1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሽብር በቱኒዝያ፥ «የእሥላማዊ መንግሥት» መስፋፋት

ሰኞ፣ መጋቢት 14 2007

ዱካውን በአፍጋኒስታንና ፓኪስታን አሳርፎ ሰሜንና ምዕራብ አፍሪቃ መድረስ ችሏል። ከናይጄሪያው ሌላኛው አሸባሪ ድርጅት ቦኮሃራም ጋር መወዳጀቱ፣ በሊቢያ መንሰራፋቱ ይነገርለታል። አሸባሪው ቡድን በሊቢያ የግብፅ ኦርቶዶክሶችን አንገት ለካራ መዳረጉ የቅርብ ትዝታነቱ ገና ሳይዘነጋ፤ በደም የታጠበ እጁን በንዑሷ ቱኒዝያ ለተጨማሪ ጥፋት መዘርጋቱ አልቀረም።

https://p.dw.com/p/1Ev4I
Tunesien Tunis Terroranschlag Bardo Museum Polizei Sicherheit Fahndung
ምስል Reuters/Z. Souissi

ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎቿ ከዓየርም ከምድርም ጦራቸውን አዝምተው ይደበድቡታል። እራሱን «እሥላማዊ መንግሥት በኢራቅ እና በሶሪያ» ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን ግን ዛሬም አልተወገደም። ይልቁንስ ቅርንጫፉን በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለመዘርጋት የተሳነው አይመስልም። ይኽ «እሥላማዊ መንግሥት» በመባል በአጭሩ የሚጠራው ሽብርተኛ ቡድን ዱካውን በአፍጋኒስታን እና ፓኪስታን አሳርፎ እስከ ሰሜንና ምዕራብ አፍሪቃ መድረስ ችሏል። ከናይጄሪያው ሌላኛው አሸባሪ ድርጅት ቦኮሃራም ጋር መወዳጀቱ፣ በሊቢያ መንሰራፋቱ ይነገርለታል። አሸባሪው ቡድን በሊቢያ የግብፅ ኦርቶዶክሶችን አንገት ለካራ መዳረጉ የቅርብ ትዝታነቱ ገና ሳይዘነጋ፤ አሁን ደግሞ በደም የታጠበ እጁን በንዑሷ ቱኒዝያ ለተጨማሪ ጥፋት መዘርጋቱ አልቀረም።

መዲና ቱኒስን ጨምሮ አብዛኞቹ ትልልቅ ከተሞቿ የሚገኙት በረዥሙ የተዘረጋው ሰሜናዊ እና ምሥራቃዊ የባሕር ጠረፏን ታከው ነው። ደቡባዊ ግዛቷ ታች ታቹን እየጠበበ ሄዶ አልጄሪያ እና ሊቢያን ድንበር አዋስኖ ያከትማል። በምዕራብ ከአልጀሪያ፣ በደቡባዊ ምሥራቅ ከሊቢያ ጋር ትዋሰናለች። በጥቅሉ፥ ከላይ ሜዲትራኒያን ባሕርን እየቃኘች ከታች በሰሃራ በረሃ እየነደደች ከመሀከል ትገናለች ቱኒዝያ።

karte Tunesien englisch
ምስል DW

ከጎረቤት አልጄሪያ እንዲሁም ለኹለት በተከፈሉ መንግሥታት ከትሪፖሊ እና ከቤንጋዚ ከምትመራው ሊቢያ ሰርገው የሚገቡ አሸባሪዎችም ገና በማቆጥቆጥ ላይ ባለው የቱኒዝያ ዲሞክራሲ ሌላ ራስ ምታት ፈጣሪዎች መሆናቸው በመነገር ላይ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት መዲና ቱኒስ ውስጥ የሽብር ጥቃት ያደረሱት ታጣቂዎች ሊቢያ ውስጥ ሥልጠና ወስደው እንደነበር ተገልጧል። ይኽ ድርጊት የቱኒዚያን ዲሞክራሲ በእንጭጩ እንዳይቀጨው የጀርመኑ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር አሳስበዋል።

«ጥቃት አድራሹ ማንም ይሁን ማን፤ የጥቃቱ ዓላማ የቱኒዝያን ዲሞክራሲ በእንጭጩ ለመቅጨት ከሆነ፤ በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ያ አይሳካም፣ እንዲሳካም አይፈቀድለትም።»

ቱኒዝያ የዛሬ አምስት ዓመት ግድም በዓረብ ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የተቀዳጀችውን ዲሞክራሲ በእርግጥም ዓለም በስስት ነው የሚመለከተው። ፍራፍሬ ሸቃጩ፣ ወጣቱ ሞሐመድ ቦአዚዚ በቱኒዚያ የደረሰበትን ግፍ መቋቋም እንዳቃተው ገልጦ ራሱን እንደ ጧፍ በእሳት ሲያነድ በሺህዎች የሚቆጠሩ የዲሞክራሲ ናፋቂዎች ከአደባባይ ወጥተው ለመብታቸው ታግለዋል። ብዙዎች ለመብታቸው የማይመለሰውን ክቡር ሕይወታቸውን ገብረዋል።

የሊቢያ ታጣቂዎች ራሳቸው በሠየሙት መንግሥት አስተዳደር
የሊቢያ ታጣቂዎች ራሳቸው በሠየሙት መንግሥት አስተዳደርምስል Reuters/G. Tomasevic

ከዓረብ ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ማግስት ጎረቤት ሊቢያን ጨምሮ ብዙዎቹ የዓረብ ሃገራት ተመሳቅለዋል። ሶሪያ፥ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድን ለመጣል ተቃዋሚዎችን በትጥቅም በስልጠናም ማደራጀት በሚለው የምዕራቡ ዓለም መርኅ የፅንፈኞች ዋነኛ መኖሪያ ከሆነች ሰንብታለች። ለተቃዋሚዎች የተላከው ጦር መሣሪያ ግን እራሱን «እሥላማዊ መንግሥት በኢራቅ እና በሶሪያ» ብሎ ወደ ሚጠራው አሸባሪ ቡድን በእጅ አዙር እንደገባ እና ቡድኑን እንዳጠናከረው ይነገርለታል።

የምዕራቡ ዓለም ጊዜያዊ ጥቅሞች ላይ ያተኮረ ስልት በሌሎች ሃገራትም እያደር ጉዳት ማድረሱ አልቀረም። ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅ ውስጥ «እሥላማዊ መንግሥት»ን ስትወጋ ለዘመናት ከተቃቃረችው ኢራን ጋር በመለሳለስ ነው። የኢራን አብዮታዊ ዘብ ልዩ ኮማንዶ ጦር አዛዥ ብርጋዲየር ጄነራል ቃሲም ሱሌይማን የኢራኑን ጦር በኢራቅ ይመራሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፈውን የየመን መንግሥት ከጨዋታ ውጪ ያደረጉት የኹቲ አማፂዎችን እንደደገፉ ይነገርላቸዋል እኚሁ የኢራኑ ብርጋዲየር ጄነራል።

የመን ሣንዓ የኹቲዎች የሽብር ጥቃት በመስጊዶች
የመን ሣንዓ የኹቲዎች የሽብር ጥቃት በመስጊዶችምስል picture-alliance/photoshot

የሺዓ ኹቲዎች ዓርብ እለት የመን ውስጥ በሚገኙ መስጊዶች ውስጥ ባደረሱት የፈንጂ ጥቃት ከ142 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ዩናይትድ ስቴትስ ጥቃቱን ማውገዟ አልቀረም። እዛው ኢራቅ ውስጥ ግን የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ጄቶች የኢራን ጠላቶች ላይ ቦብንብ ሲያዘንቡ ይታያሉ። ለጊዜው የጠላቴ ጠላት ወዳጄ የሚለውን እየተገበሩ ይመስላል። ሰሞኑን ደግሞ እንዲያ በመድፍ ሲያስቀጠቅጧቸው የከረሙትን የሶሪያውን ፕሬዚዳንት በሽር ኧል አሳድ ማነጋገር ሳይሻል አይቀርም ሲሉም ተደምጠዋል ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎቿ።

ለአራት ዓሥርት ዓመታት ሊቢያን አንድ አድርገው የገዟት አምባገነኑ ሞዓመር ጋዳፊ በምዕራባውያን ድጋፍ በተለይም በፈረንሳይ የጦር ጄት አጀብ፣ አዝማችነት ከሥልጣን ሲወገዱ ሊቢያ ዛሬ ከትሪፖሊና ከቤንጋዚ በሚዘወሩ ሁለት መንግሥታት ጥርስ ሥር ወድቃለች። አሸባሪዎችም ይርመሰመሱባታል።

ቱኒዚያ እና ጎረቤቶቿ
ቱኒዚያ እና ጎረቤቶቿ

የዓረቡ ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የዲሞክራሲ ጥሪ ጎረቤት ቱኒዝያ ላይ ግን ሰሚ ያገኘ መስሎ እስካሁን ዘልቆ ነበር። ሆኖም መሐመድ ቦአዚዚ ራሱ ላይ ለኩሶ ያበራው የዲሞክራሲ ብልጭታ ዛሬ በአሸባሪዎች ጫና እና በመንግሥት የጸረ-ሽብር ትግል ሰበብ ጭራሽ እንዳይከስም ስጋት መፍጠሩም አልቀረም። በቱኒዝያ የሽብር ጥቃት ከደረሰ ወዲህ የሀገሪቱ ዲሞክራሲ አደጋ ተጋርጦበታል ይላሉ የአፍሪቃ ጉዳይ ተንታኟ «የመካከለኛው ምሥራቅ እና አፍሪቃ» የሳይንስ እና የፖለቲካ ተቋም ኃላፊ ኢዛቤሌ ቬረንፌልስ።

«አሁን ጉዳዩ ስለ ፍትኅ ሥርዓቱ ነፃነት፣ ስለ ሕገ-መንግሥቱ ተግባራዊነት ነው። በአጠቃላይ ሕገ-መንግሥቱ ውስጥ ድንቅ በሆነ መልኩ የሠፈረው በእርግጥም እውን ሊሆን ይገባል። አሁን ለምሳሌ ቀድሞውኑም እጅግ ጥብቅ የነበረው እና ከአዳንድ የሠብዓዊ መብቶች እይታ አንፃር በችግር የተሞላው የጸረ-ሽብር ሕጉ አሸባሪነትን ለመዋጋት በሚል የበለጠ የሚጠብቅ ከሆነ ያኔ አደጋ ይደቀናል። ፕሬዚዳንቱ «ሀገሪቱ አሸባሪነትን ለመዋጋት በጦርነት ላይ ናት» ሲሉ እንደተናገሩት አይነት ከሆነ የነፃነት መብትን ሊሸራርፍ፣ ሕገ-መንግሥቱንም ዋጋ ሊያስከፍል ይችል ይኾናል።»

በባርዶ ብሔራዊ ሙዚዬም ጥቃት ከደረሰ በኋላ
በባርዶ ብሔራዊ ሙዚዬም ጥቃት ከደረሰ በኋላምስል AFP/Getty Images/F. Belaid

መቀመጫውን በቱኒዝያ ያደረገው የፍሪድሪሽ ናውማን የነፃነት ተቋም የቱኒዝያ እና የሊቢያ ፕሮጀክት ኃላፊ ራልፍ ኤርብል ግን ከኢዛቤሌ የተለየ ኃሳብ ነው ያላቸው። እንደሳቸው አባባል ከእስላማዊ መንግስት ጋር ግንኙነት ያላቸው ወጣቶች በቱኒዚያ ተበራክተዋል።

ቱኒዝያ 11 ሚሊዮን ግድም ነዋሪዎች እንዳሏት ይነገርላታል። እንዲያም ሆኖ «እሥላማዊ መንግሥት በኢራቅ እና በሶሪያ» የተሰኘውን አሸባሪ ቡድን በሚቀላቀሉት ወጣቶቿ ብዛት በዓለማችን ቀዳሚ አለያም ኹለተኛ ሀገር ተደርጋ ትወሰዳለች። ራልፍ ኤርብል።

«ሦስት ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች ሶሪያ እና ኢራቅ ውስጥ እሥላማዊ መንግሥትን መቀላቀላቸው ይነገራል። ቁጥራቸው ወደ 7000 እና 8000 የሚጠጉ የሀገሪቱ ወጣቶች ጎረቤት ሀገር ሊቢያ ተሻግረው አለያም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አቅንተው ፅንፈኛ ቡድኖችን እንዳይቀላቀሉ ለማከላከል ስማቸው ለፖሊስ እና የፀጥታ ኃይላት ተላልፏል። ስለዚህ ቱኒዝያ የፅንፈኝነት ችግር አለባት። »

ባሣለፍነው ሣምንት ረቡዕ ታጣቂ አሸባሪዎች በቱኒዝያ መዲና ቱኒስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ለፊት 8 ሰዎችን በተኩስ ሩምታ ከገደሉ በኋላ ያቀኑት በአቅራቢያው ወደሚገኘው ብሔራዊ ሙዚዬም ነበር። በውጭ ሃገራት እጅጉን በሚዘወተረው እና ባርዶ በተሰኘው የቱኒዝያ ብሔራዊ ሙዚዬም ፊት ለፊት አሸባሪዎቹ በከፈቱት ሌላ የተኩስ ሩምታ ደግሞ ቢያንስ 11 ሰዎች ተገድለዋል። በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገመት ወጣት ያነገበውን ክላሽንኮቭ አቅንቶ ጥይቶቹን ከአውቶቡሱ በሚወርዱት ሀገር ጎብኚዎች ላይ ሲያርከፈክፍ ማየታቸውን የዓይን እማኞች መስክረዋል።

በቱኒዚያ የደረሰውን የሽብር ጥቃት በመቃወም
በቱኒዚያ የደረሰውን የሽብር ጥቃት በመቃወምምስል Reuters/Mili

ከሽብር ጥቃት ፈፃሚ ታጣቂዎቹ መካከል ኹለቱ ሙዚዬሙ ውስጥ በፀጥታ ኃይላት እንደተገደሉ ተገልጧል። ከ20 የማያንሱ ሰዎች በሽብር ጥቃት ተጠርጥረው ተይዘዋል።«እሥላማዊ መንግሥት» የተሰኘው ቡድንም ከሽብር ጥቃቱ ጀርባ እጁ እንዳለበት ለመግለፅ ብዙም አላመነታም። ከጥቃቱ አንድ ቀን በኋላ፣ ባሳለፍው ሐሙስ ወዲያውኑ ነበር ኃፊነት መውሰዱን ያሳወቀው። በበነጋው ዓርብ ደግሞ የሺዓ ኹቲ ሚሊሺያዎች የመን ውስጥ በሚገኙ 2 መስጊዶች አደረሱት በተባለው ተከታታይ የፈንጂ ጥቃት ለተፈጁት 142 ሰዎች እልቂት ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ብሏል፤ እራሱን «እሥላማዊ መንግሥት በኢራቅ እና በሶሪያ» ብሎ የሚጠራው ይኸው አሸባሪ ቡድን።

እንደ ጎርጎሪዮሣዊው አቆጣጠር ከ2012 አንስቶ በቱኒዝያ የፀጥታ እና ደኅንነት ጉዳይ እየተበላሸ በመምጣቱ ወደ ሰሜን አፍሪቃዊቷ ሀገር ለጉብኝት እና መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ የሚመጡ የውጭ ሀገር ሰዎች ቁጥር አሽቆልቁሏል። ቱኒዝያ ኢኮኖሚዋ ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ መሠረቱን ያደረገው በቱሪዝም ዘርፍ ከሚገኝ ገቢ እንደሆነ ይነገራል።

የባርዶ ብሔራዊ ሙዚዬም ጥቃት አድራሾች በደኅንነት ካሜራ
የባርዶ ብሔራዊ ሙዚዬም ጥቃት አድራሾች በደኅንነት ካሜራምስል picture-alliance/dpa/Tunisan Interior Ministry

ቱኒዝያ በዘመናዊ ሕገ-መንግሥት ሥርዓት የምትተዳደር ሲሆን፤ ዓለማዊ እና ሃይማኖታዊ ፓርቲዎች በጥምረት የሚመሩት የሀገሪቱ መንግሥት ፕሬዚዳንቱን ከመረጠ ገና ሦስት ወርም አላለፈ። ምክር ቤቱ ፊት ለፊት እና የቱኒዚያ ዋነኛ ገቢ የሆነው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ጥቃት በመሰንዘር በምርጫ ስልጣን ላይ የወጣውን መንግሥት በጂሃድ ለመቆጣጠር የሚጣጣሩ ቡድኖች በቱኒዝያ እንደሚርመሰመሱ ይነገራል። ሆኖም ከእስላማዊ መንግሥት ጋር አብረው ለመዋጋት ሶሪያ እና ኢራቅ ሄደው የተመለሱ የቱኒዝያ ወጣቶች በሄዱበት ቦታ ያዩት ነገር ከብዥታ የጸዳ አመለካከት እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ ተንታኟ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በቱኒዝያ የሽብር ጥቃት ከደረሰ በኋላ ጥበቃ በዓየር ማረፊያ
በቱኒዝያ የሽብር ጥቃት ከደረሰ በኋላ ጥበቃ በዓየር ማረፊያምስል Belaid//AFP/Getty Images

«በቱኒዝያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የዓረብ ሃገራትም የሚገኙ በርካታ ተመላሾች ከተሳሳተ አመለካከታቸው ነፃ የሆኑ ናቸው። እያንዳንዱ ተመላሽ ጽንፈኛ ይሆናል ብቻ ማለት አንችልም። ሶሪያ ውስጥ ባዩት ነገር ጽንፈኝነታቸውን እርግፍ አድርገው ሊተዉ ወይንም ከነበሩበት ብዥታ እና የቀን ቅዠት ሊወጡ የሚችሉ አሉ። »

ቱኒዝያ ውስጥ ከእስላማዊ መንግሥት ጋር ቅርበት አለያም ከሌላኛው ሽብርተኛ ቡድን ኧልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው እስልምና አክራሪ ቡድኖች ይገኛሉ። እነዚህ ቡድኖች በሰሜን አፍሪቃ የዓረብ ማግሬብ ኅብረት አባል ሃገራት ውስጥ የሚገኙ አክራሪዎችን የራሳቸው ለማድረግ በተደጋጋሚ እርስ በእርስ ሲቃረኑ ቢታይም ልክ ፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ውስጥ እንደተከሰቱት የሽብር ጥቃቶች ትብብር ሲያደርጉም ይታያል፤ እንደተንታኟ ገለጣ። በፓሪስ ሻርሊ ኤብዶ በተሰኘው የስላቅ መጽሔት ሕንጻ ውስጥ እና በአይሁድ የሸቀጥ መደብር ውስጥ የተፈጸሙትን የሽብር ጥቃቶች ትብብር ማስታወስ ይቻላል። የተለያዩ ቡድኖች ለአንድ ዓላማ የቆሙበት የሽብር ጥቃት።

በቱኒዝያ በበላይነት ለመውጣት ጽንፈኛ ቡድኖች እርስ በርስ የሚያደርጉት ፍትጊያ እንዳለ ሆኖ በሀገሪቱ የሰፈነው የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግርም ወጣቶችን ወደ ጽንፈኝነት ጎዳና እንደሚገፈትራቸው ይነገራል። በቱኒዚያ ሥራ አጡ ወጣት ቁጥሩ ከፍተኛ ነው። በተለይ በሀገሪቱ የባሕር ጠረፍ ላይ በተዘረጉ ትልልቅ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ወጣቶች ኑሯቸውን በቅጡ ለመግፋት የሚያስችል የሥራ ዕድል እንደሌላቸው፤ ካለም እጅግ ውስን እንደሆነ ይነገራል። ይሁንና በአንድ ሀገር መሠረታዊ ሠብዓዊ መብቶች እስከተከበሩና የሕግ የበላይነት እስከሰፈነ ድረስ ኢኮኖሚያዊ እድገቱም ያን ፈር ተክትሎ እንደሚመጣ ወጣቶቹ አያጡትም። ለዚህም ነበር የዓረቡን ዓለም ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ የጀመሩት እና ለሌሎችም አርዓያ ለመሆን የበቁት።

ሰልፈኞች የሞሐመድ ቦአዚዚን ፎቶ አንግበው
ሰልፈኞች የሞሐመድ ቦአዚዚን ፎቶ አንግበውምስል picture-alliance/AP Photo/Salah Habibi

ይኽ በበርካቶች የሕይወት መስዋዕትነት የአምባገነኑ ፕሬዚዳንት ቤን ዓሊ አስተዳደርን ገርስሶ መታየት የጀመረ የቱኒዝያ የዲሞክራሲ ጭላንጭል በአክራሪዎች እና አሸባሪዎች አለያም እነሱን ለመዋጋት በሚል ሰበብ በሚወጡ ሕጎች እንዳይከስም ማሳሳቡ አልቀረም። ኃያላኑ መንግስታት በበኩላቸው የቱኒዝያ ሕዝብ የዲሞክራሲ ጥያቄ እንዳይጨነግፍ ሙሉ ትኩረታቸውን መስጠታቸው አልቀረም። በእርግጥም ቱኒዝያ ከዓረቡ ዓለም ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ማግሥት መሥመር ስተው በአሸባሪዎች እና ጽንፈኞች እጅ ከመውደቅ የተረፈች ሃገር ናትና፤ ትኩረት ያሻታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ