1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቁጣ የቀሰቀሰዉ የቱርክ ባለስልጣናት አስተያየት

ሰኞ፣ የካቲት 27 2009

የቱርክ ባለስልጣናት በጀርመን ለሚገኙ ቱርካውያን በመጪው ሚያዝያ በቱርክ ሊካሄድ በታቀደው ህዝበ-ውሳኔ ላይ በጀርመን አንዳንድ ከተሞች ሊያደርጉት የነበረው ቅስቀሳ መታገዱን ተከትሎ ፕሬዚዳንት  ራቺፕ ጣይብ ኤርዶኃን እገዳዉን  ከናዚ ሥራ ጋር ማዛመዳቸዉ በጀርመን በርካታ ፖለቲከኞችን አስቆጥቶአል።

https://p.dw.com/p/2YjMT
Sprachkenntnis bei Ehegattennachzug Symbolbild deutsch-türkische Ehe
ምስል Sean Gallup/Getty Images

Q& A _Politische Krise Zwischen Türkei und Deutschland - MP3-Stereo

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የምትገኘዉ ቱርክ ሰብዓዊ መብት እየተጣሰና ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች እየታሰሩና ከስራ እየተባረሩ ባለበት አስተዳደር ባለስልጣናት ጀርመን  መጥተዉ የጀርመን ዜግነት ያላቸዉን ቱርኮች መቀስቀስ ይችላሉ አይችሉም በጀርመን ፖለቲከኞች ዘንድ አከራካሪ ርእስ ሆኖ ሰንብቶአል። የእገዳው ውሳኔ የተወሰደው በማዘጋጃ ቤቶች መሆኑን የተናገሩት መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በሃገራቱ መካከል የተቀሰቀሰዉን አተካራ ለማርገብ ከቱርኩ አቻቸዉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢናሊ ይልድሪም ጋር በሳምንቱ መጨረሻ በስልክ ተነጋግረዋል። የቱርኩ የኤኮኖሚ ሚንስትር ኮሎኝ ተገኝተዉ ለቱርክ ተወላጆች ንግግር አድርገዋል፤ ነገ ማክሰኞም ሃምቡርግ ከተማ ይመጣሉ ተብሎ የተጠበቁት ሚኒስትሩ እንደማይመጡ ከመሸ በወጣ ዜና ተረጋግጦአል። በጀርመን አንፃር ባለፉት ቀናት ከቱርክ መንግሥት ስለተሰነዘረ አስተያየት የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ ሽቴፈን ዛይበርት ዛሬ በበርሊን ለጋዜጠኞች  በሰጡት መግለጫ ላይ «ከናዚ ዘመን ጋር የሚደረግ ማንኛውም ንፅፅር» በመሰረቱ እውነታውን የሚያዛባ ነው ሲሉ አስተያየቱን ውድቅ አድርገውታል።  « በዴሞክራሲያዊት ጀርመን እና በናዚ ዘመን ፖሊሲዎች መካከል የሚደረግ ማንኛውንም ንፅፅር አጥብቀን እንቃወማለን።  እንደነዚህ ዓይነቶቹ ንፅፅሮች ሁሌም የማይረቡ እና አለቦታቸው የሚሰነዘሩ ናቸው፣ ምክንያቱም፣ በስብዕና አንፃር የተፈጸሙ ወንጀሎችን አስተናንሶ ወደማየቱ ያመራሉ።»
ዛይበርት ከዚሁ ጋር በማያያዝም ቱርክ በወቅቱ በሀገሯ በእስር ላይ የሚገኘው የጀርመን እና የቱርክ ዜግነት ያለው ጋዜጠኛ ዴኒስ ዩቼል ባስቸኳይ እንድትፈታ ጠይቀዋል። በጀርመን የቱርካውያን ማህበረሰብ ሊቀመንበር ገካይ ሶፉዎግሉም የፕሬዚደንት ኤርዶኻንን ትችት እላፊ የሄደ ነው ሲሉ በጥብቅ ነቅፈዋል። የቱርክና የጀርመን ፖለቲከኞች የቃላት ጦርነትን በተመለከተ የበርሊኑን ወኪላችንን አነጋግረነዉ ነበር።  

Mevlüt Cavusoglu türkischer Außenminister
ምስል picture-alliance/dpa/B. Ozbilici


ይልማ ኃይለሚካኤል
አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሃመድ