1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመርሳ ተቃውሞ 10 ሰዎች መሞታቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ቅዳሜ፣ ጥር 19 2010

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በመርሳ ከተማ ዛሬ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የሀብሩ ወረዳ ፍርድ ቤት ኃላፊን ጨምሮ 10 ሰዎች መሞታቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ፡፡ መሥሪያ ቤቶች እና ቤቶች መቃጠላቸውን፣ በፖሊስ ጣቢያ የነበሩ እስረኞችም «ማምለጣቸውን» ገልጸዋል፡፡  

https://p.dw.com/p/2rcw7
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

የከተማይቱ ነዋሪዎች እንደገለጹት በመርሳ ከተማ ተቃውሞ እና የተኩስ ድምጽ መሰማት የጀመረው ዛሬ ቅዳሜ ከጠዋት ጀምሮ ነው፡፡ በወልድያ እና ቆቦ በነበረው ግጭት የደረሰውን ጉዳት ተቃውመው አደባባይ ከወጡ የከተማይቱ ነዋሪዎች መካከል ሦስቱ የተገደሉት በሀብሩ ወረዳ ፍርድ ቤት ኃላፊ መሆኑን ስማቸው እንዳይጠቀስ የሚፈልጉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል፡፡ ሌሎች ሦስት ሰዎችን ያቆሰሉት የፍርድ ቤቱ ኃላፊ በነዋሪዎች መገደላቸውን እና እርሳቸው በውስጥ እንዳሉ ቤታቸው በእሳት መጋየቱን እኚሁ ነዋሪ አስረድተዋል፡፡ ይህን መረጃ ሌላ የከተማይቱ ነዋሪም አረጋግጠዋል፡፡ 

በዛሬው ተቃውሞ ከሞቱት ሌላ በርካቶች መቁሰላቸውን ከስፍራው የወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ አንደኛው ነዋሪ ቁስለኞች ወደ መርሳ ጤና ጣቢያ ሲገቡ መመልከታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ “ወደ 5 ሰዎች ቆስለዋል” የሚሉት ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ ቁስለኞች በሶስት አምቡላንስ ተጭነው ወደ ደሴ አቅጣጫ ሲሄዱ ማየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከመርሳ ወደ ወልድያ ያለው መንገድ መዘጋቱን የሚናገሩት እኚሁ ነዋሪ ከከተማይቱ ወደ ደሴ በሚወስደው መንገድ እስከ መሃል አምባ እና አብዮት ፍሬ ድረስ “መስመር ዝግ ነው” ብለዋል፡፡ “አምቡላንሶቹ የጫኑት የተመቱ ወጣቶችን ስለሆነ እንዲያልፉ ተደርጓል” ሲሉ አክለዋል፡፡    

በመርሳ ዘወትር ቅዳሜ የሚቆመው ገበያ በተቃውሞው ምክንያት መበተኑን፣ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች መዘጋታቸውን እና የትራንስፖርት አገልግሎት መቆሙን ገልጸዋል፡፡ የከተማይቱ ዋና ገበያ ካለበት አዲስ ከተማ አካባቢ የተነሳው ተቃውሞ ወደ 01 ቀበሌ፣ ወረ ላሎ እና መርሳ ሸል ወደሚባሉ የከተማይቱ ክፍሎች መዛመቱን አመልክተዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ የሀብሩ ወረዳ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ ጣቢያ እና «የስርዓቱ ደጋፊዎች ናቸው» ያሏቸውን ሰዎች መኖሪያ ቤቶች ማቃጠላቸውን ነዋሪዎች እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የከተማይቱን ማዘጋጃ ቤት መስታወቶች መሰባበራቸውን እና በህንጻው ላይም ጉዳት ማድረሳቸውን አብራርተዋል፡፡ 

“ሁለት ፖሊስ ጣቢያዎች አሉ የከተማ እና የገጠር የሚባሉ፡፡ ሁለቱም ያሉት ቀበሌ 01 ነው፡፡ እነዚያ ተቃጥለዋል፤ እስረኞች አምልጠዋል” ሲሉ አንደኛው ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ፖሊስ ጣቢያው መቃጠሉን የተናገሩት ሌላኛው ነዋሪ በበኩላቸው ስለእስረኞቹ ሁኔታ የተረጋገጠ መረጃ የለኝም ብለዋል፡፡     

በመርሳ እስከ ቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በከተማይቱ የጥይት ተኩስ ይሰማ እንደነበር የተናገሩት ነዋሪዎች በከተማይቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና የክልሉ አድማ በታኝ ፖሊሶች እንደሚታዩ ጠቁመዋል፡፡ የጸጥታ ኃይሎቹ አባይ ተራራ እና ቀበሌ 02 ኮሌጅ አካባቢ በብዛት እንደሚታዩ ተናግረዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ፖሊሶች በከተማይቱ ያለ ባንክ ቤት ጉዳት እንዳይደርስበት ጥበቃ ሲያደርጉ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡ አንደኛው ነዋሪ “ፖሊሶች እስካሁን ምንም ያደረጉት ነገር የለም፡፡ ባንክ ቤት ብቻ እንዳትነኩ ብለው ሌላውን እንደፈለጋችሁ ብለዋል፡፡ አጋዚዎች ገብተዋል፤ ፌደራሎች ናቸው የተኮሱት” ብለዋል፡፡ የአማራ ብሔራዊ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ በአካል እና ንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል ማለታቸውን የጽ/ቤታቸው የፌስቡክ ገጽ ጠቅሷል።    

ተስፋለም ወልደየስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ