1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሽልማት ለዴዝሞን ቱቱ

ቅዳሜ፣ መስከረም 26 2005

ሞ ኢብራሂም የተሰኘዉ ተቋም ለደቡብ አፍሪቃዊዉ የፀረ አፓርታይድ ታጋይ ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ ልዩ ያለዉን ሽልማት እንደሚሰጥ አስታወቀ። ተቋሙ ሽልማቱ ሊቀጳጳሱ በዘመናቸዉ ላበረከቱት አስተዋፅኦና በኃያላን ፊት እዉነቱን ለመናገር በመድፈራቸዉ መሆኑን አመልክቷል።

https://p.dw.com/p/16LQN
ምስል picture-alliance/dpa

ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ በጎርጎሮሳዉያኑ የዘመን ቀመር ጥቅምት ሰባት ቀን 1931ዓ,ም ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ክላርከስዶርፕ በተባለች ስፍራ ተወለዱ። ለአባታቸዉ ዘካሪያ ዚሊሎ ቱቱ እና ለእናታቸዉ አሌታ ብቸኛ ወንድ ልጅ ናቸዉ። ለደቡብ አፍሪቃ ደግሞ የመጀመሪያዉ የሀገሪቱ ጥቁር የአንግሊካን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ። በወጣትነታቸዉ ሃኪም ለመሆን የነበራቸዉ ምኞት መምህር በነበሩት አባታቸዉ እና የትምህርት ቤት ምግብ አብሳይ በሆኑት እናታቸዉ ገቢ የትምህርት ወጪዉ ሊሸፈን ስላልቻለ እሳቸዉም ወደማስተማር ነበር ከመነሻዉ የተሰማሩት። ዉለዉ አደሩና ትምህርታቸዉን ሲቀጥሉ የዘለቁት ወደስነመለኮት ጥናት ሆነ። ገና በአፍላ እድሜያቸዉ ለሰዉ ልጆች መብት መቆርቆራቸዉም ዛሬ ለሚያሳዩት ሰብዓዊነት የተላበሰ ባህሪ መገለጫ እንደሆነ ነዉ የሚነገርላቸዉ።  

Mo Ibrahim
ሞ ኢብራሂምምስል DW

አፍሪቃ ዉስጥ አስተዳደራዊ ብስለትን ብሎም ስልጣን ካለግፊት ይብቃኝን ለሚያስተምሩ መሪዎች የጡረታ እድሜያቸዉን የሚያጣጥሙበትን ጠቀም ያለ ዶላር የሚሸልመዉ ሞ ኢብራሂም ለኃያላን እዉነትን በግልፅ ለመንገር ድፍረታቸዉ ልዩ ያለዉን ሽልማት ትናንት ሰጥቷቸዋል። በደቡብ አፍሪቃ የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ ስቲቨን ላዉፈር ሽልማቱ የተሰጠበትን ምክንያት ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል፤

«የሞ ኢብራሂም ተቋም ለረዥም ዘመን ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ ለሰብዓዊ መብት መከበርና ላደረጉት ትግልና ሃቀኝነት ዛሬ ልዩ ሽልማት ለሊቀ ጳጳሳት ዴዝሞን ቱቱ ሰጥቷል።  በተጨማሪም ተቋሙ ቱቱ በእድሜ ዘመናቸዉ እጅግ አከራካሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በባለስልጣት ፊት ሳይቀር ሃቁን ለመናገራቸዉ እዉቅና ሰጥቷል። የልዩ ሽልማቱ ምክንያት ይህ ነዉ።»

ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ ለሰብዓዊ መብቶች በሚያደርጉት ሙግትም ብዙዎች ሊተቹበት የማይደርፉትን እስራኤል በፍልስጤም እንዲሁም ቻይና በቲቤት ላይ ይፈፅማሉ ያሉትን በይፋ ለመተቸት ወደኋላ አለማለታቸዉ ተገልጿል። ሊቀ ጳጳሱ ከዚህ በፊትም የደቡብ አፍሪቃ የአፓርታይድ ስርዓት በሰላም እንዲወገድ ላደረጉት ጥረት የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ናቸዉ። አፍሪቃ ዉስጥም የተለያዩ ግጭቶችን በመሸምገል የሚታወቁትና በግልፅ ንግግራቸዉ የሚከበሩት ቱቱ በሱዳናዊዉ ቱጃር ሞ ኢብራኢም ከተቋቋመዉ የሽልማት ድርጅት አንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ያገኛሉ። ለሊቀ ጳጳሱ የተሰጠዉን ሽልማት ከዚህ ቀደም ተቋሙ ለአፍሪቃ መሪዎች ከሚሰጠዉ ጋ በማነፃፀር ስቲቨን ላዉፈር ሲያስረዱ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፤

Südafrika Nelson Mandela erhällt Rapport der Wahrheitskommission von Tutu
ምስል picture-alliance/dpa

«ተቋሙ በየጊዜዉ በአንድ ወቅት የአንድ የአፍሪቃ ሀገር መሪ ለነበረ የዴሞክራሲ ፅንሰ ሃሳብ ለገባዉና በተገቢዉ ጊዜ ከስልጣኑ ለተነሳ፤ የህግ የበላይነትን ለሚያከብር እና በቀጣይ ለተመረጠ ተተኪ መንበሩን ለሚለቅ ሰዉ ሽልማት ይሰጣል። ይህ በየዓመቱ በዚህ ሁኔታ የሚሰጥ ሽልማት ሲሆን ዛሬ ሊቀ ጳጳስ ቱቱ ከተሰጣቸዉ የተለየ ነዉ። ይሄኛዉ ሊቀ ጳጳስ ቱቱ በእድሜ ዘመናቸዉ ላበረከቱት አስተዋፅኦ የተሰጠ ልዩ ሽልማት ነዉ።»

ሽልማቱ ለሊቀጳጳሳቱ እንደሚሰጥ ይፋ በተደረገበት ሥነርዓት ላይ የተቋሙ መሥራች ሞ ኢብራሂም የጠቆሙት እንዲህ ያለዉ ሽልማት ለቀጣዩ ትዉልድ የዴዝሞን ቱቱን አርያነት የሚያጎላ መሆኑን ነዉ። ከጆሃንስበርግ የወጡ ዘገባዎች እንደጠቆሙትም ሽልማቱ በያዝነዉ የአዉሮጳዉያን ዓመት መገባደጃ ሴኔጋል ዳካር ላይ በይፋ ይሰጣል። ዋና ፅሕፈት ቤቱ ሎንዶን የሚገኘዉ የሞኢብራሂም ተቋም በመልካም አስተዳደሩና በሚከተለዉ የዴሞክራሲ ፈለግ ላከበረዉ የአፍሪቃ መሪ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ሲሸልም፤ ከጎርጎሮሳዉያኑ 2010 ዓ,ም ጀምሮ ግን ይህን መስፈርት የሚያሟላ ባለማግኘቱ ለማንም አልሰጠም።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ