1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሩዋንዳ ዓማፂ መሪዎች ላይ ብይን

Eshete Bekeleማክሰኞ፣ መስከረም 18 2008

የጀርመን ፍርድ ቤት ሁለት የሩዋንዳ ሽምቅ ውጊያ መሪዎች በጎረቤት የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ውስጥ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል የእስር ብይን አስተላለፈ። ኢግናስ ሙርዋናሺያካና ምክትላቸው የነበሩት ስትራቶን ሙሶኒ ታጣቂዎቻቸው የጅምላ ግድያ እንዲፈጽሙና አስገድደው እንዲደፍሩ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል የሚል ክስ ነበር የቀረበባቸው።

https://p.dw.com/p/1GfdV
Ignace Murwanashyaka
ምስል picture-alliance/dpa

[No title]

በጀርመን የሽቱትጋርት ፍርድ ቤት የሩዋንዳ ዜግነት ባላቸው ሁለት የዓማፂ መሪዎች ላይ የእስራት ብይን አስተላልፏል። መቀመጫውን በኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ያደረገው የሩዋንዳ ዓማፂ ቡድን መሪዎች በደቡብ ምዕራብ ጀርመን በምትገኘው የማንሃይም ከተማ በመሆን ለታጣቂዎቻቸው ትዕዛዝ ያስተላልፉ ነበር ተብሏል።
በፍርድ ቤቱ የሩዋንዳ ነፃ አውጪ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች (Democratic Forces for the Liberation of Rwanda) መሪ ነበሩ የተባሉት ኢግናስ ሙርዋናሺያካ የአስራ ሦስት አመታት ምክትላቸው የነበሩት ስትራቶን ሙሶኒ ደግሞ የስምንት አመታት እስር ተበይኖባቸዋል። ስትራቶን ሙሶኒ ከብይኑ በፊት በማረሚያ ቤት ያሳለፉት ጊዜ ተቆጥሮ ወዲያው ተለቀዋል።
የሩዋንዳ ፍትኅ ሚኒስትርና ዋና አቃቤ ሕግ ቡሴንግ ጆንስተን በጅምላ ጭፍጨፋ ቆፈን ውስጥ ላለችው አገራቸው ትክክለኛ ውሳኔ ብለውታል። ሆኖም የዓማፂ ቡድኑ መሪዎች በአገራቸው ቢዳኙ ይመርጡ እንደነበር አቃቤ ሕጉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
«ብይኑ የሩዋንዳ ነፃ አውጪ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች የጥቃት ስለባ ለሆኑ የተወሰነ በመሆኑ አንድ የሚያረካ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ሩዋንዳ ዲ.ኤፍ.ኤል.አር. ከሚያቀነቅነው የጅምላ ጭፍጨፋ አስተሳሰብ ጋር ትግል ውስጥ ያለች አገር ነች። እዚህ በ1994 የተፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ ከሚያቅዱና ለማጠናቀቅ ከሚደረግ ሙከራ ጋር የሚደረግ ትግል ነው። ሰፋ አድርገን ስንመለከተው የጅምላ ጭፍጨፋና አስተሳሰቡን ለመዋጋት ትክክለኛ መንገድ ነው።»
ሁለቱ የዓማፂ መሪዎች ከ20 አመታት በላይ በኖሩባት ጀርመን በሳተላይት ስልክ፤ አጭር የስልክ መልእክትና ኢ-ሜይል በመጠቀም ታጣቂዎቻቸው ጥቃት እንዲፈጽሙ ትዕዛዝ ያስተላልፉ እንደነበር በጀርመኗ ሽቱትጋርት ከተማ ባስቻለው ፍርድ ቤት ተገልጧል።
የሩዋንዳ ነፃ አውጪ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች የተመሰረተው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ሥልጣን ከያዙ በኋላ በጎርጎሮሳዊው 1994 ዓ.ም. ነው። ሩዋንዳ ታጣቂ ኃይሉን ለመውጋት ወታደሮቿን ወደ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ልካለች። በኮንጎ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተልዕኮም በያዝንው የጎርጎሮሳዊው ዓመት አማጺውን ለመውጋት እቅድ ነበረው።
ከ1,500 እስከ 2,000 የሚደርሱ የሁቱ ታጣቂዎች ያሉት የሩዋንዳ ነፃ አውጪ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች በምሥራቃዊ ሩዋንዳ ዘረፋ፤ አስገድዶ መድፈርን የመሳሰሉ አሰቃቂ ወንጀሎች ፈጽሟል ተብሏል። ህጻናትን አስገድዶ ለውትድርና ሲመለምል ወርቅና የከበሩ ማዕድናትን በሕገ-ወጥ መንገድ ሲነግድ ነበርም ተብሏል።
የሽቱትጋርቱን ፍርድ ቤት ውሳኔን ይበል ያሉት የፍትኅ ሚኒትር ግን አሁንም በምሥራቃዊ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሸምቋል በሚባለው የታጣቂ ቡድን ላይ ስላለው ተጽዕኖ እርግጠኛ አይደሉም።
«ዓለም ተባብሮ የሩዋንዳ ነፃ አውጪ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎችን ቅሪት ከምሥራቃዊ ኮንጎ ማጥፋት ይኖርበታል። በ1994 የፈጸሙትን የጅምላ ጭፍጨፋ ለማጠናቀቅ የሚያቅዱበት፤ ሴቶችን የሚደፍሩበትና በዜጎች ላይ በደል የሚፈጽሙበት ቦታ ነው። ይህ ለእኔ በታጣቂ ቡድኑ ላይ የተወሰነ ጥሩ ርምጃ ነው። ይሁንና ታጣቂ ቡድኑን ሙሉ በሙሉ ስለማጥፋቱ እርግጠኛ አይደለሁም። »
የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ላፎርጅ ፊልስ ባዜዬ የሁለቱን መሪዎች ችሎት ፖለቲካዊ ብለውታል። ተከሳሾቹም ቢሆኑ አራት አመታት በፈጀው ችሎት ጥፋተኛ አይደለንም በማለት የቀረበባቸውን ክደው ተከራክረዋል።
ከሳሽ አቃቤ ሕግ ባቀረበው የክስ ዶሴ ከ200 በላይ ግድያዎች፤ በርካታ የአስገድዶ መድፈር ፤ ሰዎችን እንደ መጠጊያ በመጠቀም ለጥቃት የማጋለጥ ወንጀሎች ተዘርዝረዋል ተብሏል።
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሰ

FDLR Kämpfer
ምስል DW/S. Schlindwein
Deutschland Prozess gegen mutmaßliche Kriegsverbrecher der ruandischen Rebellenorganisation FDLR
ምስል picture-alliance/dpa/D. Calagan