1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምሥራቅ ዩክሬን ውዝግቡ ተባብሷል

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 8 2006

ምሥራቅ ዩክሬን ውስጥ መፍቅሬ ሩስያ ሚሊሽያዎች ዛሬ ስድስት ብረት ለበስ ወታደራዊ መኪናዎችን መያዛቸውን ዩክሬን አስታወቀች ። የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር መኪናዎቹ እንዳይንቀሳቀሱ መጀመሪያ በአካባቢው ነዋሪዎች ከታገዱ በኋላ አክራሪ ኃይሎች እንደወሰዱዋቸው ዛሬ ተናግሯል።

https://p.dw.com/p/1BjlS
Ostukraine Krise Slawjansk 16.04.2014
ምስል picture-alliance/dpa

ወታደራዊ መኪናዎቹ ካራማቶርስክ በተባለው ከተማ የተቀሰቀሰውን የመገንጠል እንቅስቃሴ ለማስቆም ነበር የተሰማሩት ። አሶስየትድ ፕሬስ እንደዘገበው ደግሞ ፊታቸውን የሸፈኑ ወታደሮችን የጫኑ 6 ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ስሎቭያንስክ የተባለችው ከተማ ገብተዋል ። ከተማይቱ በዩክሬን ጊዜያዊ መንግስት ላይ ያመፁ ወገኖች የሚገኙባት ከተማ ናት ። አሶስየትድ ፕሬስ የጠቀሰው አንድ ሰው ወታደሮቹ ዩክሬንን ከድተው ከመፍቅሬ ሩስያዎቹ ጋር የተቀላቀሉ ወታደሮች ሳይሆኑ አልቀረም ብሏል ። ሰርጎ ገቦች የከተማይቱን የፖሊስ ጣቢያ ፅህፈት ቤትና የአስተዳደር ህንፃዎችን በመያዝ ምሥራቅ ዩክሬን ሰፋ ያለ የራስ ገዝ አስተዳደር እንዲሰጣትና ከሩስያም ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲመሰረት ጠይቀዋል ። ቢያንስ ስምንት በሚሆኑ የምሥራቅ ዩክሬን ከተሞች ተመሳሳይ እርምጃዎች ተወስደዋል ። የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር አርሴኒ ያትሴንዩክ ሩስያን አመጹን በማቀነባበር ወንጅለዋል ። ያትሴኒክ ሩስያ ከነዳጅ ዘይትና ከጋዝ በተጨማሪ አሁን ወደ ሽብርም እየላከች ነው ሲሉ ከሰዋል ። በዩክሬን የተባባሰው ቀውስ መንግሥት የበኩሉን እርምጃ እንዲወስድ የሚያደርግ ነው ስትል ዩናይትድ ስቴትስ አስታውቃለች የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጄይ ካርኒ

Ostukraine Krise pro-russische Kräfte bei Kramatorsk 16.04.2014
ምስል Reuters

«የዩክሬን መንግሥት ህግና ሥርዓት የማስከበር ሃላፊነት አለበት ። በምሥራቅ ዩክሬን የሚካሄዱት ትንኮሳዎች መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ የሚያደርጉ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ እያደረጉ ነው ።»

የተመድ ዋና ፀሃፊ ባን ኪሙን በጉዳዩ ላይ ከሩስያው ፕሬዝዳንት ባን ኪሙን በበኩላቸው ተጨማሪ ግጭቶች እንዳይከሰቱ በቃል አቀባያቸው ስቴፋን ዱጃሪክ በኩል ጥሪ አስተላልፈዋል ።

« ዋና ፀሃፊው በምሥራቅ ዩክሬን የሚካሄደው ብጥብጥ በጣም አሳስቧቸዋል ። ሁሉም ወገኖች ሁኔታው እንዳይባባስ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት እንዲያደርጉ እና ተጨማሪ ግጭቶችን እንዲከላከሉ ጥሬ አቅርበዋል ።»

Ostukraine Krise Kramatorsk 16.04.2014
ምስል Reuters

በምሥራቅ ዩክሬን ግዛቶች የሩሲያ ወገንተኛ የሆኑት ታጣቂዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ መጠናከሩ እየተነገረ ነዉ። የሩሲያን ሰንደቅ ዓላማ የሚያዉለበልቡ መሳሪያ የተጠመደባቸዉ ተሽከርካሪዎች ዉጥረት በተባባሰባቸዉ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ መታየታቸዉ ተዘግቧል። የዩክሬን መንግስት ትናንት በአካባቢዉ ፀረ ሽብር ዘመቻ መጀመሩን በማመልከት ወታደሮችና ታንኮችን ወደስፍራዉ ልኳል። ዛሬ የወጡ ዘገባዎች ደግሞ ስድስት መሳሪያ የተጠመደባቸዉን የዩክሬን ተሽከርካሪዎች በእነዚህ ኃይሎች መያዛቸዉን ያመለክታሉ። ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬን በእርስ በርስ ጦርነት ልትታመስ ዳርዳር እያለች ነዉ የሚል ስጋቷን ታሰማለች። የዩክሬንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በርሊን የሚገኘዉ ዘጋቢችን ይልማ ኃይለ ሚካኤልን በስልክ አንዳንድ ነጥቦችን በማንሳት አነጋግሬዋለሁ።

ይልማ ኃይለሚካኤል

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ