1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሆንግ ኮንግ የቀጠለው ተቃውሞ

ሰኞ፣ መስከረም 19 2007

የቻይና ልዩ አስተዳደር ግዛት፥ ሆንግ ኮንግ ተማሪዎች መብታቸው እንዲከበር እና ነፃ ምርጫ እንዲካሄድ በመጠየቅ የጀመሩት የተቃውሞ ሰልፍ እጅግ በመጠናከሩ ድርጊቱ የሆንግ ኮንግን አስተዳደርን ብቻ ሳይሆን የፔኪንግ መንግሥትንም አስደንግጧል።

https://p.dw.com/p/1DNHV
Demonstrationen Hongkong 29.09.2014
ምስል AFP/Getty Images/Alex Ogle

በቻይና የሆንግ ኮንግ ግዛት በሺዎች የሚቆጠሩ መፍቀሬ ዴሞክራሲ ሰልፈኞች የከተማይቱን የፊናንስ ማዕከል በመክበብ የጀመሩትን ሰላማዊ ተቃውሞ ዛሬም እንደቀጠሉ ይገኛሉ። ልዩ አስተዳደር መብት ያለው ግዛታቸው ተጨማሪ ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲኖሩት በመጠየቅ አደባባይ የወጡት ተቃዋሚዎች የያዙትን አካባቢ ለማስለቀቅ ተሰማርቶ የነበረው ልዮ የፀጥታ አስከባሪ ኃይል ተቃውሞው በሰላማዊ መንገድ በመካሄዱ የተነሳ ፣ በወቅቱ መነሳቱን ፖሊስ አመልክቶዋል። ልዩው ኃይል ቀደም ሲል ተቃዋሚዎችን ለመበተን በቆመጥ፣ በሚያስለቅስ ጢስ እና በቁንዶ በርበሬ ስፕሬይ በመጠቀም ያደረገው ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱ ተገልጾዋል። የሆንግ ኮንግ አስተዳዳሪ ሎይንግ ቹን ዪንግ ተቃዋሚዎች የያዙትን አካባቢ እንዲለቁ ተማፅነዋል።

China Studentenprotest in Hongkong Occupy Central Regenschirm und Deminstrant
ምስል X. Olleros/AFP/Getty Images

« መንገዶችን የዘጉት ሰዎች ትራፊኩን እና የሕዝቡን ዕለታዊ ኑሮ እንዳያውኩ አካባቢውን ባስቸኳይ በሰላም እንዲለቁ አሳስባለሁ። «occupy central» የተባለው ተቃውሞ አስተባባሪዎችም ለኅብረተሰቡ ጥቅም ሲሉ የያዙትን አካባቢ የያዙበትን ድርጊት እንዲያበቁ አሳስባለሁ። »

የቻይና መንግሥት ድርጊቱን ሕገ ወጥ ብሎታል።

ተቃዋሚው ለፖሊስ የኃይል ተግባር እንደማይንበረከክ አስተባባሪው ቻን ኪን ማን አስታውቀዋል።

« ሰዎች ዴሞክራሲ እንዲሰፍን በመጠየቅ ዛሬም አደባባይ መውጣታቸው የሚያበረታታ ነው። ብዙ ሰዎች «ሀቀኛ ዴሞክራሲ እንፈልጋለን፤ ሀቀኛ ምርጫ እንፈልጋለን።» የሚሉ መፈክሮችን ያሰሙ ነበር። የንቅናቄአችን ዓላማም ይህ ነው። እና ዛሬ በታየው ሁኔታ ተደስተናል። »

ተቃዋሚዎቹ ተቃዋሚዎች እአአ በ2017 በሆንግ ኮንግ በሚደረገው የግዛቱ አስተዳዳሪ ምርጫ ላይ የቻይና ማዕከላይ መንግሥትን ፈቃድ ያገኘ ዕጩ ብቻ እንዲቀርብ የወጣውን ውሳኔ ውድቅ አድርገውታል። የቀድሞ የብሪታንያ ዘውድ ቅኝ ግዛት የቻይና አካል ከሆነች ከ1997 ዓም ወዲህ በግዛቱ ትልቅ ተቃውሞ ሲካሄድ ያሁኑ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።

በሆንግ ኮንግ የቀጠለን የተቃውሞ ሰልፍ አስመልክቶ በርሊን የሚገኘው የዶይቸ ቬለ ወኪል- ይልማ ኃይለሚካኤል ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል።

ይልማ ኃይለሚካኤል

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ