1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሐጅ የሞቱ ኢትዮጵያውያን

ዓርብ፣ መስከረም 21 2008

በአመታዊው የሐጅ የጸሎት ስነ-ስርዓት ላይ በደረሰው አደጋ ከሞቱት አብላጫውን ቁጥር የያዙት ኢራናውያን ናቸው። የኢራን መንግሥት464 ዜጎቹ መሞታቸውን አረጋግጧል።የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደግሞ የሞቱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 13 መድረሱን አስታውቋል። የሟቾች ቁጥር ግን ከዚህም በላይ ነው እየተባለ ነው።

https://p.dw.com/p/1Ghuv
Saudi-Arabien Hadsch Massenpanik in Mina
ምስል picture-alliance/AP Photo

[No title]


በአመታዊው የሐጅ ጉዞ በሚና በተፈጠረው ግፊያና መጨናነቅ ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ጨምሯል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ጽ/ቤት መስከረም 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ 13 መሞታቸውንና 26 መቁሰላቸውን አስታውቋል። መግለጫው ለአመታዊው የጸሎት ስነ-ስርዓት «አስር ሺህ ያህል » ኢትዮጵያውያን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማምራታቸውን ይገልጻል።
በሳዑዲ አረቢያ የሚገኘው ጋዜጠኛ ነቢዩ ሲራክ ግን የሟቾች ቁጥር ዘግይቶ የወጣው መግለጫ ከጠቀሰው በላይ መሆኑን ይናገራል።

ሳዑዲ አረቢያ በጸሎት ስርዓቱ ህይወታቸውን ያጡ ከ 1,000 በላይ ምዕምናንን ፎቶግራፎች በአገሯ ለሚገኙ የውጭ ዲፕሎማቶች ሰጥታለች። የሟቾች ቁጥርና ማንነት በፍጥነት አለመታወቅና የአደጋው ምክንያት ሳዑዲ አረቢያን እያስተቻት ነው።
ጉዳዩን በፍጥነት እንዲጣራ ያዘዙት የሳዑዲ ባለስልጣናትም የሟቾችን ማንነት የደም ናሙናዎች ለመለየት ማቀዳቸውን ነብዩ ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።
የሟቾቹ ቁጥር እስካሁን በውል ባይታወቅም በየእለቱ ግን ጭማሪ በማሳየት ላይ ይገኛል። ኢራን 464 ዜጎቿ በሚና ሰይጣንን የመውገር ተምሳሌታዊ ስርዓት ላይ በተፈጠረው ግርግር ህይወታቸውን ማጣታቸውን አስታውቃለች። ኢንዶኔዥያ 91 ዜጎቿ ህይወታቸውን ማጣታቸውንና 38 እስካሁን ያሉበት አለመታወቁን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። ፓኪስታን 57 ዜጎቿ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ከ2 ሚሊዮን በላይ የእስልምና እምነት ተተከታዮች በተሳተፉበት አመታዊ የሐጅ ጸሎት በጥቂቱ 1,036 ምዕምናን ሳይሞቱ እንዳልቀረ አሶሼትድ ፕሬስ አስታውቋል። ሳዑዲ አረቢያ የሟቾቹ ቁጥር 769 ብቻ ነው ማለቷ አይዘነጋም።

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ