1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተወካዮች ምክር ቤት የመቀመጫ ብዛት ወደ 660 ከፍ እንዲል ተወስኗል።

ሰኞ፣ ጥቅምት 27 2010

ለድርድር የተቀመጡት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥርዓቱ ወደ ቅይጥ ትይዩ እንዲቀየር ከስምምነት ደርሰዋል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመቀመጫ ቁጥርም አሁን ካለበት 550 ወደ 660 ከፍ እንዲል ወስነዋል። ለመሆኑ ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ስርዓት ምን አይነት ነው? 

https://p.dw.com/p/2n8IH
Äthiopien Parlamentswahlen
ምስል Reuters/T. Negeri

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 660 መቀመጫዎች ይኖሩታል

ከረጅም ጊዜ ውይይት እና ድርድር በኋላ በሥልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር እና ወደ 11 ገደማ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ቅይጥ ትይዩ እንዲሆን መስማማታቸውን አስታውቀዋል። ድርድሩ ሲጀመር ተቃዋሚዎች የምርጫ ሥርዓቱ ሙሉ ተመጣጣኝ ገዢው ግንባር ደግሞ ቅይጥ ትይዩ ይሁን የሚሉ ሐሳቦች ነበሯቸው። አቶ ሙሉጌታ አበበ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅትን ወክለው በድርድሩ ከተሳተፉ መካከል አንዱ ናቸው።

"ወደ አስራ አንድ የምንሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ላይ ሙሉ ተመጣጣኝ ውክልና የሚል ነው ይዘን የነበረው። ኢሕአዴግ ደግሞ  ቅይጥ ትይዩ የሚል ነው ይዞ የመጣው። ቅይጥ ትይዩ የሚለው ሙሉ አይደለም በመቶኛ አስቀምጥ ብለንው ነበረ።  90/10 በመቶ ብሎ አስቀመጠ።ባደረግንው ክርክር 15 በመቶ አስገባ። እንደገና ውሳኔ ወስነን ልናልፍ ስንልጊዜ ስጡን ብሎ ጠይቆ ነበር። ያንን ጊዜ ወስዶ 5% ጨምሮ 20/80 ብሎ መጣ። እኛ ሙሉ ተመጣጣኝ ውክልናን ወደ ቅይጥ ትይዩ ያመጣንው መቶኛው 50/50 እንዲሆን ነበር። በኢሕአዴግ ባሕሪ አንፃር ከ20 በላይ ወደ ላይ መውጣት እንደማይፈልግ አስቀመጠ። ረጅም ክርክር አደረግን። ከዛም በኋላ ሌሎቹ የያዝናቸው የሕዝብ አጀንዳዎች በዚህ ከዚህ በላይ መቆየት አስፈላጊ ስለማይሆን ብለን 20 በ 80 {የፖለቲካ} ምኅዳሩን ያሰፋል ብለን ባናምንም በልዩነት ተቀብለን ወደ ሌሎቹ ድርድር አልፈናል።"  

Äthiopien Parlamentswahlen
ምስል DW/Y. G. Egziabhare

የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ስትከተል ሁለት አስርት አመታት ለዘለቀችው ኢትዮጵያ ለውጡ ምን ይሆን?  አቶ ውብሸት ሙላት የሕገ-መንግሥት ጥናት ባለሙያ ናቸው። 

"ከአንድ የምርጫ ጣቢያ ላይ አንደኛ የሆነውን እያሳለፍን የምንጠቀምበት አንድ የምርጫ ሥርዓት አለ። በዚህ መንገድ 80 በመቶውን አሁን በተስማሙበት መንገድ በየምርጫ ጣቢያው ድምፅ ይሰጣል ማለት ነው። በሁለተኛ መንገድ ደግሞ ተመጣጣኝ ውክልና የሚባል የምርጫ ሥርዓት አለ። ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ማለት ለፌድራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚመረጥ ሰው አገሪቱ እንደ አንድ የምርጫ ጣቢያ ትወሰድና ፓርቲዎችን ብቻ ሰዎች ይመርጣሉ። ለምሳሌ 100 ወንበር ለመውሰድ ከሆነ የተገኘው ድምፅ ለመቶ የምርጫ ወንበር ይሰላና ባገኙት መጠን ወደ ፓርላማ ይገባሉ ማለት ነው።"

አቶ ሙሉጌታ አበበ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የተስማሙበት የቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት "ጠቧል" እየተባለ የሚወቀሰውን የፖለቲካ ምኅደር ከመሰረቱ እንደማይቀይር እምነታቸው ነው። ከ20 ዓመታት በላይ ዘልቋል የሚሉትን የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት መቀየር በራሱ ስኬት እንደሆነ ግን ይናገራሉ።

የሕገ-መንግሥት ጥናት ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ስርዓት ተግባራዊነት ውስብስብ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። የምርጫ ሥርዓቱ ለአስተዳደር ምቹ አለመሆኑ ለማጭበርበር ተጋላጭ ሊያደርገው እንደሚችልም ሥጋት አላቸው።

ለድርድር የተቀመጡት የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመቀመጫ ወንበሮች ብዛት ወደ 660 ከፍ እንዲል ከሥምምነት መድረሳቸውን አቶ ሙሉጌታ አበበ ጨምረው ተናግረዋል። አቶ ሙሉጌታ 110 ወንበሮች መጨመራቸውን ተቃዋሚዎች ባይቀበሉም ገዢው ግንባር "ቴክኒካዊ ችግር አለብኝ" በማለቱ "በልዩነት" እንዳለፉት ገልጠዋል። 


እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ