በራድዮ ኃይል አማኙ | ይዘት | DW | 28.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ይዘት

በራድዮ ኃይል አማኙ

በተከታታይ አጫጭር ቪዲዮዎች ከጋዜጠኞቻችን መካከል የተወሰኑትን እናስተዋውቃችኋለን፡፡ ሙያቸውን እንዴት እና ለምን እንደመረጡት፤ እንዴትስ እንደሚሰሩት ያጫውቱችኋል፡፡ #whereicomefrom

ነጋሽ መሐመድ የዶይቼ ቬለ የአማርኛ ክፍልን የተቀላቀለው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1999 ነው፡፡ ከዚያ በፊት፤ ሶስት ዓመት አስቀድሞ ለስልጠና ወደ ዶይቼ ቬለ በመምጣት ቆይታ አድርጎ ተመልሷል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንን ኃይል ከለጋነቱ ጀምሮ የተረዳው ነጋሽ ፤ መገናኛ ዘዴዎች ህዝብን ለማገናኘት እና ህይወታቸውን ለማሻሻል ያላቸውን ተጽዕኖም ተገንዝቧል፡፡ በተለይ የራድዮ ሚና ከፍተኛ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ነጻ እና ተአማኒ መረጃን ለሀገሩ ህዝብ የሚያሰራጨው ነጋሽ፤ ዶይቼ ቬለ የዲሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት እና የሲቪል ማብረሰብ እሴቶችን ያስተጋባል ባይ ነዉ፡፡ በዶይቼ ቬለ የአማርኛ ክፍል ለአድማጮቹ ይበልጥ ይበጃል ብሎ የሚያምነውን ዜና በየዕለቱ ሲመርጥ ሁሌም እነዚህን እሴቶች መሰረት በማድረግ ነው፡፡

ከሀገር ቤት በሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቀት

ኬንያዊቱ ኤዲትዝ ኪሚኒ በርሊን በሚገኘው የዶይቼ ቬለ ቴሌቭዥን ጣቢያ በዜና አቅራቢነት ለመሥራት  በጎርጎርያኑ 2017 መጀመሪያ ሐገሯን ለቅቃ ጀርመን ገባች፡፡ በሀገሯ ትልቁ የዜና ማሰራጫ በሆነው KTN ዋና ዜና አቅራቢ የነበረችው ኤዲትዝ በርካታ አድናቂዎች ነበሯት፡፡ እነርሱን ትታ ወደ በርሊን ብትመጣም የሰባት ዓመት የጋዜጠኝነት ልምዷ አብሯት አለ፡፡ ኤዲትዝ የጋዜጠኝነት ሙያን የጀመረችው በKTN ቴሌቪዥን ጣቢያ የተካሄደ ውድድርን ካሸነፍች በኋላ ነበር፡፡ ከኬንያ ወጣቶች የቴሌቪዥን ዜና አቅራቢነት ተሰጥኦ ያላቸውን ለመምረጥ የተደረገዉን ውድድር ያሸነፈችዉ ኤዲትዝ በዚያው ጣቢያ «On the Record» የተሰኘ የራሷን ዝግጅት ጀመረች፡፡ በዚህም ከኬንያ ታዋቂ ወጣት ጋዜጠኞች መካከል ስሟ የሚጠራ ሆነ፡፡ ለከባቢያዊ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት የምትሰጠው ኤዲትዝ ዶይቼ ቬለ በዓለም የኢኮኖሚክ ፎረም ስብሰባ ወቅት በታዳሽ ኃይሎች ላይ ያዘጋጀውን ክርክር መርታለች፡፡ ወደ ጀርመን ከመምጣቷ በፊትም የዶይቼ ቬለ የምስራቅ አፍሪካ ወኪል እና ECO@Africa የተሰኘው ዝግጅት አቅርቢ ነበረች፡፡

ከአሜሪካ ደቡብ ወደ አውሮፓ እምብርት

በዶይቼ ቬለ The Day with Brent Goff የተሰኘ የራሱ ዝግጅት ያለው እና ዋና ዜና አቅራቢ የሆነው ብሬንት ጎፍ አደናጋሪ ትርክቶች እና ሀሰተኛ ዜናዎች በበዙበት በዚህ ዘመን ጠንቃቃ ጋዜጠኝነት ከምንጊዜውም በላይ ጠቃሚ መሆኑን ያውቃል፡፡ በአሜሪካ የኖርዝ ካሮላይና ገጠራማ ስፍራ ያደገው ጎፍ ጋዜጠኝነትን አሀዱ ያለው ሚዙሪ በሚገኝ አነስተኛ ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፡፡ የፎልብራይት ስኮላርሺፕን አግኝቶ በጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዲግሪ ትምሕርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ግን ትልቅ ጣቢያን ለመቀላቀል ያልም ያዘ፡፡ በርሊን በሚገኘው የCNN ቅርንጫፍ በአዘጋጅነት መስራት ሲጀምር የእርሱ ቦታ እንዲህ ዓለም አቀፍ ዜና የሚሰራበት  ሥፍራ መሆን አወቀ፡፡ ወደ ዶይቼ ቬለ በጎርጎሪያኑ 2000 የመጣው ጎፍ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከቀጥታ ስርጭት አቅራቢዎች መካከል በጣም የሚታወቅ ሆኗል፡፡ በበርሊን የዜና ክፍል እና በመላው ዓለም ባሉ ተመልካቾቹ ዘንድም በታታሪነቱና ብርታቱ ይታወቃል፡፡

ሐገረ ብዙዉ

ጀዓፈር አብዱልከሪም የተወለደው ላይቤሪያ፤ ያደገው  ሊባኖስ እና ስዊትዘርላንድ ነው፡፡ የተማረዉ በፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ብሪታንያ ነዉ፡፡ አሁን በበርሊን የዶይቼ ቬለ ባልደረባ ሆኖ እየሰራ ይገኛል፡፡ በአረብኛ ቋንቋ የሚተላለፈው እና ሽልማት ያስገኘለት Shababtalk በተሰኘው የወጣቶች ዝግጅቱ ወደ አረቡ ዓለም ተጉዞ ዘገባዎች ሰርቷል፡፡ ወጣቶች፤ ለመናገር አይነኬ በሆኑ ርዕሶች ላይ ሳይቀር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንዲናገሩ መድረክ ሰጥቷቸዋል፡፡ የቅርብ ጊዜ ስራው በስደተኞች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የስደተኞችን ድምጽ ለማሰማት በሊባኖስ ከሚገኘው ባር ኤልያስ እስከ ዮርዳኖሶቹ ሌስቦስ፤ ዛዓታሪ የስደተኞች መጠለያዎች ድረስ ተጉዟል፡፡ በጀርመን ያሉ የስደተኛ መቀበያ ማዕከላትንም አካሏል፡፡