1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሥነ-ቅመማ የዘንድሮው የኖቤል ተሸላሚው፤

ረቡዕ፣ ጥቅምት 1 2004

አምና መጋቢት 2 ቀን 2003 (11,03 2011)፤ ከ 7 ወራት ገደማ በፊት፤ ሰሜን ምዕራብ ጃፓንን እጅግ ኃይለኛ የውቅያኖስ ማዕበል(ሱናሚ)ካጥለቀለቀና 20,000 ህዝብ ደብዛው እንዲጠፋ ካደረገ ወዲህ፤ Cosmo Power የተባለው የጃፓን ፋብሪካ ፕሬዚዳት ሾጂ ታናካ ፤

https://p.dw.com/p/RqaT
ምስል Department of Materials Engineering/Haifa

ያ ዓይነቱ የጥፋት ውሃ ተመልሶ ቢመጣ ህይወትን ማትረፍ የሚቻልበት ብልሃት መገኘቱን አብሥረዋል። ታናካ ፤ ቢጫ ባህር ሰርጓጅ ጀልባ ወይም መርከብ ሳይሆን የሠሩት፤ ኳስ-መሰል ፣ ድቡልቡል ተንሣፋፊ መሣሪያ ነው። አንድ ጠባብ በርና አንድ የመስታውት መስኮት ፤ለንፁህ አየር ማግኛና ውሃ ለማንጠፍጠፊያ 2 ልዩ ቀዳዳዎች አሉት ። ወርዱ ፣ 1,2 ሜትር ሲሆን ፤ ለ 4 ሰዎች መቀመጫ ያለው ፤ ለክፉ ቀን ተብሎ በማንኛውም የጃፓናውያን አማካይ ቤት ውስጥ ማስቀመጫ ቦታ የማይታጣለት ህይወት- አድን መሣሪያ ነው። ይኸው በጣም ቀላል፣ ሆኖም ከብረት የጠነከረ ተናሳፋፊ ፣ ድቡልቡል ነፍስ አድን መሣሪያ ፣ ውህ ወደ ውስጡ በፍጹም የማያስገባ ሲሆን ፤ ማንኛውም የሚንሳፈፍ ነገር አደጋ እንዳያደርስበትም ይከላከላል። መሣሪያው ደመቅ ያለ ቢጫ ቀለም የሚቀባው ፣ Shoji Tanaka እንደሚሉት፣ ሁኔታዎች ሲረግቡ፣ የህይወት አድን ሠራተኞች በቀላሉ ከሩቅ እንዲያዩት ታስቦ ነው። ነፍስ አድኑ ድቡልቡል መሣሪያ፤ ቤት ውስጥ ሲቀመጥ፤ ልጆች የድብብቆሽ ጨዋታ አመቺ ስለሆነ ይወዱታል። ሾጂ ታናካ እንደገለጹት እስካሁን 700 ሰዎች እንዲሸጥላቸው ያዘዙ ሲሆን ፣ ዋጋው፤288,000 የን ማለትም 3,800 ዶላር ነው። ይህ፣ «ኖኅ» የሚል ስያሜ ለተሰጠው ለመደበኛው ዘመናዊ የኖኅ መርከብ እንበለው የሚከፈል ዋጋ ነው። በውስጡ ተጨማሪ ልዩ መንተራሻዎችና ንዝረት መከላከያ ያለው ደግሞ 4,500 ዶላር ያዋጣል።

ኖኅ የተባለው መሣሪያ፤ እንደተገለጸው፤ ለሱናሚ ብቻ ሳይሆን ከምድር ነውጥ አደጋም ራስን ለመከላከል ይጠቅማል።

ከየብስና ውቅያኖስ ለሚያጋጥም አደጋ እንዲህ ዓይነት ህይወት ማትረፊያ መሣሪያ መሠራቱን ነበረ አሁን ያዳመጥን ከኅዋ በኩልስ ቢመጣ ምን ይደረጋል? ባለፈው ቅዳሜ ሌሊት ለእሁድ አጥቢያ፤ በሰሜኑ ንፍቀ ክበብና በሌላውም የዓለም ክፍል በውድቅት ሌሊት ፤የተወርዋሪ ከዋክብት ፍምና ዓመድ መርከፍከፉ ተነግሯል። ይህን በሚገባ መመልከት የተቻለው ደመና ባልሸፈነው ሰማይ ላይ ነው። በጀርመን ሀገር ፤ የአየር ጠባይ ምርምር መ/ቤት ቀደም አድርጎ እንዳስታወቀው፤ የተወርዋሪ ከዋክብትና ፍምና ዓመድ ማየት የተቻለው ባለፈው ቅዳሜ ፤ ከእኩለ ሌሊት ሁለት ሰዓት ያህል ቀደም ብሎ ነበር።

ከተፈረካከሱ ተወርዋሪ ከዋክብት የሚወድቀው ጠጠር ሆነ ዓመድ ምድር ላይ ወርዶ አደጋ የሚያደርስ አልነበረም፤ የሚያደርስም አይደለም። የኅዋ ምርምር የሚያከናውኑ መንግሥታት፣ ግን ፣ የምርምር ሳቴላይቶቻቸው እንዳይጎዱባቸው በእጅጉ ይሠጋሉ። ከዚያ የከፋ አደጋ ያጋጥማል ብለው ግን አያስቡም።

አብዛኞቹ፣ ተወርዋሪ ከዋክብት ምንጫቸው፤ የስብርባሪ ከዋክብትመቀነት በሚሰኘው፤ በማርስና በጁፒተር መካከል በሚገኘው የኅዋ ክፍል ነው።

በምድር ከባቢ አየር ላይ ግሞ፣ ተቃጥሎ ፤ቀሪው ዓመድ፣ ካፊያም ሆነ ዝናም መስሎ ወደ ምድር ይወርዳል። በፀሐይ ዙሪያ የሚሽከረከሩ፤ ፕላኔቶች ብቻ አይደሉም። ሥፍር ቁጥር የሌለው አሸዋ፣ ዓመድና ትልልቅ ድንጋይም ሆነ ጠጠር ፤ በፕላኔቶቹ ዙሪያና በምኅዋራቸው ይበናል። ይህ ሲሆንም ነው፣ መሬት ላይ እስከመውደቅ የሚደርሰው። ከሰሞኑ፤ በሰዓት ቁጥራቸው እስከ 600 ገደማ የሚደርሱ ተወርዋሪ ከዋክብት፣ ከባቢ አየራችንን ሰንጥቀው ሲከንፉ ማየት መቻሉን የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል።

የጀርመን የአየርና የኅዋ ጉዞ ጉዳይ ማዕከል(DLR) ባልደረባ ዊልፍሪድ ቶስት እንዳሉት፤ የስባሪ ከዋክብት አካል በምድራችን ከባቢ አየር፤ የዓመድ አቶሞች ካሉት አየር ጋር ከ 3000 ዲግሪ ሴልሴስ በላይ በመጋል ያበራል። ከምድራችን 80 እስከ 100 ኪሎሜትር ርቀት፣ ኅዋ ላይ ፣ ተወርዋሪ ከዋክብቱ ከአንድ ሴኮንድ በኋላ ፍም ነው የሚመስሉት ። አናዳንዶቹ፤ 2 ሴኮንድ በሚወስድ ቅጽበት ይበልጥ ያበራሉ። የእሳት ኳስ ነው የሚመስሉት።

አብዛኞቹ ተወርዋሪ ከዋክብት፤ ድናጋያማ አካላቸው ሙሉ በሙሉ ካልጋለና ካልተቃጠለ፤ በተለይ ትልቅ ከሆነ አደገኛነቱ የሚያጠያይቅ አይሆንም። እርግጥ ነው በኅዋ፤ ከአንድ መቶ ሜትር እስከ አንድ ኪሎ ሜትር ወርድ ያላቸው ግዙፍ ስባሪ ከዋክብት መኖራቸው የታወቀ ነው። ግን እንደዚህ ዓይነቶቹ ትልልቆቹ ስባሪ ከዋክብት ፣በምድራችን ታሪክ ከስንት አንድ ጊዜ ነው እስከመላተም የደረሱት።

የተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ጉባዔ፣ በሰየመው የሥነ ቅመማ መታሰቢያ ዘመን ማለትም 2011 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት፤ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ዕለት በአጭሩ እንዳወሳነው፤ ዳን ሼኽትማን የተባሉት እሥራኤላዊ የብርቅ አንጸባራቂ ድንጋዮች «ሬር ክሪስታልስ» ተመራማሪ ፤ በሥነ-ቅመማ የዘንድሮው የኖበል ሽልማት አሸናፊ ሆነዋል። ተማራማሪው ይህን ምሥጢር በምርምር ከደረሱበት 30 ዓመት ይሁን እንጂ፣ ባልደረቦቻቸው ሳይቀሩ ሲያሾፉባቸው እንደነበረ ታውቋል። ሳይንስ ፣ ዕውቀት መቅሰምና ትምህርት ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን፤ ለማይታሰብ ግኝትም ግልጽነትን ይጠይቃል። ሼኽትማን ፤አቶሞች ተመሳሳይ ቅርጽ ባለበት ሁኔታ በተፈጥሮ የቁስ አካል ተደጋግመው ከሚገኙባቸው ባፈነገጠ ሁኔታ ፤ ብርቅ አንጸባራቂ ብርጭቆ መሰል ጠጣር ነገሮችን ማግኘት እንደሚቻል ያሥመሠከሩ ናቸው። ግኝታቸው መቼ ነበረ የተሣካው? ባልተቤታቸው፤ ወ/ሮ ዚፒ ሼኽትማን እንዲህ ያስታውሳሉ።

«አስገራሚውን አንጸባራቂ ጠጣር ቁስ አካል (ክሪስታል)ምሥጢር ያገኘው እ ጎ አ በ 1982 ነው። ማንም ሊያምነው አልፈለገም። ለብዙ ዓመታት ተቃውሞውንም ሽሙጡንም መቋቋም ነበረበት። በርሱ በጣም ነው የምኮራው።»

ዳን ሼኽትማን ይህን ያኔ የምርምራቸውን ውጤት ለማግኘት ቢበቁም፤ ምርምሩን አቋርጠው እንዲተዉ ተለምነውም ነበረ። ግን ከ 30 ዓመታት ወዲህ የእስዊድን የሳይንስ ኖበል ኮሚቴ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጥርጣሬውም፣ ሐሜቱም ሁሉ እንዲወገድ አብቅቷል። ዳን ሼኽትማን---

«ዛሬ፤ በሺ የሚቆጠሩ ሳይንቲስቶች፤ ያተኮርኩበትን የምርምር ዘርፍና ውጤቱን የራሳቸው አድርገው እንደሚቀበሉት እርግጠኛ ነኝ። ማድረግም ይችላሉ። ያለእነዚህ ሺ ሳይንቲስቶች ይህ ምርምር አሁን ከደረሰበት ደረጃ ላይ አይደርስም ነበር። »

የዳን ሼኽትማን አጠቃላይ ትኩረት አንጸባራቂ ጠጣር ቁስ አካላት ናቸው። የ 70 ዓመቱ አዛውንት ተመራማሪ ዩናይትድ እስቴትስም ውስጥ ይሠራሉ። የኖቤሉ ሽልማት ለትንሽዋ ሀገር እሥራኤል ዓለም አቀፍ እውቅናን የሚያስገኝ ሲሆን፤ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሺሞን ፔሬስ ፤ ተመራማሪውን ብቻ ሳይሆን የአገራቸውን ህዝብ በመላ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።

«እርስዎ፤ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሼኽትማን፤ ዛሬ ለአሥራኤል ትልቅ ሥጦታ አበርክተዋል። በሀገራችን 10ኛው የኖቤል ተሸላሚ ነዎት! በዓለማችን፤ እንዲህ በዛ ያለ ሽልማት የሚያገኙ አገሮች ብዙዎች አይደሉም። »

ዳን ሼኽትማን ሃይፋ ውስጥ በታዋቂው የሥነ-ቴክኒክ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ናቸው። ዩናይትድ እስቴትስም ውስጥ ያስተምራሉ። በሳይንሱ ዓለም ፤ የኖቤል ሽልማት ከማንኛውም ሽልማት ላቅ ያለ ትርጉም የሚሰጠው ነው።

ተክሌ የኋላ፣

ሸዋዬ ለገሰ