1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በርሊን ፤ ለግሪክ የሜርክልና የሳርኮዚ ጥሪ

ዓርብ፣ ሰኔ 10 2003

የጀርመንና የፈረንሳይ መሪዎች ግሪክን ከፋይናንስ ቀውስ የሚታደጋት አዲሱ የብድር መርሀ ግብር በተቻለ ፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ አቀረቡ ።

https://p.dw.com/p/RUMm

ዛሬ በርሊን ውስጥ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚ ጋር በጉዳዩ ላይ የመከሩት የጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በተቻለ ፍጥነት ለችግሩ መፍትሄ መሻት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል ። ሜርክል ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ጀርመንና ፈረንሳይ በመጪው የአውሮፓ ህብረት ጉባኤ ላይ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥ እንደሚፈልጉ ያሳስባሉ ። ስለ መርሃግብሩ አስፈላጊነት ያወሱት ሜርክል የግሪክ መንግሥትና ተቃዋሚዎችም የበበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል ።

« ግሪክ አሁን ለምትገኝበት ተጨባጭ ሁኔታ አዲስ መርሀ ግብር ያስፈልገናል ። ይህ በአንድ በኩል ግሪክ ግዴታዋን መወጣቷን ይጠይቃል ። ትናንት በስልክ ከግሪኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ፓፓንድርዮ ጋር እንደገና ተነጋግሬ ነበር ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግሪክ ሃላፊነቷን እንዴት እንደምትወጣ እርሳቸውም ይህን ተፈፃሚ ለማድረግ ና አገራቸውም ትክክለኛውን አቅጣጫ እንድትይዝ በምን ዓይነት መንገድ ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ለማወቅ ችያለሁ ። እዚህ ላይ ላስታውሰው የምፈልገው ታቃዋሚዎች የግሪኩን ጠቅላይ ሚኒስትር ቢደግፉና አገሪቱ ቀናውን መንገድ እንድትከተል ለማብቃት ቢተባበሩ የሚበጅ ይሆናል። »

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኒኮላ ሳርኮዚም እንደ ሜርክል ሁሉ መንግስታቸው የአዲሱ መርሀ ግብር ደጋፊ መሆኑን አስታውቀው የግሪክ መንግሥት በጀመራቸው የተሃድሶ እርምጃዎች እንዲገፋም ጠይቀዋል ።

« እንደ ወዳጆቻችን እንደ ጀርመኖች ሁሉ እኛም ለግሪክ አዲስ መርሀ ግብር አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን ። የግሪክ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እናደንቃለን ። በተሀድሶውና በምጣኔ ሃብቱ የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎ ይበልጥ ለመጠናከር በተያዘው መንገድ እንዲገፋበትም እንጠይቃለን ። »

ሜርክልም የግሉ ዘርፍ በተሃድሶው ሂደት በፈቃደኝነት በመሳተፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት እንደሚፈልጉም ተናግረዋል ። ሁሉቱ መሪዎች በውይይታቸው ማጠቃለያ ስለ ግሪክ አጠቃላይ የፋይናንስ ይዞታ ከ3 ቱ የግሪክ ዓለም ዓቀፍ አበዳሪዎች ማለትም ከአውሮፓ ህብረት ፣ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት እና ከአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ሙሉ ዘገባ እንዲቀርብላቸውም ጠይቀዋል ።

ሂሩት መለሠ

ነጋሽ መሐመድ