1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቀልድ ወደ ፖለቲካ ሲቀየር

ዓርብ፣ ሐምሌ 14 2009

የተወሰኑ እዚህ ጀርመን የሚገኙ ታዳጊዎች ለአንድ ሳምንት ያህል ራሳቸውን የአውሮጳ ኅብረት የምክር ቤት አባል ብሆን ብለዉ ፈትነዋል። እንደ ቀልድ የፖለቲካዉን ዓለም መቀላቀል የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ርዕስ ነው።

https://p.dw.com/p/2gnsP
Bonn Friedrich-Ebert-Gymnasium
ምስል DW/Nina Niebergall

Jugend 210717 EU-Parlamentsspiel in Schulen - Report - MP3-Stereo

ለስብሰባ ወደ ጀርመን የቦን ከተማ መዘጋጃ ቤት አዳራሽ ለመግባት ብዙ ግርግር አለ። የቦን ከተማ የፍሪድሪክ ኤበርት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በሩ እስኪከፈት እየጠበቁ ነው። ወንዶቹ ጥቁር ሱፍ እና ነጭ ሸሚዛቸውን አድርገዋል። አንዳንዶቹ እንደውም ክራቫትም አስረዋል። ሴቶቹም በፊናቸው፤ ቀሚስ ወይም ሱሪያቸውን አድርገው እንደ ትልልቆቹ ወይዘሮ ፖለቲከኞች ዘንጠዋል። ምክንያቱም ስብሰባው የባለስልጣናት ነው።  ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሁሉም የአውሮጳ የምክር ቤት የሕዝብ ተወካዮች አባላት ይሆናሉ።

ለወትሮው ስለቦን ከተማ ጉዳይ ዉይይት በሚደረግበት አዳራሽ ዛሬ የአውሮጳ ኅብረት ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ተቀምጠዋል። በምሥራቅ አፍሪቃ የተከሰተው ድርቅ ፣ አለም አቀፍ ሽብርተኝነትን መዋጋት፤ ከቱርክ ጋር ኅብረቱ ያለው ግንኙነት ሌላም ሌላም። ዕድሜያቸው ከ 14-16 የሆኑት 135 ተማሪዎች ብራስልስ የሚሰበሰቡትን ፖለቲከኞች ለመምሰል ይሞክራሉ። ለአንድ ሳምንት ያህል የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የግሪክ የምክር ቤት አባል ብሆን ኖሮ ይላሉ።

የምክር ቤቱ የድርድር አጀንዳ የተከፈተው በምሥራቅ አፍሪቃ ጉዳይ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ስለተጠቁበት ድርቅ እና በታጣቂዎች መካከል በተደጋጋሚ ስለሚከሰቱ ግጭቶች። ጉዳዮን ከመገናኛ ብዙኃን የሰሙት ወጣቶች የአፍሪቃ ኅብረት ምን ማድረግ ይችላል? ብለው ይመክራሉ። የተወሰኑት ተማሪዎችም በጋራ ያሰባሰቡትን የመፍትሄ ሀሳብም ለተሰብሳቢው ያሰማሉ። የውኃ ማውጫ ጉድጓድ መገንባት፣ ከሃገራቱ ጋር ነፃ የንግድ ስምምት መድረስ ፤ የአውሮጳ ኅብረት -የግጭቶች የመፍትሄ ሃሳብ አፈላላጊ መሆን ከቀረቡት የመፍትሄ ሀሳቦቹ መካከል ናቸው። ከዛም በቀረቡት ሀሳቦች ላይ ወጣቶቹ ትችት ይሰነዝሩ ጀመር፤ «የአውሮጳ ኅብረት -የግጭቶች የመፍትሄ ሃሳብ አፈላላጊ ይሁን የሚል ሀሳብ ቀርቧል ፤ ነገር ግን እንዴት ብለው ነው አደገኛ በሆነ እና ጦርነት ያለበት ቦታ ድርጅቶች ጥቃት ቢሰነዘርባቸው የሚከላከሉት? »

Bonn Friedrich-Ebert-Gymnasium
ምስል DW/Nina Niebergall

ይህ ብቻ አይደለም ይላል ከጊዜያዊው የምክር ቤት አባላቱ አንዱ፤ በውስጡ ያለውን ፍርሃት እንደምንም እየዋጠ እና ድምፁን ጎላ እያደረገ፤« የሰብዓዊ ዕርዳታ፤ የውኃ ማውጫ ጉድጓድ በመቆፈር፤ ቦዮች፣ ቱቦዎች የመሳሰሉት፤ በዚህ ብዙ ገንዘብ በሚያስወጣ የውኋ ጉድጓድ ፋንታ፤ ለጊዜው እነዚህን ሰዎች በየዕለቱ ንጹህ ውኃ የሚያገኙበት መንገድ ላይ መወያየት ያስፈልጋል። በዚህ ላይ መጨመር የምፈልገው ነገር፤ እነዚህ እቅዶች አንድን መንግሥት ከሌላኛው የበለጠ ስልጣን በመስጠት ግጭት ሊያስነሱ እንደሚችሉ ነው። ይህ ግጭት ደግሞ ጭራሽ ጦርነት ሁሉ ሊያስነሳ ይችላል። ስለዚህ የአውሮጳ ኅብረትን ከሩቅ ለመመልከት አዳጋች ያደርገዋል።»

በዚህ ሁኔታ ክርክሩ ተጧጧፈ። የአየርላንድ ጊዜያዊው የምክር ቤት ተወካይ የሆነችው ሌላኛዋ ተማሪ ተነሳች፤ የአውሮጳ ኅብረት ድጋፍ የሚሰጠው የተወሰኑትን ሃገራት መርጦ አይደለም። ድጋፋችን ለሁሉም አገሮች ነው የሚሆነው። በማለት ቀጠለች፤« አስቀድሞ ስለፖለቲካው መረዳት ያስፈልጋል። የአውሮጳ ኅብረት በቀጥታ በተጋጩት ሃገራቱ መካከል ሳይገባ ፤ ሃገራቱ አለመግባባታቸውን በኃይል ሳይሆን በሰላም  ለመፍታት እንዲችሉ ዕድሉን ይፈጥርላቸዋል።»

ለዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎቹ ብዙ ነገሮች ግልፅ አይደሉም። የትኛው ሠራዊት ነው ኃላፊነት የሚወስደው? የአውሮጳ ኅብረት ጦር የለውም ይላል አንዱ፤ ሙስና መስፋፋቱን በምን ማረጋገጥ እንችላለን? ይላል ሌላኛው። ትላልቅ የውኃ መተላለፊያ ቧንቧዎች በሃገራቱ መሬት ሲዘረጋ ፍቃደኞች ናቸው? የሚሉ ሌላም ሌላም ጥያቄ እና ሀሳቦች ተሰነዘሩ።

 የምክር ቤቱ ቦርድ ድርድሩ መስመሩን ጠብቆ መሄዱን ይቆጣጠራል። ሁሉም ተከባብረዉ እና አንቱ እየተባባሉ ነው የሚወያዩት።  ለውጥ የሚሹ ነገሮች በጽሑፍ ነው የሚቀርቡት። የድምፅ አሰጣጥ እና ምርጫውም እውነታውን የመሰለ ነው። አላማው አስመስለው ተማሪዎቹ እውነተኛውን ዲሞክራሲ በተግባር እንዲያዩት ለማድረግ ነዉ።

« ተማሪዎቹ አንድ ወረቀት ላይ የጋራ አቋምን የሚያንፀባርቅ ኃሳብ በጹሁፍ ለማቅረብ ምን ያህል አድካሚ እንደሆነ እንደዚህ በተግባር ይማራሉ።» ይላሉ የፖለቲካው መምህር ማርኩስ ማተርን። «   በትምህርት ቤታችን 9ኛ ክፍል ላይ የፖለቲካ ትምህርት በተወሰነ ደረጃ ነው የሚሰጠው፤ ይህ ፕሮጀክት ተማሪዎቹ ለትምህርቱ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ተብሎ የተዘጋጀ ነው።»

መምህር ማርኩስ ማተር
ምስል DW/Nina Niebergall

አስተማሪው እቅዳቸው የተሳካ ይመስላል። ተማሪዎቹ ለጉዳዮ ትኩረት ሰጥተዋል።« የመፍትሄ ረቂቁን ባዘጋጀንበት ወቅት ስለወቅታዊ የአውሮጳ የፖለቲካ ሁኔታ ለመገንዘብ ችለናል። ስለዚህ ለወደፊት የሚጠቅመን ብዙ ነገር ተምረናል ብዬ አምናለሁ።»

ይላል የ14 ዓመቱ ኢቲኔ። እሱ እንደሚለው እንደቀልድ ስለፖለቲካው ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የተማረው ፤ አሁን ከበፊቱ በተሻለ መልኩ ሀሳቡን መግለፅ እና  መወያየት ችሏል። ሌላኛው ተማሪ ፊቴ ደግሞ ጠዋት በምክር ቤቱ ስለተወያዩበት ጉዳይ ከትምህርት ቤት በኋላም ከጓደኞቹ ጋር የሚወያይበት ርዕስ ሆኗል። ቤን ደግሞ፤«በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እንዴት መወያየት እንደሚቻል እና በጋራ መፍትሄ እንደሚፈለግ ተምሬያለሁ። ወደፊት በፖለቲካ ጉዳይ ይበልጥ ተሳትፎ ለማድረግ እና ምናልባትም በሥራው ዓለምም በዚሁ መሳተፍ እፈልጋለሁ።»

ሊውዘ በአውሮጳ ፓርላማ ሞዴል ስትሳተፍ አሁን አራተኛ ጊዜዋ ነው። ከመላው ጀርመን ከተሰባሰቡ ተማሪዎች ጋር ለመወያየት በርሊን ከተማ ድረስ ሄዳለች። « በመጀመሪያ የተረዳሁት ነገር ቢኖር፤ በእኛ ዕድሜ ወይም ከኛ በታች ላሉ ልጆች ፖለቲካ አስደሳች ሊሆን መቻሉን ነው። ውስብስብ የሆኑ ነገሮችን መረዳት እና ማገናዘብ ይቻላል። ምንም እንኳን ወጣት ቢኮንም ስለ ጉዳዮ ማሰብ እና ሀሳብ መስጠት ይቻላል። እና ከዛን ጊዜ ጀምሮ ፖለቲካ ያስደስተኛል። መረጃም ለማግኘት እጥራለሁ። »

ሊውዘ ፣ማርቲን እና ጊሲነ የምክር ቤቱ የቦርድ አባላት ናቸው።
ምስል DW/N. Niebergall

የ11ኛ ክፍል ተማሪዋ ፣ማርቲን እና ጊሲነ የምክር ቤቱ የቦርድ አባላት ናቸው። ይህንን ስልጣን ያገኙት የአውሮጳን ኅብረት አስመስለው ሲወያዩ በቂ ልምድ ከቀሰሙት ተርታ የተሰለፉት ናቸው።  ሁሉም አሁን ፖለቲከኛነትን ማስመሰል ብቻ ሳይሆን ወደ እውነታዉ የፖለቲካ ዓለም ገብተዉ የፓርቲ አባል ሆነዋል። በፖለቲካው ዓለም መሳተፍ የሁሉም ፍላጎት አይደለም። አንዳንዶች ፊት ለፊት ቆመው ንግግር ሲያደርጉ እና ምክር ቤቱ የሰጣቸውን መብት ለማሳየት ሲሞክሩ፤ አንዳንዶች ከኋላ ደብሯቸው ያዛጋሉ። ለሁሉም ተማሪዎች ግን ይህ ፕሮጀክት የትምህርታቸው አንድ ክፍል ነው። የተማሪዎቹ ተሳትፎ ተገምግሞ ውጤት ይሰጥበታል። መምህራቸውን ይበልጥ የሚያስደስታቸው ግን በተማሪዎቹ አስተሳሰብ ላይ የሚጭሩት የፖለቲካ ፍላጎት ነው።

«ከነዚህ 135 የ9ኛ ክፍል ተማሪዎች 20 በመቶው ኋላ ላይ በፍቃደኝነት ጋዜጣ የሚያነቡ ከሆነ ወይም ዜና የሚከታተሉ ከሆነ፤ ወይም ደግሞ በዚህ ልምምድ ተካፍላ የነበረች አንዲት ተማሪ እንደነገረችኝ፤ መምህር « ትናንት በቴሊቭዥን አንድ የምክር ቤት ዘገባ አይቼ ነበር፤ ሁሉም ነገር ገብቶኝ እስከ መጨረሻው ተከታተልኩ» ስትለኝ፤ ፕሮጀክቱ ጥሩ ነበር እንድል ያደርገኛል።»ይላሉ መምህር ማርኩስ ማተርን።

ተማሪዎቹ ጊዜያዊ የአውሮጳ ኅብረት ተወካዮች በዛሬው አጀንዳቸው የተወያዩበት ለምሥራቅ አፍሪቃ ድርቅ መፍትሄ የማፈላለግ ሀሳብ በመጨረሻ ድምፅ ተሰጥቶበታል። ድርቁን ለመከላከል የአውሮጳ ኅብረት የሚኖረው የምሥራቅ አፍሪቃ ተሳትፎ ባገኘዉ መጠነኛ ድምፅ ምክንያት ለጥቂት ሳይጸድቅ ቀርቷል። ለአንዳንዶች ሀሳቡ በቂ መፍትሄዎችን ይዞ አልቀረበም። አንዳንዶች ደግሞ ኅብረቱ ብዙ ጣልቃ ሊገባ አይገባዉም ባይ ናቸው፣ ለሌሎቹ እቅዱ ተጨባጭ መስሎ አልታያቸዉም። ዞሮ ዞሮ በመጨረሻ ሁሉም የራሳቸው የሆነዉን ሃሳብ ይዘዋል።

ኒና ኒበርጋል / ልደት አበበ

ሸዋዬ ለገሰ