-ከለዘብተኛ ሲሻዉ ይከባበርባታል፤ ሲለዉ ይተላለቅባትል። ጳጳሱ እንዳሉት ሁሉም ይወዳታል። ባለፈዉ ሳምንት አስር ቢሊዮን ዶላር አዋጣላት። ደግሞ በተቃራኒዉ ሁሉም ይፋጅ-ያፋጅባታል። የሠላም ተስፋዋን አጨናጎለባት። ላፍታ-ሶሪያ እንበል-አብራችሁኝ ቆዩ።

የቀድሞዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እዉቅ ዲፕሎማትና የፊንላንድ ፕሬዝደንት ማርቲ ኦይቫ ካሌቪ አሕቲሳሪ በ2012 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የተደረገዉን ሙከራ «የጠፋዉ መልካም ዕድል» ይሉታል። ከናሚቢያ እስከ አቼ፣ ኢንዶኔዢያ፤ ከኮሶቮ እስከ ኢራቅ ሠላም ለማስፈን የተደረጉ ጥረቶችን የመሩት ዲፕሎማት የሶሪያ ተፋላሚዎችን ለማደራደር ሞክረዉ ነበር።

ማርቲ አሕቲሳሪ በሶሪያ ሠላም ለማስፋን በጅምር የቀረ ሙከራቸዉን ያደረጉት ከአራት ዓመት በፊት ነበር። የካቲት 2012። አሕትሳሪ ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን ያላቸዉን መንግሥታት ዲፕሎማቶችን ሲያነጋግሩ የሩሲያዉ አምባሳደር ያቀረቡት ሐሳብ - ለአቲሳሪ አይደለም የጦርነትን ጥፋት ለሚያዉቅ ሁሉ አሳማኝ ነበር።

የሩሲያዉ አምባሳደር ቪታሊ ቹርኪን በሰወስት ነጥብ ከከሸኑት ሐሳብ አንዱ፤ የፕሬዝደንት በሽር አል አሰድ መንግሥት ሥልጣን እንዲለቅ የሚጠይቅ ነበር። የአሰድ ተቃዋሚዎች ጊዚያዊ ድል ያሰፈነደቃቸዉ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ግን «የአሰድ ሥርዓት መወገዱ ሥለማይቀር» በሚል ምክንያት ሐሳቡን ዉድቅ አደረጉት። ጦርነቱ የሶሪያዎች ብቻ ወይም የእርስ በርስ እንዳልሆነ በግልፅ ተረጋገጠ። የሚያልቅ፤ የሚሰቃይ፤ የሚሰደደዉ ግን በርግጥ ሶሪያዊ ነዉ።

Syrien Aleppo Zerstörung Bombardierung
ምስል Reuters/A.Ismail

ኖቤል ተሸላሚዉ አሕቲሳሪ ባለፈዉ መስከረም እንዳሉት የያኔ-ሙከራቸዉ ወዲያዉ በሙከራ ቀረ። በተለይ «አሜሪካና ብሪታንያ፤ አሰድ በጥቂት ሳምንታት ዉስጥ ከሥልጣን መወገዳቸዉ ሥለማይቀር ምንም (ድርድር) ማድረግ አያስፈልግም የሚል እምነት ሥለነበራቸዉ ምንም አልተደረገም።» አከሉ አዛዉንቱ ዲፕሎማት።

ከአሕቲሳሪ ሙከራ በሕዋላ፤ የአረብ ሊግ፤ የሩሲያ፤ የኢራን፤ የኢራቅ፤ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ዲፕሎማሲ ከሽፏል። እንደ አሕቲሳሪ ሁሉ ለሠላም ዲፕሎማሲያዊ ጥረታቸዉ ዕዉቅና ኖቤል የተሸለሙት የኮፊ አናን እና እንደ ኮፊ አናን ሁሉ በዲፕሎማሲዉ አርጅተዉ የገረጀፉት የላሕዳር ብራሒሚ ጥረት ለታሪክ ዝክር ከወመዘክር ተከርችሟል።

የድርድር ተስፋ-ሙከራዉ በተደጋጋሚ በመክሸፉ ለአደራዳሪዎች «የማይቻል ተልዕኮ» የሚል ሥም ከወጣላቸዉ በኋላ የተሾሙት ስቴፋን ደ ሚስቱራ ግን ተስፋ አልቆረጡም ነበር።

«የማይቻል ተልዕኮ የሚለዉን ሥም ታስታዉሳላችሁ። አዎ የማይቻለዉ ተልዕኮ የመቻል አዝማሚያ እያሳየ ነዉ።»

የሶሪያ ተፋላሚ ኃይላት፤ የአረብ፤ የፋርስ፤ የቱርክ፤ የአሜሪካ፤ የምዕራብ አዉሮጳ እና የሩሲያ ደጋፊ-አስታጣቂዎቻቸዉ ጄኔቭ-3 በተባለዉ ድርድር ለመሳተፍ መልዕክተኞቻቸዉን ሲልኩ የደሚስቱራ ተስፋ-ተስፋ የወለደ መስሎ ነበር። ከነበር ግን አላለፈም። መልዕክተኞቹ ጄኔቭ በገቡ ማግስት ድርድሩ ተቋረጠ።

ድርድሩ ሳይጀመር ለመቋረጡ ተፋላሚ ኃይላትና ደጋፊዎቻቸዉ ለመዉቃቀስ አልሰነፉም። ለመወቃቀስ፤ መወጋገዝ፤ መዋጋት ከሚጣደፉበት ፍጥነት ግማሹን እንኳ ለመግባባት አለማዋላቸዉ በለንደኑ ወኪላችን ድልነሳ ጌታነሕ አገላለፅ ግራ-አጋቢ ነዉ።

Genf Syrien Konferenz HNC Vertreter Opposition Mistura
ምስል Reuters/D. Balibouse

ከአሕቲሳሪ ጅምር እስከ ደ ሚስቱራ ጥረት አሥራ-አራት ሙከራዎች ተደርገዋል። በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ወጥቷል። ድምር ዉጤት እልቂት። አሕቲሳሪ የመጀመሪያዉን ድርድር ሲሞክሩ በጦርነቱ የተገደለዉ ሕዝብ ሐያ ሺሕ አልደረሰም ነበር።

የአረብ ቱጃሮች፤ የፋርስ፤ የቱርክ፤ የአይሁድ መንግሥታት የአሜሪካ፤ የምዕራብ አዉሮጳ፤ የሩሲያ ኃያል-ሐብታሞች የተነከሩበት ጦርነት ዛሬ ሩብ ሚሊዮን ሕዝብ አልቆበታል። ከሚሊዮን በላይ አካሉ ጎድሏል። ከአስራ-አምስት ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ አንድም ተሰድዷል አለያም ተፈናቅሏል።

አሕቲሳሪ የመጀመሪያዉን ድርድር ሲሞክሩ የተፋላሚዎቹ ቁጥር አስራ-አምስት ተብሎ ይገመት ነበር። ዛሬ እራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለዉን አደገኛ ቡድን ጨምሮ ከአንድ ሺሕ የሚበልጡ ሸማቂ ቡድናት ተፈልፍለዋል። ከመቶ ሺሕ የሚበልጡ ታጣቂዎች ይርመሰመሱባታል።ሶሪያ።

የፖለቲካ ተንታኞች ደጋግመዉ እንዳሉት እስካሁን አሸናፊም ተሸናፊም ያተለየበት ጦርነት የሚቆመዉ ሞስኮ እና ዋሽግተን፤ ቴሕራንና ሪያድ፤ ጠባቸዉን ሲያበርዱብቻ ነዉ። እነዚሕ ኃይላት ሠላም እንዲያወርዱ መሻኢኽ፤ ቀሳዉስት አሁንም ይፀልያሉ፤ ይማፀናሉም።የሮማ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አንዱ ናቸዉ።

«ተፋላሚ ሐይላትን ባስቸኳይ ለማደራደር ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ አስፈላጊዉን ጥረት እንዲያደርግ እማፀናለሁ። በዚያች ተወዳጅ እና የስዉአን ሐገር ለወደፊቱ እርቅ እና ሠላም ለማዉረድ ዋስትና የሚሆነዉ ግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ ሲያገኝ ብቻ ነዉ።»

Syrische Flüchtlinge an der türkisch-syrischen Grenze
ምስል Reuters/O. Orsal

የግብረ ሠናይ ድርጅቶችም አቤት ይላሉ። ተደራደሩ-ወይም አደራድሩ።

«እርዳታ ለማቅረብ ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልጋል።እኛ የሕክምና እንጂ የፖለቲካ ድርጅት አይደለንም። ሥለዚሕ መደራደር የሚገባቸዉ የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸዉ። እርግጥ ነዉ የጄኔቫዉ ድርድር ሲጀመር በጣም ደስ ብሎን ነበር። ድርድሩ በገለልተኝነት ርዳታ ለማቅረብ የምንችልበት ጥሩ አጋጣሚ ሥለሚፈጥር ነዉ።»

ይላሉ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ባልደረባ ሳም ቴይለር። ከድርድር ሌላ-ሌላ መፍትሔ የለም የሚሉ ዲፕሎማቶችም-አሉ። ግን ጥቂት ናቸዉ። በዚያ ላይ የዲፕሎማት ሆዱ---የወፍ ወንዱ----ማለቱ መጥፎ አይደለም።

«ባለፉት ቀናት የሆነዉን ሥንመለከት ይሕ ግጭት በወታደራዊ ሐይል ይፈታል የሚል እምነት ያለዉ ሰዉ ይኖራል ብዬ አላስብም። ወደ ፖለቲካዊዉ ሒደት መመለስ ይገባናል።»

የጀርመኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር። ከወደ ጄኔቭ የፖለቲካዉ ሒደት መጨናጎሉ ሲረጋገጥ ለንደን ላይ የተሰየመዉ የሐብታሞች ጉባኤ ባንፃሩ በጦርነቱ ለተጎዱት ሶሪያዉያን መርጃ አስር ቢሊዮን ዶላር ለማዋጣት ተስማምቷል።

ዓለም ለአንድ ሐገር ሕዝብ መርጃ-ባንድ ጊዜ ይሕን ያሕል ገንዘብ ሲያዋጣ ያሁኑ የመጀመሪያዉ ነዉ። ዋና ምክንያቱ የለንደኑ ወኪላችን ድልነሳ ጌታነሕ እንደሚለዉ ስዉር አይደለም-ችግሩ የአዉሮጳን እምብርት ሥለቧጠጠ ነዉ።

Syrer an der Grenze zur Türkei
ምስል Reuters/O. Orsal

የአፍሪቃን ችግረኞች ለመርዳት፤ አፍቃኒስታን፤ ኢራቅን ዳግም ለመገንባት፤ የፍልስጤም ሕዝብን ችግር ለማቃለል እየተባለ በየጊዜዉ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለመስጠት ቃል ሲገባ-እንሰማለን። ቃል ሲታጠፍ እናያለን። የሶሪያዉን ከሌሎቹ ጋር ማመሳሰል አይቻልም» ይላል የለንደኑ ወኪላችን። ምክንያቱም ይቀጥላል።

ከዶላሩ ቀድሞ የደረሰዉ ግን ተዋጊ ጄት፤ ቦምብ-ሚሳዬሉ ነዉ።የጠመንጃዉ ላንቃ ካልተዘጋ ምግብ መድሐኒትለተቸገረዉ ሕዝብ የሚደርስበት ሥልት መኖሩ እንደገና አጠያያቂ ነዉ። ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ