1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ የግብር መክፈያ ቀን ለማራዘም ታስቧል

ሰኞ፣ ሐምሌ 17 2009

የንግድ ተቋማት የቀን ገቢ ግምት ይፋ መደረጉን ተከትሎ የአገልግሎት መስጠት ማቆም አድማ በተለያዩ አካባቢዎች ተደርጓል፡፡ አድማው ወደ አዲስ አበባ ተዛምቶ ዛሬ በመርካቶ የሚገኙ ሱቆች በከፊል ተዘግተው ውለዋል፡፡ ተቃውሞው ያሳሰባቸው የሚመስሉት የፌደራልና የክልል ኃላፊዎች መፍትሄ ነው ያሏቸውን እርምጃዎች ለመውሰድ ጉዳዩን እያጠናን ነው ይላሉ፡፡

https://p.dw.com/p/2h4op
Äthiopien VW Käfer Straße
ምስል Imago/imagebroker

Confusion & protest on Tax in Ethiopia - MP3-Stereo

ሐምሌ ሁሌም ቢሆን ከግብር ጋር የተያያዙ ብሶቶች እና ቅሬታዎች ጎላ ብለው የሚደመጡበት ወር ነው፡፡ በነጋዴዎች እና የንግድ ተቋማት ባለቤቶች የሚታየው የእዚህ ዓመቱ ቅሬታ ግን ባስ፣ መረር፣ ጠንከር ብሎ እስከ ተቃውሞ እና አድማ ድረስ ደርሷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙት አምቦ እና ጊንጪ ከሳምንት በፊት የተጀመረው የአገልግሎት መስጠት ማቆም አድማ ገፍቶ አዲስ አበባ ደርሷል፡፡ ሊያውም የሀገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ እምብርት ናት በምትባለው መርካቶ፡፡ 

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን አንድ በመርካቶ ያሉ ነጋዴ ዛሬ በመርካቶ ያለውን ድባብ እንዲህ ገልጸውታል፡፡ 

“መርካቶ ከፊል ነው፡፡ አንዳንድ ቦታዎች እንደ ሸማ ተራ አካባቢ፣ ሰላም ባስ አካባቢ እንዳለ ተነጋግረው ዘግተዋል፡፡ [የግብር ውሳኔ] የተነገራቸው ሰዎች አሉ፡፡ እነርሱ ናቸው የዘጉት፡፡ የግብር ውሳኔውን እየከፋፈሉ ነው ለሰው የነገሩት፡፡ አንዳንዶቹም ሲሄዱ ነው ያወቁት፡፡ እና [ውሳኔው] የተነገራቸው በአንድ አካባቢ ያሉ ተነጋግረው ነው እንደዚያ ያደረጉት፡፡ እስካሁን ድረስ አብዛኛው የመርካቶ ነጋዴ ውሳኔው አልተነገረውም፡፡ ያወቁት ግን አጠቃላይ ማለት ይቻላል ተነጋግረው አድማ ላይ ናቸው” ይላሉ ነጋዴው፡፡  

ሱቃቸውን የዘጉት ነጋዴዎች መደብሮቻቸው “በቀበሌ ባለስልጣናት ይታሸጉብናል” በሚል ፍራቻ ከቦታው ሳይርቁ ሁኔታውን ሲከታተሉ እንደዋሉ የመርካቶው ነጋዴ ለዶይቼ ቬሌ አስረድተዋል፡፡ ነጋዴዎቹ ተቃውሟቸውን በአድማ ጭምር እየገለጹበት የሚገኘው አማካይ የቀን ገቢ ግምት የተሰራው በገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን ገማቾች ነው፡፡ 

ከመስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው  በአዲስ አበባ ለዚህ ዓመት የግብር ክፍያ መረጃ የተሰበሰበው በ148‚728 ግብር ከፋዮች ላይ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 32 በመቶ ያህሉ ቅሬታ ማስገባታቸውን በባለስልጣኑ የአዲስ አበባ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ አታክልቲ ገብረእግዚያብሔር ለዶይቼ ቬሌ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ገልጸው ነበር፡፡

Äthiopien Geschäfte streiken wegen Steuergesetz in Oromiya (Ambo)
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

“ከዚህ 32 በመቶ ደግሞ 38.6 በመቶ ፈትተናል፡፡ ስለዚህ ይህን ስንፈታ ምንድነው? የተሰበሰበው መረጃ ትክክል ከሆነ ትክክል ነው፡፡ ትክክል ካልሆነ ደግሞ ያው በዚህ ልክ ነው መሆን ያለበት [በሚል] ያስተካክለዋል” ብለዋል አቶ አታክልቲ፡፡  

እንደ አቶ አታክልቲ ገለጻ ቅሬታዎችን የሚመለከተው ቡድን ግምቱን ከሰራው አካል የተለየ ነው፡፡ በቀን ገቢ ግምት ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎቹን እየተመለከቱ የሚገኙትም ከመደበኛ የቅሬታ ስርዓት ውጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አቶ አታክልቲ ቅሬታዎችን ለማስተናገድ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ቢናገሩም በአነስተኛ ንግድ ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች ዘንድ ያለው ሮሮ አልተቋረጠም፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ በአዲስ አበባ ታትሞ ለንባብ የበቃው “ሪፖርተር” ጋዜጣ የእነዚህ ነጋዴዎች ቅሬታ ተከትሎ መንግስት “ራሳቸው ያመኑበትን እንዲከፍሉ” ውሳኔ ላይ መድረሱን ዘግቦ ነበር፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የትምህርትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ይህንን አስተባብለዋል፡፡ 

“እንደዚህ የሚባል ነገር የለም፡፡ የነበረው የተወሰነው ውሳኔ ለህዝቡም፣ ለግብር ከፋዩም ተገልጾለታል፡፡ ግብር ከፋዩም ቅሬታ አለኝ የሚለውን በህጋዊ ስርዓቱ አቅርቦ እያታየ ነው እንጂ ሌላ የተወሰነ ነገር የለም” ይላሉ አቶ ኤፍሬም፡፡ 

በባለስልጣኑ በኃላፊነት ደረጃ የሚሰሩ ሌላ ባልደረባ ደግሞ ጉዳዩ ገና በውይይት ላይ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት በበርካታ ከተሞቹ የቀን ገቢ ግምቱን ተቃውሞ ሲያስተናግድ የቆየው የኦሮሚያ ክልል በበኩሉ የንግድ ማንቀሳቀሻ ገንዘባቸው ከ500 ሺህ ብር በታች ለሆኑ በ“ደረጃ ሐ” ለተመዘገቡ ግብር ከፋዮች የግብር መክፈያ ጊዜን ለማራዘም አቅዷል፡፡

በኦሮሚያ የገቢዎች ባለስልጣን የግብር ከፋዮች ትምህርት ክፍል እና ኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ታሪኬ ሱጴ “የ‘ሐ’ ደረጃ ያሉት ግብር ከፋዮች [ቀነ ገደብ] ሐምሌ 30 ነው የሚያልቀው፡፡ አሁን ያለው ቅሬታ [ማቅረቢያ] ጊዜ ስለፈጀ ቅሬታው ታይቶ እስከሚጣራ እና በስተኋላ ላይ ወደ ቅጣት እንዳይገቡ እስከ [ነሐሴ 15] እንዲራዘም በምክክር ላይ ነው ያለነው፡፡ ወደዚያ መሄዳችን የማይቀር ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡  

በኦሮሚያ 390 ሺህ አጠቃላይ ግብር ከፋዮች አሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የቀን ገቢግምት የሚመለከታቸው 319 ሺህ ገደማ ሲሆኑ ከመካከላቸው 19 በመቶ ያህሉ በአገማመቱ ላይ ቅሬታ ማቅረባቸውን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ