1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፍርድ ቤት ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቅዷል

ሐሙስ፣ ሐምሌ 20 2009

የኢትዮጵያ መንግስት በሙስና ጠርጥሬያቸዋለሁ በሚል መታሰራቸውን ከትላንት በስቲያ ይፋ ያደረጋቸው የመንግስት ኃላፊዎች እና ባለሀብቶች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ የመንግስት ኃላፊዎቹ በፌደራል እና አዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ በገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር እንደዚሁም በስኳር ኮርፖሬሽን የሰሩ እና በመስራት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

https://p.dw.com/p/2hGov
Äthiopien Journalisten Martin Schibbye und Johan Persson
ምስል AP

ፍርድ ቤት ለፖሊስ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቅዷል

ዛሬ ፍርድ ቤት ከቀረቡት ውስጥ የቀድሞው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ ይገኙበታል፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት እና ካለፈው ሐምሌ ወር አንስቶ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን እየሰሩ የነበሩት አቶ በቀለ ንጉሴም ከተጠርጣሪዎቹ  አንዱ ናቸው፡፡

ከተጠርጣሪ ባለሀብቶች ውስጥ ሁለቱ የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው፡፡ አንደኛው ከኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 የስኳር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ የታሰሩት የቻይናው የጄጄአይሲ ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ ጂ ዮኦን ሲሆኑ ሌላኛው ደግሞ ቀደም ሲል በሙስና ተጠርጥረው በማረሚያ ቤት የሚገኙት እስራኤላዊው የትድሃር ኮንስትራክሽን ባለቤት እና ስራ አስኪያጅ ሚናሽ ሌቪ ናቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ዛሬ ፍርድ ቤት መቅረባቸውን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈንታው አምባው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ 

“ሰላሳ ሰባት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች በዛሬው ዕለት በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቶ ለነሐሴ 3‚ 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተይዟል” ብለዋል፡፡ 

ለገዢው ፓርቲ ቅርበት ያለው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደዘገበው ፖሊስ ሰላሳ ሰባቱም ተጠርጣሪዎች ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት የፕሮጀክት ስራ የወጣን ከ1.15 ቢሊዮን ብር በላይ አጉድለዋል ሲል ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና ጥያቄ ይፈቀድላቸው ዘንድ ችሎቱን ቢጠይቁም ፖሊስ የተለያዩ ሰነዶችን ሊያሸሹ ይችላሉ በሚል ጥያቄያቸውን መቃወሙን ዘገባው አትቷል፡፡ ፖሊስ ምርመራ ለማካሄድ ተጨማሪ 14 ቀን ይሰጠኝ ማለቱን የጠቀሰው ፋና ፍርድ ቤቱም ጥያቄውን መቀበሉን ዘግቧል፡፡ 

በከፍተኛው ፍርድ ቤት ቅጽር ግቢ የነበረ ጋዜጠኛ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የነበረውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ለዶይቸ ቬለ አስረድቷል፡፡ 

“በዝግ ችሎት ነበር የተደረገው፡፡ የተወሰኑ ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ ቤተሰብ ውጭ ሆኖ እንዲጠብቅ ነበር የተደረገው፡፡ ሲወጡ በጣም ስሜታዊ ነበሩ፡፡ የሚያለቅሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ የተከሰሱት ሰዎች ለማበረታት ሲሞክሩ ነበር፡፡ በጣም ጥብቅ የጸጥታ ቁጥጥር ነበር፡፡ ስልክ እንዳትቀርጹ እያሉ ሰዎችን ሲነግሩ ነበር” ሲል ጋዜጠኛው እማኝነቱን ሰጥቷል፡፡ እንደጋዜጠኛው አባባል ከተከሰሱት 37 ግለሰቦች መካከል ሶስቱ ዛሬ ፍርድ ቤት አልቀረቡም፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ